ከመልሶ ማቋቋም በኋላ ነዋሪዎቹን የወሰደው የትግራይ ክልል ብቻ ነው ተባለ

0
309

• የቀሩት ስምንት ክልሎች እስካሁን ምላሽ አልሰጡም

በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በጎዳና የሚኖሩ ዜጎችን በማንሳትና ለመልሶ ማቋቋም ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ክልሎች እንዲወስዱ ጥያቄ ቀርቦላቸው ጥያቄውን ተቀብሎ 26 የክልሉን ተወላጆች የወሰደው የትግራይ ክልል ብቻ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሻው አበራ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

አስተዳደሩ አብዛኞቹን ተቋቋሚዎች ወደ ክልል ለመመለስ ጥያቄ ቢያቀርብም ክልሎች ለመቀበል ባለመፍቀዳቸው ውዝግብ ውስጥ እየገቡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት እትሟ ማስነበቧ ይታወሳል።

ከወር በፊት ከአዲስ አበባ ጎዳና አዳሪዎችን ማንሳት የተጀመረው በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስተባባሪነትም ጭምር ተነሽዎቹ እስከ 45 ቀናት በማዕከል አገግመው ወደ የተወለዱበት ክልል እንዲሔዱ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር የነገሩን እንደሻው፣ በአንዳንድ ክልሎች የተፈናቃዮች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ከእኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ላለመስጠት ማነቆ ሆኖባቸዋል ብለዋል።

በዚህም 50 ሺሕ ጎዳና አዳሪዎችን ለማንሳት ያቀደው ከተማ አስተዳደሩ፥ በመጀመሪያ ዙር እስከ አምስት ሺሕ ለማንሳት እቅድም ይዞ ነበር። ሥራው በተጀመረ በቀናት ውስጥ ይነሳሉ ተብሎ የታቀደው 2 ሺሕ የጎዳና አዳሪዎች ቢሆንም ቁጥሩ ወደ 3 ሺሕ አሻቅቧል። ይህም ሆኖ ተነሽቹን በማዕከላት ይዞ የሚገኘው አስተዳደሩ ወደ ክልሎች መመለስ ያለባቸውን ሰዎች ለመላክ ለክልሎች በደብዳቤ ቢጠይቅም አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል።

ከነዚህ ሦስት ሺሕ ተቋቋሚዎች ውስጥ በዕድሜ መግፋት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት የማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና ሕጻናት ወደ ክልሎች እንደማይላኩ ለአዲስ ማለዳ ያሳወቁት እንደሻው፣ በአረጋውያንና ሴቶችና ሕጻናት ዙሪያ ከሚሠሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ተነጋግረው አንዲወስዷቸው እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የመሥራት አቅም ኖሯቸውና ሥልጠና ወስደው ለሥራ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶችና ተመራቂ ተማሪዎች የሆኑት ወጣቶችን ፍላጎት ጠይቀን ወደ ክልላቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ኦሮሚያ ክልል 277፣ አማራ ክልል 269፣ ደቡብ ክልል 384፣ ትግራይ ክልል 26፣ ድሬዳዋ 2፣ ሐረሪ 3፣ አዲስ አበባ 25፣ ቤኒሻንጉል 3፣ ድሬዳዋ 2፣ አፋር 1፣ ሶማሌ 1 ቢኖሩም የእነዚህን ወጣቶች ፍላጎት ተቀብሎ ጥሪ ያቀረበው ክልል የትግራይ ክልል ብቻ መሆኑን እንደሻው ለአዲስ ማለደ ተናግረዋል፡፡

አዲስ ማለዳ በባለፈው ሳምንት እትሟ የአማራ ክልል፣ የሚነሱ ዜጎች ብዛት፣ የሚሔዱበት አካባቢ፣ መሰማራት የሚፈልጉበት ሥራ እና መሰል ጉዳዮች ሳይጣሩ ሰዎችን አፍሶ ወደ ክልሎች መላክ የመንግሥትን ሀብት ከማባከን ያለፈ ውጤት የለውም በማለት እንደማይቀበለው ማሳወቁን መግለጿ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here