የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 344 ሚሊዮን ብር ከሰረ

0
1041

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2011 በጀት ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ 344 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደገጠመው ታወቀ። ከብድር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ድክመት እንዳለበት በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፤ በበጀት ዓመቱ መስከረም ወር ላይ ያስመዘገበው የኪሳራ መጠን ከማይመለስና አጠራጣሪ ብድር ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የልማት ባንክ የሰጣቸው ብድሮች ሙሉ በሙሉ የተበላሹ ናቸው ማለት አይቻልም ሲሉ ይጀምራሉ። ከተወሰደው ብድር በአግባቡ ሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም የተበላሸው ብድር መጠን ግን ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበጀት ዓመቱ የካቲት ወር መጨረሻ 2011 ድረስ 6 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ማበደሩ የተገለፀ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ53 ነጥብ 4 በመቶኛ ብልጫ አለው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የባንኩ የብድር ክምችት 46 ነጥብ 17 ቢሊዮን መድረሱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ33 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ በ2011 በጀት ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ 3 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብድር መሰብሰቡ ተጠቃሽ ሲሆን ይህም በ12 ነጥብ 45 በመቶ ከአምናው ጋር ብልጫ አለው።

የባንኩ የየካቲት ወር መጨረሻ መረጃ እንደሚያመላክተው ጠቅላላ ሀብቱ 84 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሲሆን፤ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ደግሞ ካፒታል አለው። ስለ ልማት ባንክ ዝርዝር መረጃን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ይናገር ደሴ የልማት ባንክ ሁኔታ አሳሳቢ ነው፣ እስካሁን በሔደበት ሁኔታ አያስቀጥለውም ይላሉ። እስካሁን የሰጠውን ብድር በመሰብሰብ ረገድም አሁን ያለበት አቋም ደካማ ስለሆነ ይህንም ተሳቢ አድርገን ከብሔራዊ ባንክና ከልማት ባንክ በተወጣጣ ቡድን ማሻሻያ እየተሠራ እንደሆነ ገልፀዋል።

ባንኩ በኢትዮጵያ በተመረጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የገንዘብ ድጋፍ በብድር መልክ እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ በማምረት እና በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች በስፋት በማበደር ይታወቃል። በዚህም መሰረት እስካሁን ድረስ ባንኩ በእርሻ ዘርፍ ለተሰማሩ 480 ፕሮጀክቶች ብድር መስጠቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዘዳንት ኃይለእየሱስ በቀለ ተናግረዋል።

ፕሬዘዳንቱ አያይዘው እንዳስታወቁት፤ ባንኩ በ534 ብድር በወሰዱ ፕሮጀክቶች ላይ ባደረገው ጥናት መሰረት፤ 172 የሚሆኑት ምርት ሲመረትባቸው እንደነበር የታወቀ ሲሆን፣ 286 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል መሬት ያለሙ መሆናቸው ታውቋል ። ከእነዚህ ውስጥ ግን 76 የሚሆኑ ብድር የተወሰደባቸው ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ገንዘቡን ሥራ ላይ ሳያውሉ ባለሀብቶች መሰወራቸውን የባንኩ አጥኚ ቡድን አረጋግጧል።

ኃይለእየሱስ ጨምረው እንደገለፁት ብድር ከመሰጠቱ በፊት ባንኩ የአዋጭነት ጥናትን በጥልቀት ማጥናት የነበረበት መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ላይ በባንኩ ጥናት መሰረት ዝናብን መሰረት ያደረጉ ትላልቅ የእርሻ ልማቶች አዋጭ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። አያይዘውም ባንኩ ከዚህ በኋላ በዝናብ ለሚለማ እርሻ ምንም ዓይነት ብድር እንደማይሰጥ አስረግጠዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here