3497 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ቅሬታ አስገቡ

0
595

3497 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ከቦታ አላግባብ መፈናቀል፣ የደሞዝ ጭማሪ፣ ዕድገት የሥራ ድርሻና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ካለማግኘት ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች እንዳቀረቡ የድርጅቱ የሠራተኞች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ ገለፀ።

ከነዚህም መካከል 2722 የሚሆኑት የድርጅቱ ሠራተኞች ዕድገት ልናገኝ ይገባል በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ 700 የሚሆኑት ምላሽ ቢያገኙም ቀሪዎቹ ክፍት ቦታ ባለመገኘቱ ጥያቄያቸው እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ማኅበሩ ገልጿል።

ባለፉት ወራት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የንግድ ባንክ ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪን ጨምሮ የተለያዩ ቅሬታዎችን ማሰማታቸውንና የሥራ አድማ እንደሚያደርጉ መናገራቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ፤ ባንኩ አጠቃላይ መዋቅሩን ለመፈተሸ ወስኖ የነበረ ሲሆን በዋናነት የተነሳው ጥያቄ የደሞዝ ጭማሪ ቢሆንም እስከ አሁን ተግባራዊ አልተደረገም።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ቅሬታ ያቀረቡ ሠራተኞች እንደገለፁት ለባንኩ አስተዳደር የተነሱ ጥያቄዎች እስከ አሁን ምላሽ አልተሠጠበትም። በዚህም የተነሳ ሠራተኛው ከአቅም በታች እንዲሰራና የሥራ ሞራል እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ፊርማ ቢሰበሰብም ፊርማችን የት እንደደረሰ አናውቅም ያሉት ሠራተኞቹ የሚገባንን እድገት ለማግኘት አልቻልንም ብለዋል።

የባንኩ ሠራተኞች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሃይማኖት ለማ ደሞዝና ከድርጅቱ መዋቅር ጋር በተያያዘ ያሉ ቅሬታዎች ለመፍታት ኮሚቴ ተዋቅሮ ከኹለት ወር ጊዜ በላይ ወስዶ እየሠራ ይገኛል።

ከመዋቅሩ ጋር ተያይዞ የፍትሐዊነት ጥያቄ ነበር ያሉት ሃይማኖት የአመለካከት ችግር፣ የመስፈርት ችግር፣ ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖርና ጣልቃ ገብነት ነበር ብለዋል።

ለዚህም መዋቅሩ ሲሠራ ሁሉም በየራሱ ዞን የሠራ ሲሆን በአንድ ዞን ላይ የሥራ ልምድ ኖሯቸው ቢቀጠሩ ይህ ሌላው ዞን ላይሠራ ይችላል ለዚህም ቅሬታዎች እንዲበራከቱ ሆኗል ብለዋል።

በግልና በቡድን ሆነው ቅሬታ ለሚያቀርቡ ምላሽ እየሠጠን ቢሆንም ይህ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ሃይማኖት መሔድ እስካለብን ጫፍ ድረስ ሔደን ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተናጋግረናል ብለዋል። ከሠራተኞች ጋር በመነጋገር የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታም አንፃር ጊዜ እንስጥ በሚለው ስምምነት ላይ ብንደርስም ከበቂ በላይ ጊዜ ሰጥተናል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ አክለዋል።

አሁን ላይ ለቅሬታዎቹ ምላሽ ለመስጠት ከተለያዩ ቅርንጫፎች አምስት ሠራተኞችን በመወከል የተዋቀረውና 99 አባላት ያሉት የጋራ ድምፅ የሆነው የማኅበሩ ምክር ቤት ተቋቁሞ ሚያዝያ ላይ ስብሰባ እንደሚያካሒድና የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እየሠሩ እንደሆነ ሃይማኖት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ማኅበር ከተመሰረተ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን 30 ሺሕ አባላት ያሉት ማኅበሩ ቢሆንም የሠራተኞችን ቅሬታ መፍታት አልቻለም።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት በልሁ ታከለ በሰጡት ምላሽ ̋ስህተትን በስህተት ማረም ስለማንፈልግ ጉዳዩ ሒደት ላይ በመሆኑ ባላለቀ ነገር ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም ̋ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከኹለት ዓመት በፊት አዲስ መዋቅር ለማሠራት የወጣውን የንግድ ባንክ ዓለም ዐቀፍ ጨረታ ያሸነፈው ʻፍራንክፈርት ስኩል ኦፍ ፋይናንስ ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትʼ ጥናቱን አጠናቆ መዋቅሩን ለባንኩ ማስረከቡን ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here