22 ዩኒቨርሲቲዎች በ1.4 ቢሊዮን ብር የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ሊገዛላቸው ነው

0
425

የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ በሚመጡት ሦስት ዓመታት የማዕቀፍ ግዥ እቅዳቸውን በወቅቱ ላቀረቡ 22 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚሰጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እቃዎችን ለመግዛት ከስድስት ድርጅቶች ጋር የ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ውል ተፈራረመ።

ለ187 የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚውሉ እቃዎችን ለመግዛት ኤጀንሲው ከአራት ድርጅቶች ጋር በ400 ሚሊዮን ብር ውል እንደተፈራረሙ የኤጀንሲው ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሰፋ ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ገልፃዋል።

በኹለቱም የግዥ ጨረታዎች ብሪጅ ቴክ፣ ሐሮን ኮምፒዩተር፣ አልታ ኮምፒቴክ እና ናሽናል ማርኬተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የድርጅት አሸናፊ ሆነዋል። ፍሊከር ትሬዲንግ እና ዲሲል ትሬዲንግ ደግሞ ለዩኒቨርሲቲዎቹ ብቻ እቃ ለማቅረብ ያሸነፉ ተጨማሪ ድርጅቶች ናቸው።

ለ22ቱ ዩንቨርሲቲዎች 6 ዓይነት እንዲሁም ለ187ቱ የፌደራል መንግሥት ተቋማት 8 ዓይነት እቃዎችን ለማቅረብ ውል ከተፈራረሙት አንዱ የሆነው አልታ ኮምፒ ቴክ ለኹለቱም ግዥዎች ለሚያቀርባቸው የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች 780 ሚሊዮን ብር ተስማምቷል።

ሐሮን ኮምፒተር ደግሞ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን በ681 ሚሊዮን ብር ለማቅረብ ውል አስሯል። ብሪጅ ቴክ የ253 ሚሊዮን እና ናሽናል ማርኬተርስ የ158 ሚሊዮን ብር ሲፈራረሙ ለዩንቨርሲቲዎች ለሚያቀርቡት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ደሞ ፍሊከር ትሬዲንግ የኹለት ሚሊዮን ብር እንዲሁም ዲሲ ኤል ትሬዲነግ የ703 ሺሕ ብር ውል ተፈራርመዋል።

አቅራቢ ድርጅቶቹ ከሚያዝያ መግቢያ ጀምሮ እቃዎችን ማስገባት የሚጀምሩ ሲሆን የአገር ውስጥ ምርቶች በአንድ ወር፣ ከውጪ የሚገቡት ምርቶች ደግሞ በኹለት ወር ጊዜ እንዲያቀርቡ ውል ገብተዋል ነው የተባለው።

ኤጀንሲው ሥራ ከጀመረበት 2004 ጀምሮ ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የማዕቀፍ ስምምነት ግዥ የፈፀመ ሲሆን፣ ከ2008 እስከ 2010 ባሉ ዓመታት ከ49 አቅራቢ ድርጅቶች 323 ዓይነት እቃዎችን ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መግዛቱን አሳውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here