– ግንቦት 2/2011 በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲ ይፋ ይሆናል
አሁን ያለውን የለውጥ ሒደት የሚገዳደሩ የዘረኝነት በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋታቸውን በጋራ የሚመሰረተው አዲስ አገራዊ ፓርቲ መሥራች ግብረ ኃይል ከትላንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ የሚፈታው በሰለጠነ የዜግነት ፖለቲካ ብቻ መሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል።
በወቅቱ መግለጫውን ከሰጡት አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት ተወካይ አንዷለም አራጌ፣ አሁን ያለውን የለውጥ ሒደት የሚገዳደሩ የዘረኝነት በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን ጠቁመዋል፣ እንደሳቸው ሐሳብ ይህንን የዘረኝነት ጋንግሪን ለማጥፋትም ትልቁ የመፍትሔ ሐሳብ የሚሆነው ኅብረ ብሔራዊነት ነው።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ማለት ማንኛውም ሕዝብ በየትኛውም ቦታ ያለመሸማቀቅ የሚኖርበትና የፈለገውን የሚመርጥበት ማለት መሆኑን አውስተው፣ በየክልሉ የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችና መፈናቅሎች እልባት እንዲበጅላቸው አሳስበዋል። ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመስረት ሳይቻል ስለ ዴሞክራሲ ማውራት እንደማይቻልም ተናግረዋል።
በየቦታው ስብሰባ የምናደርገው አገሪቱን የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት እንጂ ለምረጡኝ ቅስቀሳ አይደለም ያሉት ብርሃኑ የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ሆን ብለው የሚሠሩ ኃይሎች በመኖራቸው የአገሪቱ ሕዝቦች የእነሱን አካሔድ እንዲረዱት ለማድረግና ለማስተማር እንደሆነ መልሰዋል።
ለውጡ ሥጋት ላይ መሆኑን ያስታወሱት አንዷለም፣ አሮጌው ስርዓት ለመሞት፣ አዲሱ ስርዓት ደግሞ ለመወለድ ትግል ላይ መሆናቸውን በማንሳት፣ ከላይ ሆነው የሚያራግቡ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ችግሩ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም በላይ አለመሆኑን በመጠቆም።
ወደፊት በሚኖረው አገራዊ ምርጫ ሕዝቡ የታገለለት ዓላማ ግቡን እንዲመታና ጥሩ አማራጭ እንዲያገኝ በተጠናከረ ፕሮግራምና በጠራ ፖሊሲ የተደራጁና በሐሳብ የተደራጁና በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር እንደሚገባቸው መግለጫው ያስታወቀ ሲሆን፣ እንደመግለጫው ገለጻ ይህንን የአገርና የሕዝብ ጥያቄ በመቀበል ስድስት የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
አገር ዐቀፉን እንቅስቃሴ ሌሎችም የክልልና አገር ዐቀፍ ድርጅቶችና ስብስቦች እንዲቀላቀሉ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚያስተባብሩ አገር ወዳድ የአገር ሽማግለሌዎች በሚያደርጉት ጥረት አሁን ካሉት በተጨማሪ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦች ተካተው እንደሚሠሩ ትልቅ እምነት እንዳለውም አስታውቋል።
ግብረ ኃይሉ በነገው ዕለት ከ350 በላይ ለሚሆኑ አባላቱ በመሰረታዊ የደንብና የፕሮግራም ፅንሰ ሐሳቦችና በፓርቲዎች ሥነ ምግባር የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ የአሰልጣኞች ሥልጠና ይሰጣል። በሳምንቱ መጋቢት 28 እና 29/ 2011 ደግሞ እነዚሁ ሰልጣኞች በየምርጫ ወረዳዎቹ በመሔድ የሠለጠኑባቸውን ነጥቦች መልስው በማሰልጠን የምርጫ ወረዳውን አስመራጭ ኮሚቴ ያስመርጣሉ።
ሚያዝያ 6/2011 በሁሉም የምርጫ ወረዳዎች የፓርቲ መሪዎችና የጉባኤ ተወካዮች ይመረጣሉ። እስከ ሚያዝያ 30/2011 ባሉት ሦስት ሳምንታትም በደንቡ፣ በፕሮግራሙና በፖሊሲዎቹ ዙሪያ በመወያየት ለጉባኤው የሚሆን ግብዓት ያመጣሉ።
ከእነዚህ ሒደቶች በኋላ ግንቦት 1 እና 2/2011 የሚካሔደው የአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሥራች ጉባኤ የፓርቲውን ደንብ፣ ፕሮግራም፣ ሥያሜና ዓርማ ያጸድቃል። የፓርቲውን አመራር ይመርጣል፤ ዜግነትንና ማኅበራዊ ፍትሕን መሰረት ያደረገውና የምርጫ ወረዳን መነሻ በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲ ይፋ ይሆናል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011