‘‘በጋራ አለመስራታችን ለፖለቲካ ነጋዴዎች ሰለባ እንድንሆን አድርጎናል‘‘

0
341

ሰላማችንን ለማስጠበቅም በጋራ ተቀናጅተንና ተናበን አለመስራታችን ለፖለቲካ ነጋዴዎች ሰለባ እንድንሆን አድርጎናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ገረሱ ተናገሩ።

መጋቢት 19/2011 በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መገባቱን የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ኃላፊዎች ተናግረዋል። ጉዳዩን አስመልክቶ ሐሙስ የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ኃላፊዎች በባህርዳር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አለበል አማረ (ኮሎኔል) ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን ተከትሎ መልካም የሆኑና ያልሆኑ ነገሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውንና፣ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ህዝቦች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ማስተዋል እየተለመደ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ቢሮዎች ተገናኝተው በመምከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ መፈናቀል እንዲቆምና የተፈናቀሉትም ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች የመለየት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ገረሱ በበኩላቸው “ለውጡ እንዲመጣም ሁለቱ ክልሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ለአሁኑ ዕድል እንድንበቃ ያስቻሉን በመሆኑም ማንም ጥቅሙ የተነካበት የፖለቲካ ኮንትሮባንዲስት ህዝቦቹን የሚያጋጭበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም” ብለዋል።

ለውጡን ለማስቀጠልና የበለፀገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባትም ሁለቱም ህዝቦች ከአሉባልታ ርቀው ለዘላቂ ሰላማቸው ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። “ዘላቂ ሰላማችንን ለማስጠበቅም በጋራ ተቀናጅተንና ተናበን አለመስራታችን ለፖለቲካ ነጋዴዎች ሰለባ እንድንሆን አድርጎናል” ሲም አሳስበዋል።

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ወረዳ እና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ከ400 በላይ የአርጎባ ማኅበረሰብ አባላት ከመተሐራ ከተማ ተፈናቀሉ። ከተፈናቃዮቹ ጋር የተያያዘ መረጃ ከተሰራጨ በኋላ የአማራ ክልል በሥፍራው በመገኘት ለተፈናቃዮቹ እርዳታ ማቅረብ መጀመሩን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አሰማኸኝ አስረስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አሁን በአዋሽ ከተማ በሚገኝ መጠለያ የሚገኙት ተፈናቃዮች እንደሚሉት “የከተማው ወጣቶች እና በቄሮ ሥም ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባሰቡ አሉ። ውጡ ውጡ፤ አደጋ ይደርስባችኋል፤ አለዚያ ከነቤታችሁ ትቃጠላላችሁ” የሚሉ ማስፈራሪያዎች ይደርሷቸው እንደነበርና፣ “ሥራ ቦታ ቁጭ ባልኩበት መጥተው የአካል ጉዳት አድርሰውብኛል። ጥርሴ ተሰብሯል፤ ተደብድበናል። የሕግ አካል መጥቶ የጠየቀን የለም። ምን ደረሰባችሁ ያለ የለም” የሚሉት ተፈናቃዮቹ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይሁኑ የጸጥታ አስከባሪዎች ይደርሱባቸው ለነበሩ ማስፈራሪያዎች ትኩረት እንዳልሰጡ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በመጋቢት 17/2011 አስታውቀው ነበር።

ምንጃር ሸንኮርና አዋሽ ሰባተኛ ለሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታ እየደረሳቸው መሆኑን የነገሩን አሰማኸኝ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ተናግረው ተፈናቃዮቹ ሰላማቸው ተጠብቆ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ይደረጋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በመተሐራ ከተማ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት የሸሹት አብዛኞቹን ወንዶች ሲሆኑ፣ በአማራ ክልል ምንጃር ወረዳ ነዋሪዎች እና በፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ከዚህ ቀደምም በግጦሽ መሬት ሳቢያ ግጭቶች ነበሩ።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here