በሥራ ላይ ሴትነቴ ትዝ ብሎኝ አያውቅም

0
890

ሒሩት ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ ይዘዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጀርመን አገር ከሚገኘው ኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ ሠርተዋል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። የመሪነት ክሕሎታቸውን በየደረጃው ማስመስከር የቻሉት ፕሮፌሰሯ የዩንቨርሲቲው ምክትል ፕሬዘዳንት እስከመሆን የደረሱ ብቸኛዋ ሴት ናቸው። በዚህም የሥራ ድርሻ ከአምስት ዓመት በላይ አንጋፋውን የትምህርት ተቋም አገልግለዋል።

የመሪነት ብቃታቸውን በየጊዜው እያስመሰከሩ የመጡት ምሁሯ የፌደራል መንግሥቱን የሥራ ኃላፊዎች ቀልብ ይበልጥ መሳብ የጀመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አስተዳደር ጊዜ ነበር። ወደ ግብጽ የሚሄደውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ሲዋቀር የቡድኑ አባል ሆነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመረጡ። ብዙም ሳይቆይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን በድጋሚ በምሁራን ሲያዋቅሩ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ተደርገው ተሾሙ።
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ከተቆናጠጡ ጥቂት ሳምንታት በኋላ ካቢኔው እንደገና ሲዋቀር ሒሩት ወልደማሪያም የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እንደገና ተሾሙ። በዚህ የኃላፊነት ወንበር እምብዛም ሳይቆዩ አዲስ ወደተቋቋመው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርነት ተዛወሩ።

አኚህ ታታሪ ምሁር የያዙት የፌደራል መንግሥት ሹመት ከሚወዱት የመምህርነትና ተመራማሪነት ስራ አላገዳቸውም። አሁንም ድረስ የሦስተኛ ዲግሪ (ዶክትሬት) ተማሪዎችን በማማከርና በምርምር ሥራቸው እንደገፉበት ነው። ይህም ትጋታቸው ከኹለት ወር በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ተመዝኖ ከተባባሪ ፕሮፌሰርነት ወደሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል። ይህ በዩንቨርሲቲው ታሪክ ሦስተኛዋ ሴት ፕሮፌሰር፤ እንደዚሁም የመጀመሪያዋ የማኅበራዊ ሳይንስ ፕሮፌሰር ያደርጋቸዋል። የማርች ኤይት የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የአዲስ ማለዳዋ ኪያ አሊ ከፕሮፌሰሯ ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

አዲስ ማለዳ፦ ስለ አስተዳደግዎ ትንሽ ቢነግሩን!
ሒሩት ወልደማርያም (ፕሮፌሰር)፡- ለቤተሰቤ ከአራት ልጆች የመጀመሪያዋ ነኝ። አባቴ በሕይወት እያለ እንድናነብና በትምህርታችን እንድንበረታ የሚያደርገን ነበር። በየቀኑ ጋዜጣ ይገዛል፤ የተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎችን ያዳምጣል። እኛንም በሱ ፈለግ ነው ያሳደገን። እናቴ የቤተክርስቲያን ሰው ናት፤ እንድንፀልይ፣ እንድንፆም አድርጋ ነው ያሳደገችን። አባቴ የደቡብ ሰው ነው። በመምህርነት ጎጃም ደብረማርቆስ ተመድቦ ሲሠራ ከእናቴ ጋር ተዋውቆ ነው የተጋቡት። እኔም እዛው ተወለድኩ። ከዛም የ4 ዓመት ልጅ እያለሁ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ የአባቴንም ሆነ የእናቴ ቤተሰቦችን ባሕል ስላላደኩበት እምብዛም አላስታውስም። አዲስ አበባ ከመጣን በኋላ ጉስቋም (እንጦጦ መውጫ) አካባቢ መኖር ጀመርን። አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን በጣይቱ ብጡል ተማርኩ፤ ከዛ አባቴ የሚያስተምርበት በቀድሞ ሥሙ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ተማርኩ። ከዛ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያና የኹለተኛ ዲግሪዬን በስነ ልሳን ትምህርት ተመረቅኩ። ከዚያም እዛው ዩንቨርሲቲ መምህር፣ ተመራማሪና በኋላም የዩኒቨርሲቲ አመራር ሆንኩ። ከቤተሰቤ ቀጥሎ ማንነቴ የተገነባው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው።

ከኹለት ዓመት በፊት ሚንስትር ሆኜ ስሾም ነው ከዩንቨርሲቲው አመራር የወጣሁት። ባጠቃላይ አስተዳደጌ ከቁስቋም እስከ ስድስት ኪሎ ባለው አካባቢ ነው።
የመምህር ልጅ መሆንዎ በትምህርትዎ ውጤታማ እንዲሆኑ የፈጠረው ተፅዕኖ አለ?

አለ ብዬ ነው የማስበው። አባቴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ነበረው። ቤተሰባችንና አካባቢያችን ነው የእኛን ሕልም፣ የእኛን ማንነት የሚቀርፀው። አባታችን ሁልጊዜ ዕውቀት የመሻት፣ ሁሌም የማንበብና ወቅታዊ ጉዳዮችን የመከታተል ፍቅር ነበረው። ይህ እኛንም ወደዛ የመሳብ ተጽኖ ነበረው። ለምሳሌ ‘ብሪቲሽ ካውንስል’ አባል አድርጎን እዛ ሔደን እንድናነብ አድርጓል። ስለዚህ መሠረታችን አባታችን ነው። አንዴ መሠረት ከያዝሽ ደግሞ በዛው ትሔጃለሽ። አባቴ ትንሿንም ስኬት ያደንቃል፤ ያበረታታል። ሁልጊዜ ስለኔ ያወራል ስለ እህቴም እንደዛው። ያው የመጀመሪያ ልጅም ስለነበርኩ ይመስለኛል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጎበዝ ናት፤ ጠንካራ ናት ሲል በጎ ተፅዕኖ ይፈጥርብሻል። አንዳንዴም አፍራለሁ። ይህ አርዓያ ከመሆን በተጨማሪ ለራሴ ትልቅ ቦታ እንድሰጥ አድርጐኛል።

የአንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዎ ምን ይመስላል? በተለይ ከሴትነት ተግዳሮቶች ጋር በተያያዘ።
እኔ እውነት ለመናገር አንደኛም ሆነ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትስማር ሴት መሆኔም ትዝ ብሎኝ የሚያውቅ አይመስለኝም። ምንም የማስታውሰው ተፅዕኖ የለም። ትምህርት ቤት እያለሁ ከሴትነት ጋር ተያይዞ የገጠመኝ ይህ ነው የምለው እንቅፋት የለም። ብዙ ሴት ተማሪዎች በትምህርታቸው ሳይገፉ እዛው የቀሩ አንድ ክፍል የነበርን ልጆች እንዳሉ አስታውሳለሁ። በተለያየ መንገድ ትምህርታቸውን ለመከታተል የማያስችል ነገር የሚገጥማቸው ነበሩ። በልጅነታቸው አርግዘው የልጅ እናት የሆኑ፣ ወንዶች የሚደበድቧቸውና ሌሎችም ችግሮች የደረሰባቸው ሴቶች አውቃለሁ። ብዙ ጊዜ ለምማርበት ክፍል ከሌሎች ተማሪዎች አንፃር በእድሜዬ በጣም ትንሽ ስለነበርኩኝ እንደዚህ ዓይነት ነገር አልገጠመኝም። ይገርምሻል በአራት ዓመቴ አንደኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። አባቴ መምህር ስለነበር በአንዱ ክረምት ቤት ውስጥ በተሰቀለው ፊደል ሀሁ አስተማረኝና አንደኛ ክፍል ገባሁ። እናም በየደረጃከክፍል ወደሌላ ክፍል ሳልፍ ከጓደኞቼ በዕድሜ የማንሰው እኔ ነበርኩ። ለዛ ይሆናል ምንም ያልገጠመኝ።

እርስዎ ተማሪ በነበሩበት ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ከፆታ ጋር የተገናኙ ችግሮች የትኞቹ ናቸው?
ዩኒቨርሲቲ ላይ ብዙ ሴቶች ዝግጅቱ ሳይኖራቸው ነው የሚመጡት፤ ከገጠር የሚመጡ ተማሪዎች በተለይ ሁሉም ነገር እንግዳ ይሆንባቸዋል። ይህ ትኩረታቸውን ይወስደዋል። ወይም ደግሞ እንዴት ማጥናት እንዳለባቸው ሳያውቁ ይመጡና ትምህርቱን መከታተል ሲያቅታቸው ይወድቃሉ። ሌላው ደግሞ ዝግጁ ሳይሆኑ የወንድ ጓደኛ የሚይዙም ነበሩ። ሴቶች ብሎ ማጠቃለል ተገቢ አይደለም፤ ግን ሁሉም ላይ ባይሆንም ትንኮሳው እንዳለ ነው። በመምህርም ሆነ በተማሪዎች ትንኮሳ ሊደረግባቸው ይችላል። ያንን እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው የሚያስተምራቸው ስለሌለ ችግር ሊፈጠርባቸው ይችላል። በተለይ ያላደገ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የወንዱ የበላይነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ይህ ነገር በየደረጃው በግልጽ የሚታይ ነው። ትምህርት ቤት ብቻ አይደለም፤ በቤት ውስጥም ሆነ በሰፈር ውስጥ፣ በየትም ቦታ የሚገጥም ፈተና አለ። ዩኒቨርሲቲ ደሴት ወይንም የተለየ ዓለም አይደለም፤ የውጪው ዓለም ነፀብራቅ ነው። ዋናው ነገር ለሚገጥማቸው ተግዳሮት ዝግጁ መሆን ነው። ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው እዚህም አለ። ይህንን እንዴት መመከት እንዳለባቸው የሚያስተምራቸው፣ የሚመክራቸው ስለሌለ ችግር ሊፈጥርባቸው ይችላል። በትምህርታቸው ውጤታማ በመሆን በኩል፥ ዋናው ችግር ግን በትምህርት ውጤታማ የሚያደርጋቸውን በቂ ክኅሎት ይዞ አለመምጣት ነው። መማር የማጥናት፣ የማንበብና የመረዳት ችሎታ ይፈልጋል። ይህን የሚያደርጉበትን በቂ ልምድና ክኅሎት ይዘው ካልመጡ ትምህርታቸው ላይ እንከን ይፈጥራል። ይህ ሴት ላይ ሲሆን ያሳዝናል፤ ምክንያቱም ብዙ መሰናክል አልፋ ነው አንዲት ሴት እዚህ ደረጃ የምትደርሰው። ስለዚህ እዚህ ድረስ ደርሳ ብትወድቅ የተከፈለው ወሰዋዕትነት ሁሉ ብክነት ነው የሚሆነው። አንዳንዶቹ እንደውም መመለስ አፍረው ሌላ ሕይወት ውስጥ የሚገቡ አሉ።

ትምህርትዎን ካጠናቀቁ በኋላ ከመምህርነት እስከ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዘዳንትነት የቆዩበትን ጊዜ እንዴት ይገልጹታል? ምን ምን ፈተናዎች ገጠምዎት?ፈተናዎቹንስ እንዴት አለፏቸው?
የዶክትሬት ዲግሪዬን ጀርመን ነው የሠራሁት። ከጀርመን እንደመጣሁ የትምህርት ክፍሉ ውስጥ ሴት እኔ ብቻ ነበርኩ። እና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ እየተመረጠ ነበር የደረስኩት። አጋጣሚ እኔን መረጡኝ። እኔም ልምዱ ስላልነበረኝ ይህን ለመቀበል ትንሽ አንገራግሬ ነበር። ሌሎችም ልምድ ያላቸው መምህራኖቼ የነበሩ እዛው የትምህርት ክፍሉ ውስጥ ትችለዋለች የሚለው ላይ እምነት አልነበራቸውም። ብዙ ምቾት አልሰጣቸውም ነበር። ሌሎች ደግሞ በቅርብ የሚያውቁኝ ትችላለች ብለው ተመረጥኩ። ከተመረጥኩ በኋላ ልምዱ ስላልነበር በአንድ በኩል ስጋት፣ በሌላ መልኩ አትችልም ተብዬ ስለነበር እልህ ነበረብኝ። ስለዚህ መውደቅ ምርጫዬ አልነበረም። እና በጣም ነበር የምሠራው። የትምህርት ክፍሉ አዳዲስ የዶክትሬት ፕሮግራሞች አስከፈትኩ፤ ከውጪ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥሩ ትብብር እንዲኖር አደረግኩ። ዓለምዐቀፍ ኮንፈረንሶች መጥተው የማያውቁ፣ ወደኛ እንዲመጡና የትምህርት ክፍሉ እንዲያዘጋጅ አደረግኩ። እዚህ ጋር ለሌላውም ትምህርት የሚሆነው ነገር አንድ ትንሽም ቢሆን የተሰጠሽን ኃላፊነት በአግባቡ ከተወጣሽ ከፍ ወዳለ ኃላፊነት እንደምትታጪ እኔ በራሴ ነው ያየሁት።

በውል በማላስታውሰው አንድ ቀን ከዩንቨርሲቲው ኃላፊዎች ዘንድ ስልክ ተደወለልኝ፤ ያው ኮንፈረንስም ስናዘጋጅ የዩንቨርሲቲውን ኃላፊዎች እንጋብዛለን። አዳዲስ የትምህርት መርኃግብር ስናፀድቅም ይጋበዛሉ። በዛ ሁኔታ ውስጥ ነው ዕይታ ውስጥ ገባሁት። ከዚያ እዚህ ከፍ ባለ ቦታ ብታግዢን ተባልኩኝ። መጀመሪያ እንዲያውም የየትምህርት ክፍሉ ኃላፊ እንዳለሁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኃላፊነት ሥራ ደርበሽ ሥሪ ተባልኩ። ካስፈለገ የሚረዳሽ ሰው ይመደባል ብለው አበረታቱኝ። እዚህም ተመሳሳይ ስሜት ነበረኝ። ኃላፊነት በጣም ያስጨንቀኛል። ታምኖ ከተሰጠኝ በደንብ ሠርቼ ማሳየት አለብኝ የሚል ስሜት ነው ያለኝ። እናም ሆኖ የማያውቅ ነገር ነው የሠራሁት። በቅርበት የማቃቸውንና ተገቢ ሥራ የማይሠሩት ላይ ሁሉ እርምጃ እንዲወሰድ አደረኩ። ከዛ ‘associate vice president for academic affair’ ሆኜ ተሾምኩ፡፡ እዛም ኃላፊነት ላይ ሆኜ ጥሩ ነገር ሠራሁ። አንዴ በትጋት መሥራት ከተጀመረ ልማድ ይሆናል። ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ወርደው ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ ሲሾሙና የዩንቨርሲቲው አስተዳደር በአዲስ መልክ ሲዋቀር ደግሞ ‘vice president for institutional development’ በሚል ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኜ ተሾምኩ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ነው እዚህ የደረስኩት። የተሰጠሽን ኃላፊነት በአግባቡ ከተወጣሽ ለተሻለ ኃላፊነት ትታጫለሽ።

ሴቶች ወደ አመራርነት ሲመጡ የብቃት ጥያቄ ይነሳል። ወንዶች ሲሆኑ ግን ይህ ጥያቄ እምብዛም አይስተዋልም። ይህ ለምን ሆነ ብለው ያስባሉ?
ይኼ እኮ ግልጽ ነው። ማኅበረሰቡ የሴት መሪ አይቶ አያውቅም። አባታዊ ነው ስርዓቱ። አባታዊ ማለት ሁሌ ወንድ ነው የሚመራው። አደባባይ የሚውሉት ወንዶች ናቸው። ማኅበረሰቡ ለሴት የሰጠው የሥራ ክፍፍል ልጅ ማሳደግና ቤተሰብ ማስተዳደር ነው። ከዛ ወጣ ብለሽ ስትገኚ ጥያቄ ያስከትላል። ያው ካለው ልማዳዊ አስተሳሰብ የተነሳ ነው። ከዚህ እምነት ውጪ ስትገኚ ሳያዩሽ፣ ሳያውቁሽ፣ አቅምሽን ሳይመዝኑና ሳይለኩ ወዲያው አትችልም የሚል ጥያቄ ይነሳል። ይህ እኛ አገር ብቻ የሚታይ ችግር አይደለም። ዓለም ዐቀፋዊ ጉዳይ ነው። ነገር ግን እኛ አገር ያለው ባሕላዊ ማኅበረሰብ ስለሆነ የበለጠ ይፀናብናል። ስለዚህ ወደ አመራርነት ብዙ ሴቶች ሲመጡ፣ በተለይ አሁን እንደሆነው የሚኒስትርነት ቦታ ሃምሳ ሃምሳ ሲሆን፤ እንደዚሁም ከታችም ባለው እርከን ወደ አመራርነት የሚመጡ ሴቶች እየጨመረ ሲመጣ ኃላፊነቱን ትችለዋለች ወይ? ከዚህ በፊት ሠርታ ታውቃለች ወይ? ተሞክሮ አላት ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ይህ የሚሆነው ማኅበረሰቡ ሴት መሪ ለመቀበል ዝግጁ ስላልሆነ ነው። አትፈርጂበትም፤ ወደኋላ ስትሔጂ ብዙ ሴት መሪዎች ስለሌሉ ነው። ወንድ የሆነ እንደሆነ የሴቷን ያህል በጥርጣሬ የማታይበት በእኩል ሚዛን ስለማይመዘን ነው። ግን ዋናው ነገር ሠርቶ ማሳየት ነው። ካሳየሽ በኋላ በሥራሽ ያከብሩሻል። ውጤቱን ሲያዩ ይቀበሉሻል። ይህ ከታች ላሉትም ጥሩ ነው። ዋናው የእኛ ጥቅም እሱ ነው። ነገር ግን አሁን ሥልጣን ላይ ያለን ሴቶች ውጤታማ ካልሆንን ከታች ያሉትን ሴቶች ነገ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። ሒሩት ወደቀች አይደለም ፤ ሴት አልተሳካላትም ነው የሚባለው። ሁሉም የሴቶችናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገቡት። ይህ ስር የሰደደ ባሕል ነው። ብዙ የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። እናም ሴት ከሆነች መሆን ያለበት እኔም ከልምዴ ያየሁት እጥፍ መሥራት፤ እንደውም እንደምትችል ከበቂ በላይ ሠርታ ማሳየት አለባት። በርግጥ ይህ አድካሚ ነው። ወንድ ከሚሠራው ኹለት ወይንም ሦስት እጥፍ ሠርተሽ ማሳየትና ማስመስከር ፍትሐዊ አይደለም። ግን ምንም ምርጫ የለም። ደሞም ሴት ጠንካራ ናት። ኹለትም ሦስትም እጥፍ ትችላለች። ይህን ማድረግ የሚያስፈልገው የማኅበረሰባችንን አስተሳሰብ ለመቀየር ነው።

ዋናው ነገር በራስ መተማመንን ማሳደግ፤ ምን እንደምትሠሪ ማወቅ፤ እንዴት እንደምትሠሪና ከማን ጋር እንደምትሠሪ ማወቅ፤ ምን ዓይነት ኃብት በዙሪያሽ እንዳለ መገንዘብ፤ ምን ዓይነት ኃይል ማሰለፍ እንዳለብሽ ማወቅና ስልታዊ አካሄድ የመከተል ብልኃት ያስፈልጋል። ዓለም ጥሩ ነገር ይዘሽ ከመጣሽ ትቀበልሻለች። እንዲሁም ዕውቀት ተለዋዋጭ ስለሆነ ትላንት ተማርኩ ብሎ ቁጭ ማለት አያስፈልግም። አዲስ ዕውቀት በየጊዜው ስለሚመጣ በየጊዜው ራስን ማስተማርና ማብቃት ያስፈልጋል። ይህንን ራስን የማስተማር ነገርም በቀጣይነት የሚደረግ ከሆነ የማይቻል ነገር አለ ብዬ አላስብም። ምንም የማይቻል ነገር በዚህ ምድር ላይ የለም። ግን እንዴት እንደሚቻል ማወቅ ያስፈልጋል። ዋናው ምስጢር ጊዜሽን ብዙ ትርፍ በሚያስገኝ ነገር ላይ ማዋል ነው።

እርስዎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ ምን አደረጉ? አሁንስ ባሉበት የኃላፊነት ቦታ ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ምን ለመሥራት አስበዋል?
ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኜ ሁሌ ምልመላ በሚደረግ ጊዜ ሴቶች እንዲመጡ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ጥረት አድርግ ነበር። በተለይ አሁን ወደ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚንስትርነት ከመጣሁ በኋላ ብዙ ለውጥ የሚያመጡ ነገሮችን መሥራት ጀምሬአለሁ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ለእኛ ሪፖርት በሚያደርጉ 45ቱም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኘውን ቦርድ አሻሽለን አዋቅረነዋል። በዚህም መሠረት በሁሉም ቦርዶች ውስጥ ሃምሳ በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ አድርገናል። ይህን ያደረግነው ዝም ብለን በኮታ አይደለም። በነገራችን ላይ እኔ በኮታ አላምንም፤ ኮታ መጥፎ ነው። ዝም ብለሽ ለኮታ ብቻ ተብሎ ሴት ብታስገቢና በኋላ ሳትችል ብትቀር ነገሩ የከፋ ይሆናል። ጭራሽ ነገሩ ሴት ናት እንዲህ ያበላሸችው በሚል መጥፎ ምሳሌ ይሆናል። ብዙ ሴት የለም የሚባለው ነገር ደግሞ ውሸት ነው። ጉዳዩ እድል የመስጠት ነገር ነው፡፡ በየአመቱ ከከፍተኛ ትምህርት የሚመረቁ የወርቅ ተሸላሚ ተማሪዎች ብዙዎቹ ሴት ናቸው። ይህ በጣም የሚያበረታታ ነገር ነው። ስለዚህ ከየኢንዱስትሪው፣ ከየአካዳሚክ ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ ካሉት ብቁ ሴቶች አፈላልገን ውጤታማ የሆኑትን፣ ዕውቀት ክኅሎትና ጥሩ ዕይታ ያላቸውን ፈልገን በየዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሦስት ሴቶችን ለማካተት አስበናል።

ከአሁን በፊት እኔ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ነበርኩ። ሙፈርያት ካልም የሠመራ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ የነበረች ። ከዛ ውጪ ያሉት የዩንቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርዶች የሚመሩት ግን በወንድ ነው። አሁን ዐሥር ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሴቶች ናቸው የቦርድ ሰብሳቢዎቹ። ስለዚህ ሴቶች በአመራርነት እንዲሳተፉ አድርጌአለሁ። ኹለተኛው የዩኒቨርሲቲ አመራር መመልመያ መስፈርትን አሻሽያለሁ። አመራር ማለት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ማለት ነው። እያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ አንድ ፕሬዝዳንትና አራት ምክትል ፕሬዝዳንት አለው። ከአዳዲሶቹ ውስጥ ሦስት ምክትል ፕሬዝዳንት ያላቸው አሉ። በተሻሻለው መመሪያ መሠረት በእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ ቢያንስ ኹለት ጠንካራ ሴቶች በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ላይ እንዲሳተፉ ይላል። ኹለት ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት ማለት ነው። ሴቷ ፕሬዝዳንት ከሆነች ቢያንስ አንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ሴት መሆን አለባት ማለት ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ብቻ ሴት አመራር አምጥቶ፥ ኹለት አድርጉ ተብሎ ተመልሶባቸዋል። ይህ አንድም የፍትሐዊነት ጉዳይ ነው። ሴት ብቁ ከሆነች አመራር ላይ መምጣት መብቷ ነው። አመራር መሆን አለባት ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲ የወንድም የሴትም ተማሪዎች ማዕከል ነው። በተጨማሪም የሴት ዕይታና አቅም ጥቅም ላይ መዋል አለበት። የምንፈልገው ለውጥ እንዲመጣ የወንድ አቅም ብቻ በቂ አይደለም።

ሌላው ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት መምህራን ኅብረት አቋቁሜአለሁ። ሴቶች ወደኋላ የቀሩት ጠንካራ ኔትዎርክ ስለሌላቸው ነው። አሁን ግን በዚህ ማኅበር ምክንያት እርስ በእርስ ይረዳዳሉ። ለእኛም አቅማቸውን ለማጎልበት አንድ አደረጃጀት መኖሩ ይጠቅመናል።
ግን አሁንም የተዛነፈ ነገር አለ። በምርምርና በፕሬዝዳንትነት ደረጃ ብዙ ሴቶች የሉም። በመጀመሪያ ዲግሪ ላይ የሴቶች ቁጥር የተሻለ ነው። ነገር ግን ከፍ እያልን ወደ ማስተርስና ዶክትሬት ሲኬድ ቁጥራቸው እየመነመነ ይመጣል። በረዳት፣ ተባባሪና በሙሉ ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ ደግሞ የሴቶች ብዛት በጣም አናሳ ነው። ስለዚህ አሁን የጀመርነውን ኔትዎርክ አጠናክረን ወደፊት የሴቶችን አቅም ማጎልበቻ ማዕከል ማቋቋም አስበናል።

ለምን ከዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንትነትዎ ለቀቁ?
ምክትል ፕሬዝዳንት እያለሁ ባሕልና ቱሪዝም ለሚንስተርነት ስጠራ ነው የዩኒቨርስቲውን ምክትል ፕሬዝዳንትነት የለቀቅኩት። ከዛ ቀጥሎ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ በሚንስትርነት ሠርቻለሁ። አሁን ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ውስጥ ሚንስትር ሆኛለሁ። እውነቱን ለመናገር ከሆነ ‘ፌሎሺፕ’ አግኝቼም ነበር። ትልቅ ነጻ የትምህርት ዕድል ነው ያገኘሁት። እሱን አሸንፌ ወደ ጀርመን ልሔድ ስል ነው የሚንስትርነቱ ሹመት የመጣው። ከዛ ፌሎሺፑን በኹለት ዓመት አራዝሙልኝ ብዬ ጠየቅኩ። አሁንም ይኼኛው የሚንስትርነት ሹመት ሲመጣ ድጋሚ በአንድ ዓመት አራዝሙልኝ ብዬ ተራዘመልኝ። ይኼንን ሥራዬን ስጨርስ እሔዳለሁ።

አሁን ግማሽ ያህሉ የሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት ሴቶች ሆነዋል። ይህ ከታች ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ላሉት ሴቶች የሚሰጠው መልዕክት ምንድነው? በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሴቶችን ለማብቃት ምን እየተሠራ ነው?
በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ጥናት አላደረኩም። በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ያለው ነገር ግን ከላይ እንደተናገርኩት ትኩረት የሚፈልግ ነገር ነው። ከታች ሴቶች በአመራርነት እምብዛም የሉም። በሌላው ሴክተር ግን ብዙ መረጃው ስለሌለኝ ልናገር አልችልም። በአጠቃላይ ግን በትምህርቱ መስክ እንዳየሁት ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣቱ ነገር ገና ብዙ ስራ የሚፈልግ ይመስለኛል። ስለዚህ ብዙ ሥራ መሠራት፣ ማስተካከልና መለወጥ አለብን ብዬ አስባለሁ።
የኛ ወደ አመራርነት መምጣት የተምሣሌትነት ሚና አለው። ይህ ደግሞ የሚያመጣው በጎ ለውጥ አለ። ሰው ምሣሌ ይፈልጋል። ወጣት ሴቶች ስኬታማ የሆነች ሴት ሲያዩ እርስዋን እንደ ምሣሌ ወስደው እኔም ነገ እንደሷ መሆን እችላለሁ ብለው እንዲያስቡና እንዲሠሩ ያነሳሳቸዋል። የማታየውን ነገር አታምኚም፤ ሁሌ አንድ ቦታ ላይ ወንድ ብቻ ከሆነ በኃላፊነት የሚሾመው ‘ይህ የወንድ ቦታ ነው’ ብለው እንዲያስቡ ተጽኖ ያሳድርባቸዋ። ሴት ፕሬዝዳንት ፣ ሚንስትር መሆን ትችላለች የሚለው በተግባር ሲያዩ ወጣቶች ላይ ቀላል የማይባል በጎ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

የተለመደው አዙሪት የሆነ ቦታ መሰበር አለበት። ከላይ ያሉት ወንዶች ብቻ ከሆኑ ብዙ ነገሮችን በራሳቸው ዕይታ ብቻ ይቀርፃሉ። እግዚአብሔር አዳምን በመልኩ ፈጠረ እንደሚባለው ከላይ ያሉት አመራሮችም ነገሮችን በራሳቸው ዕይታ ብቻ ቃኝተው ይሰሯቸዋል። ሴት ግን ወደ አመራርነት ስትመጣ ይህን የተለመደው ነገር ተሰበረ ማለት ነው። ነገር ግን ምሣሌነቱ ውጤታማ የሚሆነው ከተሳካልሽ ነው። እዚህ ቁጭ ብለሽ ካልተሳካልሽ አሳፋሪ ነው የሚሆነው፤ ውጤታማ ከሆንሽ ለሌላው ፈር ቀዳጅ ትሆኛለሽ።

ሴቶች በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሥፍራ ላይ ሲሆኑ ውሳኔያቸውን የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዴት ነው የሚቀበሉት? ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሴት በመሆናቸው የሚደርስባቸው የተለየ ተግዳሮት ምን ይመስላል?
ብዙ ጊዜ ሴት መሆኔን አላስታውስም። ሴት ስለሆንኩ እንዲህ ይሉኛል የሚለውን ስሜት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍል ኃላፊ የነበርኩ ጊዜ አሽቀንጥሬ ጥዬዋለሁ። ድሮ ምናልባት አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ሴት ስለሆንኩ ላይሆን ይችላል። ወንድ ለወንድም አንዱ ለአንዱ ላይታዘዝ ይችላል። ዋናው ነገር ግን ሥራው በአግባቡ ካልተሠራ ለምን ብዬ እጠይቃለሁ፤ እንወያያለን። ከዛ ችግሩን እንፈታዋለን። እኔ ሴት ስለሆንኩ አይታዘዙኝም የሚል አመለካከት በፍፁም የለኝም። ሴት ስለሆንኩ አይታዘዙኝም፣ ሴት መሪ አይቀበልም የሚለው አስተሳሰብ በራሱ መጥፎ ነው፤ ይዞሽ ገደል ይገባል። አንዴ አስታውሳለሁ፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊ እያለሁ የሴሜስተሩ መጀመሪያ ላይ ኮርስ ይደለደላል፤ አስተማሪዎችም የተመደበላቸውን ኮርስ ያስተምራሉ። አንድ ጊዜ ግን ተማሪዎች መጥተው እኔ የመደብኩት መምህር ሳይሆን ሌላ ሰው እንደሚገባላቸው ነገሩኝ። እኔ የመደብኩት ዶክትራት ዲግሪ ያለው መምህር ነው። እየገባላቸው ያለው ደግሞ አዲስና ጀማሪ መምህር ነው። ይህንን ሳውቅ የቅጣት ደብዳቤ ጻፍኩበት።

ከዛ በፊት በየትምህርት ክፍሉ ውስጥ የቅጣት ደብዳቤ ፋይሉ ውስጥ ያለ መምህር አልነበረም። መምህሩ ጓደኛዬ ነው፤ እና ጉዳዩ መነጋሪያ ሆኖ ነበር። ኃላፊነቴን ለመወጣት እዛ ድረስ እሔዳለሁ። መጀመሪያ ላይ ነው መሥመር አሥምረሽ ራስሽን የምታስከብሪው። ከዛ በኋላ ሁሉም ነገር መሥመር ይዞ በትክክለኛው መንገድ መሔድ ይጀምራል። ሁሉም ሰው የሥራ ድርሻውን በትክክል ካልተወጣና በቂ ምክንያት ካላቀረበ ተገቢውን እርምጃ ትወስጃለሽ እንጂ ሴት ስለሆንኩኝ ብሎ ማሰብ አያስፈልግም። ይህ ሥራ ነው በፍላጎትና መልካም ፍቃድ የሚሠራ አይደለም። ኃላፊነት ነው፤ ተጠያቂነት አብሮ አለ። ሴት ስለሆንኩ ይንቁኛል፤ ሴት ስለሆንኩ አያከብሩኝም፤ ሴት ስለሆንኩ አይታዘዙኝም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ይህን ካልሽ ቀድመሸ ራስሽን ጣልሽው ማለት ነው። መሪ ለመሆን የወንድ ተክለ ቁመና አያስፈልግም። በጭንቅላት ነው የምትመሪው፣ ክኅሎት የሚዳብር ነገር ነው። ይህንን ስለማውቅ ሴትነቴ በሥራ ላይ ትዝ ብሎኝ አያውቅም። ጋዜጠኛ ሲጠይቀኝ ነው ሴት መሪ መሆኔን የማስታውሰው። ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ከትምህርት መሪነት ጀምሮ በየደረጃው በአመራርነት አገልግያለሁ። ያ ደግሞ ልምድ ይሰጥሻል። ስለዚህ ከተወሰነ ዓመት በኋላ የፆታውን ነገር ከምንም አትቆጥሪውም። ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ውስጥ ብቸኛዋ ሴት እኔ ነበርኩ። ግን የማስበው ለቦታው የሚመጥን ሐሳብ ይዤ መሔዴን ብቻ ነበር። የማፍረው ያን ካላደረኩ ነው እንጂ ሴት ስለሆንኩ አይደለም። ትልቁ ችግር ራስን አለማየትና አለማወቅ ነው። ስለዚህ ጥሩ መስታወት ይዞ ቀረብ አድርጎ ውስጥን በደንብ ማየት ነው፣ ጥንካሬን ማየት። መስታወቱ የማያሳይ ከሆነ ራስን በደንብ የሚያሳይ ሌላ መስታወት መቀየር ያስፈልጋል። ትልቁ ነገር በዙሪያሽ ላለ አፍራሽ ድምፅ ጆሮ አለመስጠት ነው። አንዳንዴ አፍራሽ ድምፆች ከራሳችንም ጭምር ይወጣል። ይህን አፍራሽ ድምፅ አለመስማት ነው።

በቤት ውስጥ ያለዎት የሥራ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ትንሽም ቢሆን ለቤተሰቦቼ ጥሩ ጊዜ እሰጣቸዋለሁ። ልጆቼን አደንቃቸዋለሁ፤ እከታተላቸዋለሁ። በአካል ወይም በስልክ ሳልችል በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ጭምር አወራቸዋለሁ። ነገሮችን ማቻቻል ያስፈልጋል። ስራ ቢበዛብኝም በዚህ ረገድ ተጎድተዋል ብዬ አላስብም። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here