ጉዞ ወደ ዴሞክራሲ

0
587

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመጡ ወዲህ ያለው አንድ ዓመት ለብዙ ዓመታት የሚበቃ ታሪክ ይዟል። በዴሞክራሲ ዓይን ብቻ ያየነው እንደሆነ የፖለቲካ እና ሲቪክ ምኅዳሩ ዴሞክራሲን ለመቀበል በሚያስችል መንገድ በር ተከፍቷል። ለምሳሌ፦

፩) በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ሥሟ ጠልሽቶ የነበረችው ኢትዮጵያ ሦስት አገዛዞችን ያየው እና ዜጎች በፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነታቸው ይታሰሩበት እና የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ይደርስባቸው የነበረው ‘ማዕከላዊ’ ተዘግቷል፤ አሁን ሙዚየም ይደረጋል የተባለ ቢሆንም በእርግጥ ለዚህ ምንም የተጀመረ ሥራ የለም።

፪) ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ከመታፈኑ የተነሳ ዜጎች ሳይገላመጡ ፖለቲካ የማይናገሩባት አገር እየሆነች የነበረችው ኢትዮጵያ አገር ውስጥ እንዳይነበቡ ታግደው የነበሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረገጾች ተከፍተዋል። ‘ጃም’ ይደረጉ የነበሩ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ከፍተዋል። አዳዲስ ጋዜጣዎች እና መጽሔቶች ሕትመት እና ስርጭት ጀምረዋል። የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች በፊት ይፈሯቸው የነበሩ ርዕሰ ጉዳዮችን በእንግዶች አማካይነት ማነሳሳት ጀምረዋል።

፫) የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም ‘ይቅርታ’ ተደርጎላቸው ተፈትተዋል፤ ብዙዎቹ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

፬) አፋኝ ይባል የነበረው የበጎ አድራጎትና ሲቪል ማኅበራት አዋጅ ተከልሶ ፀድቋል። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁም እንዲሁ ረቂቅ ማሻሻያ ቀርቦለታል። ሌሎችም አፋኝ ናቸው እየተባሉ ሲወቀሱ የነበሩ የምርጫ እና የሚዲያ ሕግጋት በክለሳና ሕዝባዊ ውይይት እንዲሁም በምክር ቤት ደጃፍ ለመፅደቅ ተራቸውን እየጠበቁ ነው።

እነዚህ ለዴሞክራሲ በጣም አስፈላጊ እና ምናልባትም የለውጡ ትልቅ ስኬቶች ቢሆኑም፣ የሕዝብ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉትን እንደ ፀረ-ሙስና፣ እምባ ጠባቂ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ አካላት እና ሌሎችንም ተቋማዊ ነጻነትን እና ገለልተኝነትን በማላበስ መልሶ ማዋቀር ብዙ የተወራለት በተግባር ግን ብዙ ያልተሔደበት ጉዳይ ነው። የመንግሥት ተቋማት ነጻነት እና ገለልተኝነት እርስ በርሳቸው እንዲጠባበቁ እና ሚዛን እንዲፈጥሩ ስለሚያደርግ የዴሞክራሲ ምሰሦ ነው።

ከዚህም ባለፈ ሰብኣዊ እና ፖለቲካዊ ነጻነቶችን ማክበር ፖለቲካዊ ወንጀሎችን ከመታገስ ጋር በመደበላለቁ ምክንያት የሕግ የበላይነት ተጓድሎ ታይቷል። ይህም ለደቦ ፍርድ እና ለስርዓት አልበኝነት በር የከፈተ ይመስላል። ዴሞክራሲ የተረጋጋ ስርዓት መገንባት የሚችለው የሕግ የበላይነት ከሰፈነ ብቻ በመሆኑ እነዚህን በማሟላት የተጀመረውን የዴሞክራሲ ጉዞ ከግብ ማድረስ ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here