የኦዴፓ እና የአዴፓ (በቀድሞ ሥማቸው ኦሕዴድ እና ብአዴን) ኅብረት የሕወሓትን የበላይ አገዛዝ እንዳስወገደ በብዙዎች ዘንድ ሥምምነት አለ። ግዛቸው አበበ ይህ ጥምረት የጀመረውን ለውጥ ከግብ እንዳያደርስ የተደቀነበት ፈተና የኦሮሚያ እና የአማራ ሪፐብሊኮችን መመሥረት የሚፈልጉ ፖለቲከኞች የሚያራግቡት ግጭት ነው ብለው ጽፈዋል።
የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሆኑ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ሁሉ እንደ እኩያ ድርጅቶች መታየት እንደሚገባቸው ጥያቄ የለውም። ነገር ግን በሕወሐት/ኢሕአዴግ ቤት በዳበረው ባህል መሠረት ሕወሓት ሌሎችን ድርጅቶች ሲያሰኘው በአሻንጉሊትነት እያሽከረከረ ሲፈልግም እየደቆሰ ቀጥቅጦ ሲገዛቸው ነበር የታየው።
በዚህ ወቅት የሚባሉትና ሲከወኑ የሚታዩት አንዳንድ ነገሮች ልብ ብሎ መመልከቱ ‘ኦዴፓ እና አዴፓ እንዴት ይሆን አብረው የሚዘልቁት?’ የሚል ጥያቄ ማንሳትን ተገቢ ያስመስለዋል። ኦዴፓ በውስጡና በውጭ ጠንካራ ጫና እያረፈበት መሆኑን የሚያሳብቁ በርካታ ጉዳዮች እየታዩበት ሲሆን፥ አዴፓ ደግሞ በውስጡ መጠነኛ በውጭ በኩል ግን በጣም አደገኛ ጫናወች እያረፉበት መሆኑ በግልጽ ነው። በኹለቱም ቡድኖች ላይ ጫና የሚያሳርፉት ወገኖች አንድም እኛ እንሻላለን የሚል ሕዝብ ላይ በማሳረፍ ለቀጣዩ ምርጫ የሚያሸንፉበትን መንገድ እየቀየሱ ሲሆን፥ በልላ በኩል ግን ኹለቱ ቡድኖች ኢትዮጵያውያንን በተለይም አማራውንና ኦሮሞውን በማቀራረብ ታላቅ ኢትዮጵያን መልሶ እውን የማድረግ ዓላማቸውን እንዳያሳኩ ለማድረግ ግጭትና ብጥብጥ ለመፍጠር የከጀሉ ወገኖች የሚፈጥሩት ጫና እንዳለ መጠራጠር አይገባም። ከ2008 ጀምሮ አመፅ ሲካሔድ ኢትዮጵያ ፈራርሳ ብሔር ተኮር አገር መመሥረት የሚችሉበት ጊዜ መምጣቱን እርግጠኛ በመሆን ቋምጠው ይጠባበቁ የነበሩ ወገኖች የ‘ቲም ለማ’ መነሳት አንጀትን የሚያሳርር አጋጣሚ እንደሆነባቸው የታወቀ ጉዳይ ነው።
ሕወሐት አገሪቱን የማራቆትና ሕዝቦቿን ረግጦ የመግዛት አጀንዳውን ለማራመድ እንደ ዋና ስትራቴጅ አድርጎ ሲጠቀምበት የኖረው የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች ጭድና እሳት ወይም እሳትና ቤንዚን እንዲሆኑ በማድረግ ተቀናቃኝን ማዳከም የነበረ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅና በይፋም የተነገረ ጉዳይ ነው። በአማራ እና በኦሮሚያ የተቀሰቀሱትን አመፆች ተከትሎ ብአዴን እና ኦሕዴድ በየተራ ሕወሓትን መገዳደር መጀመራቸው ለሕወሓት ጉልበተኛ አካሔድ ገደብ ወደ መሥራት አምርቷል። ይህን ተከትሎ የኦሕዴድ አመራሮች በተለይም የተከበሩ ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ የሕወሓትን የማጋጨት ስትራቴጂ ወደ መቃብር ለማውረድ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አስከትለው ወደ አማራ ክልል በመጓዝ ኹለቱ ሕዝቦች ለጥቅማቸው ብቻ ሳይሆን ለሕልውናቸው ሲሉ ወደ ቀድሞው አብሮነታቸው መመለሳቸው አማራጭ የሌለው ግዴታቸው መሆኑን በይፋ በመናገር የአብሮነት መልሶ ግንባታውን በይፋ ጀምረውት ነበር።
ይህ ሥራቸው በኢትዮጵያዊነታቸው በሚኮሩ እልፍ አእላፉ ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ደስታንና አለኝታ የማግኘት ትልቅ መንፈስ ፈጥሮ ነበረ። ይህ የለማ መገርሳ ጉዞ በርካታ የሕወሓት ባለሥልጣናትን ስሜታቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ እንዳስቆጣቸውና ስጋት ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ግልጽ ነው። የሕወሓት ባለሥልጣናት ወደ ቀድሞው የበረሀ አስተሳሰባቸው ተመልሰው ‘የቀድሞ ጠላቶችህ ተባብረው ተነሱብህ’ ሲሉ የትግራይን ሕዝብ ማስጠንቀቅ ጀምረዋል። የክልሉን ገዥ ደብረፅዮንን ጨምሮ በብዙ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች በየወረዳውና በየከተማው እየተገኙ ሰፊ የቅስቀሳ ሥራ የሠሩበት ከመሆኑም በተጨማሪ ‘ሰብ ሕድሪ ትግራይ’ (የትግራይ ባለ አደራወች) የሚል ቡድን በየዞኑና በየወረዳው ተቋቁሞ ‘ትግራይና ትግራዋይ አለቀላቸው’ የሚል ሥጋት ያጠላበት ውይይት በማካሔዱ ሕዝቡ ለጦርነት እንዲዘጋጅ በግልጽ እየሰበከ ነው።
‘የአማራ ሪፐብሊክ ምሥረታ’
በኦሮሞ ወገኖቻችን በኩል ኦሮሚያን የመገንጠል አጀንዳ እንዳለ ሁሉ በአንዳንድ የአማራ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በኩልም በግልጽ ለሕዝብ ያልተነገረ ነገር ግን ተሸፋፍኖ የሚብሰልስል የአማራ ሪፐብሊክ ምሥረታ (የብሔረ አማራ መንግሥት ምሥረታ) የሚል የመገንጠል አጀንዳ መኖሩን ማወቅ ተገቢ ነው። ‘ነጸብራቅ ቅጽ 1 – አዳኝና ገዳይ’ እና ‘ነጸብራቅ ቅጽ 2 -ፋና ወጊወች- የወያኔ ሴራ’ በሚሉ አርዕስቶች በ2010 የታተሙ መጽሐፍት የአማራ አገር ግንጠላ በይፋና በድፍረት የተነገረባቸው፣ አጀንዳውም ወደ ‘ትግል ሜዳ’ ሳይሆን ወደ ‘ገበያ’ የወረደባው የመጀመሪያ ሥራወች ናቸው። ይህ አጀንዳ በኢትዮጵያ ምድር ላይ በይፋ ሲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሁን እንጅ በውጭ አገር ለዓመታት ሲታቀድና ካርታ ተሠርቶለት ሲፎከርበት የቆየ ጉዳይ ነው።
ነፀብራቅ በተባሉት መጽሐፍት ላይ ሕሊናቸው ከማይቆጠቁጣቸው ሰዎች ልቦና ብቻ ሊመነጩ የሚችሉና ይሉኝታ ያልጎበኛቸው በርካታ ልብ ወለድ (የፈጠራ) ወሬወችን በኢምንት እውነት አጅለው የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባር ስለሚባል ቡድን ሰፊ ወሬ ይነዛሉ። የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባር ወደ ዐሥራ ኸለት ሺሕ አምስት መቶ ተዋጊዎችን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ አሠማርቶ ቤተ መንግሥቱን በማጥቃት፣ በኀይል የታገዘ መፈንቅለ መንግሥት በማካሔድ ወያኔን የማስወገድ ዕቅድ ይዞ ተንቀሳቅሶ ዕቅዱ በትንሽ ስህተት (ወታራዊ የመገናኛ ሬዲዮ በመረሣቱ) መክሸፉን የሚነግሩን እነዚህ መጽሐፍት፥ ከዚህ ክሽፈት በኋላም ግንባሩ በርካታ ውጊያዎችን በጎጃም፣ በጎንደርና በሰሜን ሸዋ አካሒዶ በርካታ የሻዕቢያና የወያኔ ታጣቂዎችን መግደሉንና መማረኩን ያትታሉ። የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባር ዋና ዓላማ የአማራ ሪፐብሊክን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ የተበተነውን የአማራ ሕዝብ አሰባስቦ መኖር መሆኑን የነገሩን እነዚህ መጽሐፍት የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ግብም ይኸው አማራን መገንጠልና ከኢትዮጵያ ውጭ ማኖር መሆኑን ይተርኩልናል። እንደ መጽሐፍቱ የታሪክ ሐተታና እንደ ግንባሩ እምነት የብሔረ አማራ መንግሥት ምሥረታ ትግል የተጀመረው በዐፄ ልብነድንግል እንደነበረና ፕሮፌሰር አሥራት ይህን የዐፄውን ዓላማ አንግበው የብሔረ አማራ መንግሥት ለመመሥረት በከተማ መዐሕድን በዱር ደግሞ የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባርን አሠማርተው ነበረ ይለናል። የዐፄ ልብነድንግልና የግንባሩን ዓርማ አንስተን እንጋደላለን የሚሉን የዚህ መጽሐፍ አሳታሚዎችና የዘመናች ሰዎች፥ ኹለቴ ተሞክሮ የከሸፈው የብሔረ አማራ መንግሥት ምሥረታ በእነሱ ሦስተኛ ጥረት እንደሚሳካ ዝተዋል።
ከመጽሐፎቹ ሽፋን በአንደኛው ላይ ምርጫው የእናንተ ነው ብለው ከእርግብና ከክላሽንኮቭ አንዱን እንዲመርጡ ይፋ ላላደረጉት ጠላታቸው አሳውቀዋል። እነዚህ ሰዎች በፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ላይ ጥርሳቸውን ቢነክሱና ጥረታቸውን ቢያጣጥሉ የሚገርም አይሆንም። እነዚህ የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባር የሚባው ቡድን አርማ አንጋቾች በአሁኑ ወቅት አማራው ኢትዮጵያዊነቱን አቅልሎ እንዲመከለት የሚገፋፉ መጽሐፍትን ማሳተማቸውን ቀጥለዋል። ‘አማራው ሕዝብ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ ያተረፈው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን በማይወዱ ሕዝቦች ተጠልቶ መኖርን ነው’ ይላሉ።
አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አማራ ክልል ተጉዘው ሕዝብ ሰብስበው ለማናገር ሲፈልጉ የሚሰነዘረው ማስጠንቀቂያ፣ የሚፈጠረው ውዝግብና የሚሰነዘረው ሕገ ወጥ እርምጃ ከዚህ ጠባብነትና ፀረ ኢትዮጵያዊነት የመነጨ መሆኑን መገመት ይቻላል። እነዚህ ከአማራ ሕዝብ የተገኙ ወገኖች የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል የፖለቲካ ድርጅት፣ አክቲቪስት፣ ፖለቲከኛና ጋዜጠኛ ጠላቶች ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን በመገኛና ብዙኀን በኩል ከሚሠራጩት መልዕክት ብቻ ሳይሆን ብልጭ ድርግም ከሚሉ ተግባራዊ ትንኮሳዎቻቸው መረዳት ይቻላል። እነዚህ ወገኖችና ተከታዮቻቻው በአዴፓ፣ በኦዴፓ፣ በፕሬዚደንት ለማ መገርሳና በሌሎችም ሰዎች ላይ ትንሽ ስህተት እየፈለጉ ለማቃለል ከመሞከር አልፈው ሕዝብ ለማነሳሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ በግልጽ እየታየ ነው።
በኦሮሚያና በአማራ ሕዝብ ውስጥ የተሰገሰጉት ጠበብ አጀንዳ ያነገቡ ቡድኖችና ግለሰቦች ለኦዴፓ እና ለአዴፓ ጠላት ከመሆን አልፈው ኹለቱ ቡድኖች በመተባበር ሊያከሽፍት የቆሙለትን የሕወሓትን ሕዝብን የመነጣጠልና አገር የማፈራረስ አጀንዳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለማስቀጠል በብርቱ የሚፈልጉ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። ይህን ማድረግ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲንና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን የሚያጋጩ አጀንዳወችን ከማራገብ ጀምሮ፣ ኹለቱ ቡድኖች በየሕዝቦቻቸው በጥርጣሬ ዓይን እንዲታዩ በማድረግ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኹለቱ ገዥ ፓርቲዎች በሕዝባቸው እንዲጠሉ የሚያደርጉ አጣብቂኞችን በመፍጠር፣ አናቋሪ ተግባራትን በመፈፀምና በማስፈፀም ትርምስ ለመፍጠር እንደሚሞክሩ መጠራጠር አይገባም።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለማ መገርሳ ኦሮሞን የካደ ዳግማዊ ጎበና ነው፤ ኦዴፓ የኦሮሚያን ጥቅም አሳልፎ እየሰጠ ነው ወዘተ… የሚሉ ሥም ማጥቆሪያወች ሆነ ተብለው እየተናፈሱና ቄሮዎች ለቲም ለማ እና በኦዴፓ ላይ አመፅ እንዲያካሒዱ እየተገፋ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኦዴፓ በሚያካሒዳቸው ስብሰባወች ወይም አቶ ለማ በሚገኙባቸው ስብሰባዎች አንድም ብስለት የጎደላቸው ወገኖች በየዋሕነት የሚያነሷቸው፣ በሌላ በኩልም ኦዴፓንና ፕሬዚደንት ለማን አጣብቂኝ ውስጥ ለመቀርቀር ሆነ ብለው የማይመለሱ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሴረኞች አሉ። በተለይም በፌደራል መንግሥት ወይም በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሪፈረንደም ውሳኔ ማግኘት የሚገባቸውን ነገሮች በፕሬዚደንት ለማ ወይም በኦዴፓ ብቻ ምላሽ የሚሰጣቸው አስመስለው የሚያቀርቡ ሴረኛ ወገኖች ኦዴፓን ከአጣብቂኝ ለመውጣት ሲሉ በሚሰጧቸው አስተያየቶች በሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ የለውጥ ጠላቶች ተቀልበው ሌላው ሕዝብም ፕሬዚደንት ለማን እና ኦዴፓን በጥርጣሬ ዓይን እንዲያያቸው ጭምር ጠቃሚዎች እየሆኑ ነው።
የለገጣፎው ቤት የማፍረስ ዘመቻ እና አዲስ አበባን/ፊንፊኔን በሚመከለከት የኛ/ኬኛ የሚለው ከኦሮሞና ከአማራው ውጭ ያለውን ሕዝብ በዘነጋና ማስተዋል በጎደለው መልኩ በመካሔድ ላይ ያለው ዘመቻ የኦነግ ቅሪቶች፣ የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባር ወራሾች ነን ባዮችና የሌሎች ፀረ ለውጥና ፀረ አንድነት ግለሰቦችንና ቡድኖችን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ሲሉ የሚያጮሁት አጀንዳ የታጨቀባቸው ግርግሮች ከመሆን የዘለሉ አይሆንም። በለገጣፎ በርካታ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤቶች ፈርሰው ሕዝብ እንደ አልባሌ እቃ፣ ሜዳ ላይ መጣሉን ተከትሎ በተከተለው ውዝግብ አንዳንድ የኦዴፓ አመራሮችና የኦሮሚያ አክቲቪስቶች ‘ምን ታመጣለህ/’ ‘የፈለገውን ያህል ቤት አፈራርሰን ቦታውን ፈረስ መጋለቢ እናደርገዋለን’ የሚሉና የመሣሰሉ የትዕቢት መልሶችን በብሔራዊና በክልላዊ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀንና በማኅበራዊ ገጾቻቸው መሰንዘራቸው በጃኬታቸው ሥር የኦነግ የቀድሞ ማሊያ በቦታው እንዳለ መሆኑን የሚያጋልጥ ነው።
ኦሮሞ እና አማራን ማቀራረብ፦ ማዘናጊያ?
አሁን አሁን በፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ተነሳሽነት ተጀምሮ የነበረው ኦሮሞንና አማራን የማቀራረብ ሥራ በሌላው ወገን ባሉ፣ በአገር ቤትና በውጭ የሚኖሩ አክቲቪስቶችና የሰብኣዊ መብቶች ጠበቃ ነን ባይ ግለሰቦች እንደ ማታለያና እንደ ማዘናጊያ ተቆጥሮ ፕሮፓጋንዳ እየተሠራበት ነው። አሁን አሁን በኹለቱም ወገኖች (በኦሮሞና በአማራ) በኩል አቀራራቢና አስታራቂዎች እየጠፉ አናቋሪዎች እየበዙ መሆኑ እየታየ ነው።
አዴፓ እና ኦዴፓ ዝምታቸውን መስበርና የሚደረገውን ነገር ሁሉ ያላዩና ያልሰሙ መስለው ከማድፈጥ ወጣ ብለው እርስ በርሳቸውም ኾነ ኹለቱን ቡድኖች በአንዴ ሊረግጡ ከሚያደቡ ፖለቲከኞች፣ አክቲቭስቶችና ጋዜጠኞች ጋር ሕዝብ ታዛቢ በሆነበት ግልጽ መድረክ መነጋገር ወይም በሐሳብ መፋለም ይገባቸዋል። ሕዝቦቻቸው ሲወናበዱ፣ ወጣቶቻቸው ለግጭት ሲገፋፉ፣ ምስኪኖች የሴረኞችና የጠባቦች ሰለባ ለመሆን ሲዘጋጁ በዝምታ ማየት የለባቸውም። የአዲስ አበባ ወይም የፊንፊኔ ጉዳይ አነጋጋሪ ከሆነ በነጻነትና በእኩልነት ሊነጋገሩ ይገባል። አዲስ አበባን በሚመለከት የእኔ ወይም የእኛ የሚለው ክርክር መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብም ጥሩ ነው። የውዝግቡ መጨረሻ አባራሪውንና ተባራውን ለመወሰን ነው ወይ ብሎ ራስን መጠየቅም ተገቢ ነው። የሸገርን ነገር ቅጥ ባጣ ሁኔታ የሚያራግቡት ግለሰቦችና ቡድኖች ችግር እዚህ ላይ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። በጥላቻ ዘመቻ ብቻ አሸናፊ ሆኖ መታየት።
ኦዴፓ እና አዴፓ ለውጡን ተከትሎ ለቄሮዎችና ለፋኖዎች በአመፁ ወቅት ስላሳዩት ጠንካራና ደካማ ጎን፣ ሕጋዊና ሕገ ወጥ ተግባር ወዘተ…. እየነገሩ ቡድኖቹ አገርንና ወገንን ሊጎዱ ከሚችሉ አካሔዶቻቻው እንዲታቀቡ ከማድረግ ይልቅ፥ ቡድኖቹ ከሕግና ከሕዝብ በላይ የሆነ መብት ያላቸው እንዲመሥላቸው የሚያደርግ አያያዝ ታይቶባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ቄሮና ፋኖ በአንድ በኩል የለውጥ ሞተሮች በሌላ በከሉል የጥፋት ኀይሎች አድርገው ራሳቸውን የሚያዩና በፈለጋቸው ጊዜ ያሻቸውን ነገር የማድረግ መብት ያላቸው ኀይሎች ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። ከቄሮዎችና ከፋኖዎች ብዙዎችም ስለ ራሳቸው ይህን መሠል ግምት አሳድረዋል።
በዚህ ስህተት ለመጠቀም የሚፈልጉ ኀይሎች ሁሉ ኹለቱን የወጣት ቡድኖች ለመጠቀም እየሠሩ መሆኑም ግልጽ ነው። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ፋኖና ቄሮ እንደ ሌላ መንግሥት እና እንደ ልዩ ኀይል ተደርገው በመቆጠራቸውና መረን የለቀቀ አካኼድ ይፈቀዳል የሚል መንፈስ ስለተንሰራፋ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሄጎ፣ በከንባታ ዞባሃ፣ በጉራጌ ዘልማ፣ በሲዳማ ኤጀቶ፣ ወዘተ. የተባሉ የወጣት ቡድኖች ተቋቁመው ለያዥ ለገናዥ አስቸጋሪ የሆነ ነገር በየክልሉ እየተከሰተ ነው። ይህ ጉዳይ ሳይቃጠል በቅጠል ካልተባለ በስተቀር ቡድኖቹ ራሳቸውም ሆኑ ቡድኖቹን በግልጽም ይሁን በስውር መገልገያ የሚያደርጉ የውስጥም ሆኑ የውጭ ኀይሎች በአገርና በወገን፣ የየሳራቸውን ሕዝብ ጨምሮ ችግር ላይ የሚጥል የለየለት አናርኪ ሊፈጠር ይችላል። የየቡድኖቹ አደገኛ ባሕሪ እየሆነ የመጣው ነገር ሁሉም ጠላታችን ነው ብለው አንድን ሕዝብ በጅምላ የመፈረጅ ዝንባሌ የሚታይባቸው ሲሆን አልፎ አልፎ ሲወስዱት የሚታየው አካሔዳቸው በዚሁ ከቀጠለ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነሳ የሚያስብል ግጭት መቀስቀስ እንደሚችሉ ነው።
ወደ አማራ እና ኦሮሞ ጉዳይ ስንመለስ፥ የወቅቱን አነጋጋሪ ጉዳዮች በሚያራግቡ በኹለቱም ሕዝቦች ሥም በሚንቀሳቀሱ ወገኖች ልብ ውስጥ የተደበቀው ገፊው ሰበብ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመርሽ ቢሆንም መዳረሻው ተመሳሳይ ነው። ኢትዮጵያን ፈርሳ ማየት። የማያግባባውና መፍትሔ አልባው የመጨረሻ ቅዠት ‘ፊንፊኔን’ የያዘች የኦሮሚያ ሪፐብሊክን ወይም ‘በረራን’ የያዘች የብሔረ አማራ አገር መመሥረት መሆኑ ሊረሳ አይገባውም። ግቡ ይህ ከሆነ ደግሞ አዳራሽ ውስጥ እጆቻቸውን ሰቅለው በሚንጡ አለቆችና እያፏጩና እየጮሁ በሚያጨበጭቡላቸው ተከታዮቻቻው ወይም ዱላና የስለት መሣሪያ ይዘው ጎዳናወች ላይ በሚፈነጩ ተከታዮቻቻው ቲያትር ብቻ የሚሳካ ጉዳይ አይደለም።
ግዛቸው አበበ በሙያቸው መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011