የመሣሪያ እጥረት አላሰራ አለኝ ያለው ኢንስቲትዩት 14 ሚሊዮን ብር ተመላሽ አደረገ

0
461

በቤተ ሙከራ ዕቃዎች እጥረት የሚጠበቅበትን ተግባር ማከናወን እንደተሳነው የገለፀው የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 15 በመቶ የሚሆን በጀቱን ተመላሽ እንዳደረገ አሳወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በቤተ ሙከራ መሣሪያዎች እጥረት ምክንያት ለመሥራት መቸገሩ የተገለፀ ሲሆን፣ በጀቱ በመኖሩ ለመግዛት ጥረት ቢደረግም ግዢ ለመፈፀም በሚወስደው ረዥም ጊዜ ምክንያት ባለፈው ዓመት የበጀቱን 15 በመቶ ድርሻ የሚይዘውን 14 ሚሊዮን ብር ተመላሽ እንዳደረገ ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሕዝብ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ፍሬው ደረጄ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊ የሚባሉ የቤተ ሙከራ ዕቃዎች ከፍተኛ እጥረት አጋጥሞት እንደነበር አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በጤና፣ ግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ መንግሥት ትኩረት እንዲደረግ ቢፈልግም፥ ባለበት የምርምር መሣሪያዎች እጥረት ተገቢው ሥራ መከወን አልቻለም። በመሆኑም ዘጠኝ ዓይነት የምርምር ዘርፎችን የለየውና በእነዚህም ላይ ለመሥራት ያቀደው መንግሥታዊው ተቋም፥ በቤተ ሙከራ የመሣሪያ እጥረት የተሟላ ሥራ መከወን አለመቻሉን እወቁልኝ ብሏል።

የምርምር መሣሪያዎቹ የዋጋ ውድነት፣ የግዢ ሒደት መንዛዛትና የጊዜ ርዝማኔ፣ ግዢ እንዲፈፀም የሚጠየቁ መሣሪያዎች በመንግሥት ግዢ ኤጀንሲ አለመታወቃቸው፣ የተባሉት መሣሪያዎች ቢገኙም ተመሳሳይነት ወይም ተቀራራቢነት ያላቸው እንጂ ኦርጂናል መሣሪያዎች አለመሆን እና ተገዝተው አገልግሎት የማይሠጡ መሣሪያዎች መኖርም ለመሣሪያዎቹ እጥረት ዋነኛ ምክንያት ናቸው በሚል በዳይሬክተሩ ተዘርዝረዋል።

በዚህም ተቋሙ በጀት ቢኖረውም ግዢ ለመፈፀም ረዥም ጊዜ በመውሰዱና ተያያዥ ችግሮች በጀት ተመላሽ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ተቋሙ የምርምር ዘርፍ የተግባር ሥራ ክፍሎች እጥረት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፣ የላብራቶሪና የቢሮ ሥራን አንድ ላይ ቀላቅሎ እስከ መሥራት መድረሱንም አሳውቋል።

በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪው የሆኑት ብርሃን አዳሴ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ዘረመል የመለየት ሥራ ነው። ይሁንና ለተለያዩ የምርምር ሥራዎች ወሳኝ የሆኑ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በአፋጣኝ ቢያስፈልጉም ማግኘት አልቻሉም።

ከግዥ ጋር በተያያዘ የምርምር ባለሙያዎች የሚጠይቁትን ግብዓት በጥራትና በወቅቱ ማቅረብ መቻል ያስፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህ ካልሆነ የግዥ ሒደቱን ሙሉ ለሙሉ ለተቋሙ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል። መንግሥት የተቋማቱን የግዥ ሥራ በአንድና የተጠቃለለ ማዕቀፍ ለመፈጸም ሲል ከጥቂት ዓመታት በፊት በመንግሥት ግዥ ኤጀንሲ በኩል እንዲፈጸም መወሰኑ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here