‘ባለአደራ’ ኮሚቴው ከፖሊስ ጋር ሳይጋባባ ቀረ

0
633
  • በውይይቱ ወቅት ከፌደራል፣ ከአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ ፖሊስ የተውጣጡ ነበሩበት

እሁድ፣ መጋቢት 15/2011 ሊደረግ ታስቦ ከነበረው ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የባለአደራ ኮሚቴው ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ያደረገው ውይይት በአለመግባባት ተቋጭቷል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ስንታየሁ ቸኮል ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ፌደራል ፖሊስ ስለስብሰባው አጀንዳ አስረዱኝ ባለው መሰረት ለማስረዳት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ቢሮ መገኘታቸውን ገልፀው፤ ከፌደራል ፖሊስ ወገን ግን በከተማው ውስጥ የደኅንነት ሥጋት ስላለ ስብሰባ ማድረግ አትችሉም ብሎናል ሲሉ አስታውቀዋል።

እኛ ለማንም እና ለየትኛውም አካባቢ የኹከት መንስኤ መሆን ስለማንፈልግ በከተማው ላይ የደኅንነት ሥጋት አለ የሚባል ከሆነ ፌደራል ፖሊስ በሚዲያ ለሕዝቡ ካሳወቀ እኛም ስብሰባውን ወደ ሌላ ጊዜ ለማዛወር እንደምንችል ተናግረናል ሲሉ ስንታየሁ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከፌደራል ፖሊስ በኩል በመገናኛ ብዙኀን ለሕዝቡ ማሳወቅ እንደማይችልና ለኮሚቴውም የአዲስ አበባ ጉዳይ መነሳት የሌለበት ጉዳይ እንደሆነ በአፅንዖት ተናግሮናል ብለዋል ሰብሳቢው። በውይይቱ ወቅት ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከኦሮሚያ ፖሊስ የተውጣጡ የሕግ አካላት መካተታቸውንና የሁሉም አቋም ተመሳሳይ እንደነበር ስንታየሁ ቸኮል ተናግረዋል።

ከፌደራል ፖሊስ የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር ባለመቀበል አቋሙን እንደያዘ ከውይይቱ የወጣው የባለአደራው ኮሚቴ በቀጣዩ ቀን፣ መጋቢት 14 የጠራውን ስብሰባ እንደሚያካሒድ መርሃ ግብር ይዞለት ነበር። ይሁን እንጂ በአለቀ ሰዓት ኮሚቴው በደረሰው ረብሻ ይነሳል የሚል መረጃ ስብሰባውን ለማራዘም መገደዱን የአዲስ ማለዳ መረጃ ያመላክታል።

ስለስብሰባው መራዘም ስንታየሁ ቸኮል ሲገልፁ፤ ስብሰባው ቃሊቲ በሚገኘው በመድኅን ዲኮር አዳራሽ ሊካሔድ ነበር፤ ነገር ግን ቃሊቲ የመንገድ ትራንስፖርት ማሰልጠኛ ተቋም አካባቢ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ስብሰባውን ለማደናቀፍና ሰላማዊ መልኩን ለመቀየር መሰባሰባቸውን የሚገልፅ መረጃ ለኮሚቴው በመድረሱ ስብሰባው ሊራዘም እንደቻለ ተናግረዋል።

ስንታየሁ አያይዘው እንደተናገሩት ከመጀመሪያው በባልደራስ ከተደረገው ስብሰባ በኋላ የተለያዩ ተግዳሮቶች ኮሚቴው እያጋጠመው ነው። በግልፅ ጦርነት ውስጥ እንገባለን እየተባልን በአደባባይ ማስፈራራት እየደረሰብን ነው ይላሉ ሰብሳቢው ስንታየሁ ቸኮል። ሕግን ባከበረና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሐሳባችን እየገለፅን ነው ያለነው፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ባልታጠቀ ቡድን ላይ ጦርነትን እየጠቀሱ ማስፈራራት የማይገባ ነው ሲሉ ተችተዋል።

የአዲስ አበባ ባላደራ ኮሚቴ የአዲስ አበባን ባለቤትነት ጥያቄ መሰረት አድርጎ የተመሰረተ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት መብት ያለው የከተማዋ ነዋሪ በሙሉ ነው የሚል አጀንዳን ያነገበ ነው። ይህ ባለአደራ ኮሚቴ እሁድ፣ መጋቢት 1/2011 በአዲስ አበባ ባልደራስ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በይፋ መመስረቱ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here