ድሬና የጎዳና ላይ ምግቦቿ

0
1051

ሻሺ መርሻ ከአዲስ አበባ 450 ኪሎ ሜትር ርቃ ባለችው ድሬዳዋ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ገቢዋ አንስተኛ በመሆኑ ሕይወቷን መምራት ቀላል ሆኖላት አያቅም። በተለይም የከተማዋ ዕድገትን ተከትሎ የኑሮ ውድነቱ በመክፋቱ ሕይወቷን በአግባቡ ለመምራት ተቸግራለች ነበር።

ነገር ግን፤ ከዛሬ ሦስት ዓመት አንስቶ በጎዳና ላይ የሚሠሩ ምግቦችን በመሸጥ መተዳደር ከጀመረች በኋላ ነገሮች ቀለል ያሉላት ይመስላል። ዕድሜዋ በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ የሆነችው ሻሺ እንደዚህ ዓይነቱ ሥራ ላይ ለመሰማራት የወሰነችው የአክስቷን ውጤታማነት ከተለመከተች በኋላ መሆኑን ትናገራለች።

በሌሎች ነጋዴዎች ጭምር በቀዳሚነትና በመልካም አርዓያነታቸው የሚጠቀሱት አክስቷ፥ ከ10 ዓመታት በላይ በተለምዶ መናኻሪያ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ጣት የሚያስቆረጥሙ የጎዳና ላይ ምግቦች በመሸጥ ይታወቃሉ። ሻሺ አበዛሽ አበባ የተባሉት እኚህ አክስቷ መታወቅና ውጤታማ መሆን፥ ኮቴያቸውን እንድትከተል ገፊ ምክንያት እንደሆናት ሻሺ ታወሳለች።

ከዚያም ካራማራ ሆቴል አካባቢ ገባ ብሎ ባለ መንደር ውስጥ በግምት 20 ካሬ ሜትር በሚያክል ቦታ ላይ በተከለለ ክፍት ዳስ ውስጥ ነበር ሻሺ የጎዳና ምግብ ማቅረብ የጀመረችው፤ ውጤታማ ለመሆንም ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም።

˝በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶችና ሌሎች ነዋሪዎች የምሠራቸውን ምግቦች ጣዕም መውደዳቸው˝ ነው ትላለች ሻሺ ስለውጤታማነቷ ስትነናገር። የምትሠራቸው የምግብ ዓይነቶች ሦስት ሲሆኑ አንድ አስተናጋጅና አንድ ዕቃ አጣቢ አላት።

ሁሉም ዓይነት ምግቦች ቲማቲም፣ ድንችና ሰላጣ ያላቸው ሲሆን ቱና፣ እንቁላል ወይም አቮካዶ ገብቶበት እንደ ተጠቃሚው ምርጫ ይሠራል።

የምግቦቿ ዋጋ ከ20 ብር አንስቶ እስከ 80 ብር ሲሆን በቀን ቢያንስ ከ50 በላይ ሰዎች ታስተናግዳለች። ሥራ የሚበዛባት ወቅት ደንገዝገዝ ሲል ወደ 12 ሰዓት ገደማ ሲሆን ጠዋት እና ከሰዓት ቀዝቀዝ ያለ ነው። ከእሷ አጠገብ ያሉ ተመሳሳይ አግልግሎት የሚሰጡ ነጋዴዎችም ተመሳሳይ ዋጋ ያስከፍላሉ፤ ገበያቸውም ከእርሷ እምብዛም አይለይም። በርግጥ የገበያው ውሎ በከተማው ለፈሉት ሌሎች የጎዳና ላይ ምግብ ነጋዴዎችም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም።

ከድሬዳዋ ከተማ መገለጫዎች መካከል ናቸው የሚባሉት የጎዳና ላይ ምግብ አቅራቢዎች በዓይነታቸው የተለያዩ ናቸው። ጥቂቶቹ ጠዋት ላይ እንደ መለዋና ፈጢራ ያሉ ምግቦችን እንደ ተጠቃሚው ፍላጎት ከእርጎ ጋር በመደባለቅ በቁርስ ሰዓት በማቅረብ የተሠማሩ ሲሆን ብዙዎቹ ልክ እንደ ሻሺ ቲማቲም፣ ድንችና ሰላጣን በመጠቀም የሚሠሩ ምግቦችን በተለይ ደንገዝገዝ ሲል በማቅረብ ይታወቃሉ።

ደቻቱ፣ ላጋሬ፣ ገንደቁሬና አውቶብስ ተራ በጎዳና ላይ በሚሠሩ ምግቦች የሚታወቁ ሰፈሮች ሲሆኑ በየ200 ሜትር ልዩነት ተሰብስበው የሚመገቡ ወጣቶችን ማየት ለድሬ ነዋሪዎች የተለመደ የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነው። ከተማዋን የሞሏት የባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች ወይም በተለምዶ ባጃጅ ሾፌሮች የጎዳና ላይ ምግቦች በመጠቀም ቀዳሚ ሲሆኑ ተማሪዎችና የቢሮ ሠራተኞች ይከተላሉ።

ከተጠቃሚዎች መካከል አንዷ የሆነችው እፀገነት ደምሴ የድሬዳዋ ቴሌቭዥን ሠራተኛ ሆና መሥራት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የጎዳና ላይ ምግቦች ትጠቀማለች። እንደነዚህ ዓይነት ምግቦች የከተማዋ መገለጫ እየሆኑ መምጣታቸውን የምትናገረው እፀገነት በየቦታው በቀላሉ መገኘታቸው፣ የዋጋቸው ተመጣጣኝነትና ከኅብረተሰቡ ባሕል ጋር የተቆራኙ መሆናቸው ለመብዛታቸው ምክንያት ነው ትላለች።

ለአብነትም የራሷን አጋጣሚ ታነሳለች። የጎዳና ላይ ምግቦች የምጠቀመው ከጓደኞቼ ጋር ለመዝናናት ስንወጣና አብረን ተሰብስበን ለማወጋት ስናስብ ነው ትላለች፥ ከአምስት ዓመታት በላይ በድሬዳዋ የኖረችው እፀገነት።

እንደ ሜሮን አሰፋ ያሉ ተጠቃሚዎች ደግሞ የጎዳና ላይ ምግብ ያለው ጥቅም ከመዝናኛነት እና ከማውጊያነት በላይ ነው። ˝ምግቦቹ ጣፋጭ በመሆናቸው በሳምንት ቢያንስ ለሦስት ቀናት እጠቀማለው˝ ያለችው የድሬዳዋ ተወላጇ ሜሮን ˝በከተማው ካሉ ምግቦች በተለይም ለእራት የምትመርጠው የጎዳና ላይ ምግቦች እንደሆነ˝ ታነሳለች ሜሮን።

እንደ እፀገነትና ሜሮን ላሉ ተጠቃሚዎች የጎዳና ላይ ምግቦች የደስታ ምንጭ ሲሆኑ ለእቴኑ ግርማ ደግሞ ከፍተኛ የገቢ ምንጮች ናቸው። ላለፉት አምስት ዓመታት በዚህ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሠማራቸው እቴኑ አራት ዓይነት የጎዳና ላይ ምግቦች የምታቀርብ ሲሆን በቀን ከ100 የሚያንሱ ተጠቃሚዎች አሏት። የምግቦቿ ዋጋ ከ20 ብር አንስቶ እስከ 80 ብር ይደርሳል።

ድንች፣ ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ እንቁላል፣ ቱና፣ አቮካዶ እና ሙዝ ያሉ ግብዓቶችን ምግቦቿን ለማዘጋጀት ትጠቀማለች።

የእነዚህ ግብዓቶች እጥረት በተለይም የአትክልቶች ሥራ ላይ የሚገጥማት ትልቁ ተግዳሮት ሲሆን የምግቧ ጣዕም ሁሌም ተመሳሳይ መሆኑ በፍጥነት ውጤታማና ታዋቂ እንድትሆን ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ በቀን ከ1500 ብር በላይ ገቢ የምታገኘው እቴኑ ታወሳለች።

በሌላ በኩል፤ እንደ እቴኑ ዓይነት የጎዳና ላይ ምግብ አቅራቢዎች ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞ የሚነሳው የጤና ጉዳይ ሲሆን ምግቦቹ በሚቀርብባቸው አካባቢ ንፅሕና የተሟላ እጅ መታጠቢያ አለመኖሩ እንደ እክል ይነሳል።

በተጨማሪ፤ ምግብ አቅራቢዎቹ በአብዛኛው የሚጠቀሙት የጥራት ችግር አለበት ተብሎ የሚታማውን የሚረጋ ዘይት መሆኑ በሰው ጤና ላይ ችግር እንዳያስከትል ሥጋት አለ። ምግቡን የሚሠሩት ሰዎች ገንዘብም ተቀባይ መሆናቸው አንዳንድ ተጠቃሚዎችን ለበሽታ እንዳጋለጣቸው ይነሳል።

ከዚህ ባሻገር የጎዳና ላይ ምግቦች በሚቀርቡበት አካባቢዎች ከፍተኛ የመኪና ፍሰት መኖሩ ተጠቃሚዎች ለመኪና አደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ግልፅ ነው። ይህ ዓይነቱ ችግሮች ግን ለእንደ ሜሮን ላሉ ተጠቃሚዎች አስጊ አይመስሉም። ˝ድሬን የሚገልጿትን የጎዳና ላይ ምግቦች ምንም ይሁን ምንም አለመጠቀም ከባድ ነው፥ ምክንያቱም ባሕላችን ስለሆነ ነው˝ ትላለች ሜሮን።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here