– ሕገ ወጥ ለተባሉት ቤቶች መፍትሔ የሚሰጥ ጥናት እየተካሔደ መሆኑም ታውቋል
በድሬደዋ ከ2003 በኋላ የተሠሩ ቤቶች ሕጋዊ አይደሉም ሲል የድሬ ዳዋ መስተዳድር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ዳይሬክቶሬት አስታወቀ። በመስተዳድሩ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሳጂድ አሊዬ እየተስፋፋ የመጣውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለማስቆም እየተሠራ መሆኑን በተለይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከከተማዋ መግቢያ ጀምሮ መስፋፊያ በሆኑና በዙርያዋ ባሉ ለአሰፋፈር ምቹ ባልሆኑ ተራራማ ቦታዎች በሕገ ወጥ መንገድ ለዓመታት ሲገነቡና እስከዛሬ ድረስ የዘለቁት ሰፈራዎች ከተማዋን መልክ ማሳጣታቸውን ሳጂድ ይናገራሉ። ሳጂድ ዛሬ ላይ ጫፍ ደርሷል ባሉት የሕገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ እስከ ሃያ ሺሕ ሲገመት፣ ለችግሩ መባባስ ዋንኛ ካሏቸው ምክንያቶች ደግሞ መንግሥት ቦታ አዘጋጅቶ መስጠት አለመቻሉ እና በተለይ በሕገ ወጥ መሬት ወረራው ላይ አመራሩ ተሳታፊ መሆኑ ነው።
ዳይሬክተሩ፣ የመሬት ወረራው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረው፤ ከባለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ ይሠሩ የነበሩትን ቤቶች በማፍረስና ሕግ በማስከበር ተግባር ላይ በሥፋት መሰማራታቸውን ጠቁመዋል። በተለይ በአገሪቱ እየተካሔደ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ግርግር ለሕገ ወጦቹ ሌላ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረና ከሁሉ ባለፈ ግን በአስተዳደሩ የሕግ የበላይነትን በአግባቡ ማስከበር አለመቻሉ ችግሩን አባብሶታል ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ኃላፊው እንደሚሉት ቢዘገይም ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ተጀምሯል። በአስተዳደሩ ካቤኔ ተገቢ ውሳኔ ማሳለፍ የሚረዳ ጥናት እየተጠና መሆኑንና ይህም ከ2003 እስከ 2010 ድረስ ያሉ ግንባታዎችን የሚያካትት እና በዚያው ጊዜ ላሉት መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል።
ሳጂድ ከ2010 ጀምሮ እስከ ዛሬም ድረስ በመገንባት ላይ የሚገኙት ግንባታዎች እንዲፈርሱ እና ድርጊቱን የፈፀሙ አካለትም እንዲጠየቁ የማድረግ ውሳኔ መተላለፉን አስረድተዋል። አስተዳደሩ ማስጠንቀቀያ እየሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአንድ ቀን ዕድሜ ያውም ምሽቱን ብቻ በመጠቀም ተሰርተው የሚያድሩ ግንባታዎች ቁጥር በርካታ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አስታውቀዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011