ስርዓተ ፆታ እና የትምህርት ዕድል

0
1700

ኬንያዊቷ የሠላም ኖቤል ሎሬት ተሸላሚ ዋንጋሪ ማታይ በአንድ ወቅት “ወደላይ ከፍ ባላችሁ ቁጥር፣ ጥቂት ሴቶችን ነው የምታገኙት” ብለው ተናግረው ነበር። እውነታው ታሪካዊ መሠረት አለው። ሴቶች ባለባቸው የቤት ውስጥ ጫና፣ ማኅበራዊ ኋላ ቀር አመለካከቶች እና ሌሎችም ጎታች ምክንያቶች ሳቢያ ትምህርት ቤት እንዳይሔዱ፣ ከሔዱም ባጭሩ እንዲያቋርጡ፣ ቢቀጥሉም ውጤታማ እንዳይሆኑ ይሆናሉ። ኪያ አሊ የስርዓተ ፆታ መድሎ ሴቶች በትምህርት ተወዳዳሪ እና መሪ ሆነው እንዳያድጉ አስተዋፅዖ አድርጓል በማለት የሐተታ ዘ ማለዳ ሽፋን ሰጥታዋለች።

ፀሐይ ያጠቆረው ጠይም ፊት ያላት ሳሮን ጌታቸው በጊዜ ብዛት ያረጀና ቀለሙ የደበዘዘ ሸሚዝና ቀሚስ ለብሳ ስትታይ ድህነት እንዳጎሳቆላትና የልጅነት ወዝዋን እንደቀማት በቀላሉ መረዳት ይቻላል። የዕድሜ አቻዎቿ ከትምህርት ማዕድ ሲቋደሱና በእረፍት ሰዓታቸው ሲቦርቁ ሳሮን ግን ለደንበኞቿ ሳንቡሳ መሸጥና ሻይ መቅዳት የዘወትር ተግባሯ ነው። ሳሮን የ16 ዓመት ወጣት ናት። ለቤተሰቦችዋም የመጨረሻ ልጅ ስትሆን፥ አራት ታላላቅ ወንድሞች አሏት። ሳሮን ቀኗ ከጠዋቱ ዐሥራ አንድ ሰዓት ሳንቡሳ በመጋገር ተጀምሮ እስከ ምሽቱ ሦስት ወይም አራት ሰዓት ድረስ ይዘልቃል። ምንም እንኳን የቤቱ ታናሽ ብትሆንም ቁርስ ሠርታ ለወንድሞቿ ማቅረብ፣ እናትዋን በሥራ ማገዝ፣ ለቤተሰቡ የገቢ ምንጭ የሆነውን ሳንቡሳና ሻይ መሸጥ የዕለት ተዕለት ሥራዋ ሲሆን ታላላቅ ወንድሞቿ ደግሞ ቀናቸውን ትምህርት ቤት በመዋል ያሳልፋሉ።

“ሴት እንጂ ወንድ ከማጀት ይውላል እንዴ?”
“ጠዋት ተነስቼ የምሸጠውን ሳንቡሳ ከእናቴ ጋር እሠራለው፤ እንዲሁም እናቴ ለመንድሞቼ ቁርስ ስትሠራ አግዛታለው” በማለት ሳሮን ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች። ሳሮን ምንም እንኳን እስከ አራተኛ ክፍል የመማር ዕድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም የእናትዋ ዕድሜ እየገፋ ሲሔድ እንዲሁም በኑሮ ውድነት ምክንያት ድህነት እየበረታባቸው ሲመጣ፥ እናትና ቤተሰቦቸዋን ለመርዳት ስትል ትምህርትዋን ለማቋረጥ ተገዳለች። ከጎንዋ ድንች በመቀቀልና በመሸጥ አብረዋት የሚውሉት እናትዋ አሰፋሽ መላኩ ፊታቸው በማድያት የጠቆረ የ58

ዓመት እናት ናቸው። ከባለቤታቸው ጋር በፍቺ ከተለያዩ በኋላ ልጆቻቸውን ብቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነት በጫንቃቸው ላይ የወደቀው አሰፋሽ ዘመናዊ ትምህርት አልተማሩም።

በእርሳቸው እምነት ሴቶች ቅድሚያ በቤት ውስጥ ሥራ ወላጆቻቸውን መርዳት አለባቸው። ወንዶች ደግሞ ከቤት ውጪ ባለ የሥራ መስክ ላይ ተሠማርተው ለቤተሰባቸው የተሻለ ገቢ የማምጣት፤ ለሚስታቸው ደግሞ ብረት መዝጊያ ባል መሆን አለባቸው። ምንም እንኳን ሳሮን የቤቱ ታናሽ ልጅ ብትሆንም፣ ከታላላቅ

ወንድሞቿ ይልቅ ትምህርትዋን አቋርጣ በቤትም በውጪም ሥራ ለምን እንደምታሳልፍ አሰፋሽ ሲገልጹ “ሴት እንጂ ወንድ ከማጀት ይውላል እንዴ?” በማለት ለማስረዳት ይሞክራሉ። እንዲሁም “ቤቷን እንደ አመሉ መያዝ ያለባት ሴት ናት። ወንድ ደግሞ ተሯሩጦ የቤተሰቡ ምሰሦ፣ ለሚስቱ ደግሞ ብረት መዝጊያ ነው መሆን ያለበት። ሴት ልጅ ተምራም ስታገባ ልጆቿን ለማሳደግ ስትል የቤት እመቤትም ልትሆን ትችላለች። ወንድ ልጅ ግን እቤት አይውልም። ስለዚህ በትምህርቱ ቢገፋ ጥሩ ነው። እርግጥ አቅም ቢፈቅድና ሁሉም ልጆቼ ቢማሩልኝ መልካም ነበር። ነገር ግን ድህነት ክፉ ነው ምርጫ ውስጥ ያስገባል። እናም ሁሉንም ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት እንዳልክ አድርጎኛል” በማለት በሐዘንና በትካዜ ስሜት ውስጥ ሆነው ገልጸዋል።

ከትምህርት ገበታ መገለል
ትምህርት የሰዎች ሕይወት ላይ ዕውቀቶችን በማጋራት፣ ለመረጃ ቅርብ በማድረግና አዳዲስ ሐሳቦችን ለማመንጨት የሚሆኑ መነሻዎችን በመስጠት ተፅዕኖ ያደርጋል። የሰዎችን የአስተሳሰብ አድማስ እንዲሰፋ በማድረግ፣ ጎጂ የሚባሉ ማኅበረሰባዊ ልማዶችን ለማስቀረትና በጥሩ ለመተካት ይረዳል። ለዚህ ነው ትምህርት የሕይወት ብርሃን ነው የሚባለው:: ይህንን ብርሃን ሁሉም ሰው የማግኘት መብት ሊኖረው ይገባል:: ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ሳሮን ያሉ ታዳጊዎች ከዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም:: ይኼ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ የሚታይ ነገር ቢሆንም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች ላይ የሚኖሩት ሴቶች በዚህ ምክንያት ይበልጥ ተጎጂ ሆነዋል:: የትምህርትን ዕድል ላለማግኘት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ፆታ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው::

ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታ ሳይቋደሱ ለዘመናት ኖረዋል:: በዚህም ምክንያት በኢኮኖሚ የባሎቻቸውና የቤተሰቦቻቸው ጥገኛ፣ በውሳኔ ሰጭነትና በአመራርነትም ተሳታፊ ሳይሆኑ ኖረዋል:: የኢትዮጵያን ታሪክ ያየን እንደሆነ ለዓመታት ሴቶች በፆታቸው ሰበብ የትምህርት ዕድል ሳይሰጣቸው ቆይቷል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ዘመናዊ ትምህርት ከመስፋፋቱ በፊት ትምህርት የሚሰጠው እንደ ቤተክርስቲያንና መስጂድ ባሉ የሃይማኖት ተቋሞች ውስጥ መሆኑ ነው። የዚህ ትምህርት ዋና ዓላማው ሰዎችን ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ስለነበር ሴቶች ተሳታፊ አልነበሩም። በጊዜ ሒደት ግን በቂ በሚባል ደረጃ ባይሆንም ሴቶች የሃይማኖት መጽሐፍትን ለማንበብ እንዲረዳቸው ፊደል የመቁጠር የተወሰነ ዕድል አግኝተው ነበር።

የዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር
ከሃይማኖታዊ ትምህርት ቀጥሎ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት አሻራ መታየት የጀመረው በካቶሊክ ቤተክርስቲያ አማካኝነት በትግራይ ክልል በምትገኘው የአዲግራት ከተማ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ። ሥሜነህ ጌታነህ የተባሉ ጸሐፊ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የተከፈተው ታኅሣሥ 1 ቀን 1837 አዲግራት ከተማ ዳርቻ በሚገኝ ጎልዓ መሆኑን ትምህርት ቤቱንና ዓሊቴናን በሚመለከት የተዘጋጁ ሰነዶችን በማጣቀስ ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አምስት መምህራን የያዘውና በፋዘር ቢያንቸሪ የሚመራው የመጀመሪያው የሆነው የጎልዓ ትምህርት ቤት ሥራውን የጀመረው በ13 ወንድ ተማሪዎች ነበር።

በትምህርት ቤቱ ይሰጥ የነበረው የትምህርት ዓይነትም ግዕዝ፣ አማርኛ፣ ላቲን፣ ቲኦሎጂና ሥነ ቅርፅ ሲሆን፥ የማስተማሪያ ቋንቋው በአብዛኛው አማርኛ እንደ ነበረ የቀድሞው የፅንሰታ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተርና መምህር፣ የአሁኑ የዓሊቴናቅ ቅድስት ማርያም ካቶሊካዊ ገዳም አስተዳዳሪው አባ ኃይለ ሓጎስ ያደረጉት ጥናት ያሳያል በማለት ድሬ ቲዩብ ላይ ጽፏል:: ነገር ግን በዓሊቴና ትምህርት ዕውቀትን ለመቅሰም ይመጡ የነበሩት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩት ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶችም የሚመጡ ነበሩ። ሥሜነህ በጎልዓ ከ171 ዓመታት በፊት የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት መንፈሳዊና ዓለማዊን ያስተባበረ መሆኑን እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴር “በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ታኅሣሥ 1 ቀን 1837 በጎልዓ (ዓዲግራት) ተከፍቷል ብለው ዕውቅና መስጠታቸውን ፀጋይን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል::

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዘመነ አክሱም ከክርስትና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ጋር የሚያያዝ ቢሆንም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ የዘመናዊ ትምህርት ፍላጎት እየታየ እንደ መጣ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በካሣና ራጃን ተሠርቶ ለትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠ ጥናት ይገልጻል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ዐፄ ምኒሊክ በ1900 ዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ ትምህርት ቤት እንዲከፈት አደረጉ:: በ1898 የወጣው አዋጅ ሁሉም ስድስት ዓመት የሞላቸው ወንድና ሴት ልጆች ትምህርት ቤት ሔደው እንዲማሩ ያዛል:: እነ ካሣ በሠሩት ጥናት መሠረት፥ ይህ አዋጅ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት መሔድ እንዳለባቸው ማካተቱ የወንዶች ሥፍራ ነው ተብሎ በባሕላዊው የትምህርት ዓለም ይታመን የነበረውን አስተሳሰብ ተገዳድሯል::

ይሁን እንጂ ምንም እንኳን በወቅቱ ትምህርት ይሰጥ የነበረው በነጻ ቢሆንም፥ የአብዛኛዎቹን ወላጆች ቀልብ ስቦ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ማድረግ አልቻለም ነበር:: ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የሃይማኖት አባቶች ጣልቃ ገብነትና ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከላኳቸው ባሕሪያቸው ይለወጣል ብለው መስጋታቸው እንደሆነ እነካሣ በጥናታቸው ገልጸዋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በንግሥናዋ ወቅት ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አዋጅ ከማውጣታቸውም በተጨማሪ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ ወላጆች ሕግ በመተላለፋቸው ቅጣት እንደሚጣልባቸው በማወጅ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ለማስገደድ ሞክረዋል:: ይህም ሴቶች ወደ ትምህርት ዓለም እንዲገቡ በጎ ሚና ቢጫወትም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ግን ማምጣት አልቻለም ነበር::

በ2007 በሕሊና በየነ (ፒኤችዲ) ‘National Assessment: Ethiopia Gender Equality and knowledge society’ በሚል ርዕስ በተሠራ ጥናት እንደተመለከተው ሴቶች ከወንዶች የበለጠ በሥራ ላይ ያሳልፋሉ። በ2005 ለመጀመሪያ ጊዜ ‘The 2013 Ethiopian Time Use Survey’ በሚል ርዕስ የተሠራ ሌላ ጥናት ምርታማ በሆኑም ይሁን ባልሆኑ፣ እንዲሁም በክፍያም ሆነ ያለክፍያ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ሴቶች ከወንድ አቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ያስረዳል። ይኸው ጥናት ሴቶች ከፍተኛ የሆነ የሥራ ጫና እንዳለባቸው ጠቅሷል። ይህም እንደሳሮን ያሉ ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ በማጥናት ፋንታ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ ሥራ ስለሚያሳልፉ በትምህርታቸው ውጤታማነት ላይ እንቅፋት ይሆናል። ሳሮን “አሁን ብቻ ሳይሆን እማር የነበረ ጊዜም የቤት ውስጥ ሥራ የምሠራው እኔ ነኝ። ሠርቼ ስጨርስ ስለሚደክመኝ የማጠናው ፈተና ሲደርስ ብቻ ነበር። ስለዚህ የትምህርት ውጤቴ ጥሩ አልነበረም” ትላለች።

በሌላ በኩል በተለያየ ጊዜ እንደ ዩኒሴፍ ያሉ ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ አጥኚዎች የተሠሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሴቶች በትምህርታቸው ውጤታማ የማይሆኑበትና ባስ ሲልም ትምህርታቸውን አቋርጠው ገቢ ማስገኛ ወይንም በቤት ውስጥ ሥራ ላይ ብቻ ሙሉ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ገፊ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ማኅበረሰቡ ውስጥ ለሴቶች ያለው የተሳሳተ አመለካከት ነው። ልክ እንደ አሰፋሽ ያሉ ወላጆች ሁሉንም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የመላክ አቅም ሲያንሳቸው የመማር ዕድልን ቅድሚያ ለወንዶች ልጆቻቸው በመስጠት ሴቶች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ የሚያደርጉበት ሌላው ምክንያት ነው።

ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ትምህርትን በአግባቡ ለመከታተል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ወላጆች ለልጆቻቸው ማሟላት አለመቻል ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ2009 እስከ 2010 በትምህርት ሚኒስቴር ለኹለተኛ ጊዜ በተደረገ ግምገማ 89.7 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ማረጋገጥ መርሐ ግብሩ ውስጥ የአጠቃላይ ትምህርት ግምገማ ትንሹን መሥፈርት ማሟላት አልቻሉም:: የመጀመሪያው ዙር ግምገማ ኻያ በመቶ በ2006፣ አርባ በመቶ በ2007 እና የተቀረው አርባ በመቶ ደግሞ በ2008 በአገር ዐቀፍ ደረጃ 95 በመቶ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የተደረገ ሲሆን በአማካይ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች የአጠቃላይ ትምህርት ግምገማን ትንሹን መሥፈርት እንኳን ማሟላት እንዳልቻሉ በትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሮክቶሬት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መሻሻል ባለሙያ የሆኑት ከተማ ቀውይ ገልጸዋል::

“የትምህርት ቤቶች ጥራትና ደረጃ ከተማሪዎች ውጤት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው” የሚሉት ከተማ ትንሹን መሥፈርት ያላሟሉ ትምህርት ቤቶች ቁጥር አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው ብለዋል:: ይህ ጥናት በተሠራበት ወቅት ከመገምገሚያ መሥፈርቶቹ መካከል አንዱ ትምህርት ቤቱ የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ውጤት ለማሻሻል እና ለማሳደግ ልዩ ድጋፍ አድርጓል ወይ የሚለው ነበር:: ከጥናቱ አጠቃላይ ውጤት ተነስተን ትምህርት ቤቶች ለሴት ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጋቸውን፣ ይህም ለትምህርት ጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት እንደሆነ መረዳት ይቻላል:: ሌላው በመማር ማስተማር ሒደት ላይ ጥቁር ነጥብ በማሳረፍ የሴቶችን ውጤታማነት የሚቀንሰው ከፆታ ጋር የተያያዙ ትንኮሳዎችና ጥቃቶች ናቸው። ብዙዎች እንደ ጥቃት ከማይቆጥሩት ለከፋ አንስቶ በቤትም ሆነ ከቤት ውጪ የሚያጋጥማቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ትምህርታቸውን ተግተው በመማር ፋንታ ለጭንቀትና አለመረጋጋት በማጋለጥ ውጤታማነታቸውን ከመቀነስ አንስቶ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ እስከማስገደድ የሚደርስ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል።

ፆታዊ ትንኮሳ በትምህርት ቤት
ሰላም ሙላቱ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሟ የተቀየረ) የመጀመሪያ ዓመት የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት። ዩኒቨርሲቲውን ስትቀላቀል ለማደሪያነት የተሰጣት ክፍል በሴት ተማሪዎች የማደሪያ ሕንፃ ስድስተኛው ወለል ላይ ነው። ይህ ሕንፃ ከወንዶች ዶርም ጋር የተያያዘ ሲሆን በወንዶችና በሴቶች ዶርም መካከል ያለውን ሕንፃ የሚለየው በመስታወት በር ነበር። ከወራት በፊት ይህ በር በመሰበሩ ምክንያት በምሽት በወንዶች ማደሪያ ውስጥ ከሚገኙት ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት የተሰበረውን በር አልፈው የሴቶች የመኝታ ክፍል ወዳለበት ሕንፃ በማለፍ የሴቶቹን የመኝታ ክፍል በኃይል ሲያንኳኩ እንደነበርና ዩኒቨርስቲው በሩን በላሜራ በመዝጋት ፈጣንና ተገቢ እርምጃ የወሰደበት ሁኔታ እንደነበር በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተነግሮዋል።

በወቅቱ የመኝታ ክፍል በራቸው ከተደበደበባቸው ሴት ተማሪዎች መካከል አንድዋ ሰላም ነበረች። ሰላም ሁኔታውን ለአዲስ ማለዳ ስታስረዳ “መሽቶ ስለነበር ሁላችንም የማደሪያ ክፍላችን ውስጥ ነበርን። በድንገት ግን በራችን በኃይል መንኳኳት ጀመረ። ሁላችንም በጣም ደንግጠንና ተረብሸን ነበር። በወቅቱ ከመፍራት ውጪ ምን ማድረግ እንዳለብን እንኳን አላወቅንም። ለምሳሌ እኔ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ስለሆንኩ ግቢውን እራሱ ገና በመላመድ ላይ ነበርኩ። እንደዚህ ያለ ነገር ይፈጠራል ብዬ በጭራሽ አልጠበኩም። ስለዚህ በጣም ፈርቼና ተጨንቄ ነበር” ብላለች። ሰላም ቤተ መጻሕፍት አምሽተው ሲመለሱ ከነበሩ ጓደኞችዋ እንደሰማችው ከሆነ በሩን ሲደበድቡ ከነበሩት ወንድ ተማሪዎች መካከል ሲጋራ የሚያጨሱና እንዲሁም መጠጥ ጠጥተው እንደነበር የሚያስታውቁ ተማሪዎች ነበሩበት። ውጪ የነበሩና ይህንን ሁኔታ ከሩቅ ያዩት ሴት ተማሪዎች በመጮህ በወቅቱ ዕርዳታ ጠይቀው ነበር።

ይህን መሰል ድርጊቶች የሚያሳዩት ምን ያህል የፆታዊ ትንኮሳ ባሕል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንኳን ሳይቀር ሥር የሰደደ ችግር እንደሆነ የሚናገሩትና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የስርዓተ ፆታ ባለሞያ “ሴቶቹና ወንዶቹ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ አብረው የሚማሩ፣ ከክፍል ውጪም ጓደኛሞች የሆኑ ናቸው። ስለዚህ ቀን በሰላም አብረዋቸው የዋሉ ጓደኞቻቸውን በምሽት መረበሻቸው የተሻለ መረዳት አላቸው በሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል እንኳን ሴትን የመተንኮስ ባሕል ምን ያህል አስጊ እንደሆነ ነው የጅማ ዩኒቨርስቲው ታሪክ የሚያሳየው” ብለዋል። የኢትዮያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚንስቴር ሚንስትር የሆኑት ሒሩት ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚደርሱ ትንኮሳዎች ከትምህርት ቤት ግቢ ውጪ ያለው ዓለም ነጸብራቅ እንደሆነ ያምናሉ። በመሆኑም በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ውስጥ በስርዓተ ፆታ ቢሮ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚደረገው ትግል ባሻገር ማኅበረሰቡን በማስተማር መለወጥ የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናሉ።

ሴቶችና የትምህርት ፖሊሲ
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም የሚለው እንቅስቃሴ በ1982 በዩኔስኮ፣ ዩኒሴፍ፣ ዓለም ባንክ፣ በዩኤን የልማት ፕሮግራምና በዩኤን ፖፑሌሽን ፈንድ ተጀመረ። እንቅስቃሴው ከልማት አንጀንዳዎች መካከል ትምህርትን በማካተት ብዙ አገራት ለትምህርት ትኩረት እንዲሰጡ ሠርተዋል። ይህ ሥራም ፍሬ አፍርቶ ዓለማቀፍ የትምህርት ኮንፈረንስ በጆሚቴን ተካሔደ። ብዙ አገሮች ከዚህ ስብሰባ በኋላ ‘Jomitien Declaration’ን በመቀበል ወደ ትምህርት ፖሊሲነት አሳደጉት። ኢትዮጵያም ከ‘ጆሚቴን ዲክላሬሽን’ አራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያዩ ዘርፎችን የለየና የተጠናከረ የትምህርትና ሥልጠና የትምህርት ፖሊሲ አወጣች። በመቀጠልም ይህንኑ ፖሊሲ በማሻሻል በ2010 አዲስ ፖሊሲ አውጥታለች።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊስ ባወጣችበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የትምህርት ሁኔታ ጥሩ የሚባል ሁኔታ ላይ አልነበረም። የትምህርት ዕድል ከማግኘት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ትልቁ ችግር ደግሞ ወንድና ሴት ልጆች እኩል የትምህርት ዕድል አለማግኘታቸው ነው። ይሁን እንጂ ፖሊሲው ከወጣ በኋላ ወንዶችና ሴቶች የሚያገኙትን ዕድል ለማቀራረብ በተደረጉ ጥረቶች የታዩ መሻሻሎች አሉ። ለምሳሌ አብርሃ አስፋው “Gender Inequality in Tertiary Education in Ethiopia” በሚል ርዕስ በሠሩት ጥናት መሠረት በፆታ መካከል (gender gap) የነበረው ልዩነት በ1992 ከነበረው 15 በመቶ በ2003 ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል። ነገር ግን በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እምብዛም ለውጥ አልታየም::
አብርሃ ኢትዮጵያ ውስጥ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው የትምህርት ዕድል የማግኘት ልዩነት የሚዳርጉ ተግዳሮት የሆኑና ለወንዶች ያደላ የትምህርት ስርዓት እንዲኖረን ያደረጉ ሦስት ምክንያቶች አሉ ይላሉ:: የመጀመሪያው ሴቶች ልዩ ድጋፍ በማግኘት በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የወጡ ፖሊሲዎች ወደ ተግባር በአግባቡ አለመለወጣቸው ነው:: ኹለተኛው ከትምህርት ውጪ ያሉና ከፆታ ጋር የተያያዙ ችግሮች በቤት ውስጥ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት የመሔድ ዕድላቸውን ይቀንሰዋል:: ለምሳሌ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች የገቢ ምንጭ መሆን ላይ የተሻሉ ናቸው ብሎ ማሰብ አንዱ ነው:: ለወንዶች ማድላት ደግሞ ሦስተኛው ምክንያት ነው:: “ብዙ ጊዜ ወላጆች ሴቶች ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ሥራ ማሳተፍ ላይ እንዲሁም ቶሎ እንድታገባ መገፋፋት ላይ ያተኩራሉ:: እርግጥ የኢኮኖሚ አቅማቸው የተሻለ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሱ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ቢልኩም ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ግን አይደለም” በማለት አብርሃ ይከራከራሉ።

የትምህርት ፖሊሲው ክለሳ
ብዙ ዓመታት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመሥራት ያሳለፉት ዘነበወርቅ ታደሰ በ1986 ወጥቶ የነበረው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ለሴቶች ከሞላ ጎደል በቂ ትኩረት ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፥ አሁን በ2010 ተሻሽሎ የወጣው ፖሊሲ ግን በ1986 የነበሩትን ክፍተቶች ሞልቶ ለሴት ተማሪዎች መስጠት የሚገባውን በቂ ትኩረት ማጠናከር ሲገባው ጭራሽ በ1986 ላይ ከነበረው ያነሰ ትኩረት ነው ለሴቶች የሰጠው ባይ ናቸው። “አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ለሴቶች ትንሽ ትኩረት ነው የሰጠው። ሙሉ አይደለም። በአገራችን ሴቶች ከድሮ በተሻለ ወደ ትምህርት ቤት እየገቡ ነው ተብሏል። እንደውም በአንደኛ ደረጃ ያሉ ሴቶች የትምህርት ምዝገባ መጠን ዘጠና በመቶ ደርሷል እየተባለ ነው። ነገር ግን ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የሚያስመዘግቡ ወላጆች አንዳንዶቹ በግድ ሌሎቹ ደግሞ የትምህርት ጥቅም ገብቷቸው ነው። ስለዚህ መመዝገባቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ እስከ መጨረሻው መዝለቃቸውም ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል። በተጨማሪም ልጆቹ ምን ያህል እየተማሩ ነው የሚለውም አብሮ መታየት አለበት። አምስተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብና መጻፍ በትክክል የማይችሉ ሴቶች አሉ። እርግጥ የትምህርት ጥራች ችግር የሁሉም ነው፤ ነገር ግን ተፅዕኖው ሴቶችን ይበልጥ ይጎዳል” በማለት ዘነበወርቅ ያብራራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ሴት ልጆች ከትምህርት መልስ ቤተሰቦቻቸውን በሥራ የማገዝ ኃላፊነት ስላለባቸው ለማጥናት በቂ ጊዜ አያገኙም። ወንዶች ይህን ጫና ስለሌለባቸው ለትምህርታቸው በቂ ትኩረት ለመስጠት አይቸገሩም። ዘነበወርቅ “ሌላው ቀርቶ ዩኒቨርስቲ የገቡት ልጆች እንኳን በቂ ዝግጅት የላቸውም። በፆታቸው ምክንያት ብቻ ባለባቸው ጫና በችሎታቸው ልክ መሥራት ይከብዳቸዋል” ብለዋል። በዘነበወርቅ እምነት የ2010 የትምህርት ፖሊሲ ይህንን ያገናዘበ አይደለም። ሴቶችን የሚያበረታታ የትምህርት ካሪኩለም በሌለበት ይህ መደረጉ ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው። “ከሴቶች ሕይወት ጋር የተያያዘ የትምህርት ካሪኩለም የለም። የትምህርት መጽሐፎችም የሴቶችን ችሎታና አቅም በበቂ ሁኔታ አያሳዩም” ብለዋል።

ታሪካዊ ቅርስን ማረም
አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ሲቀረፅ ጥናት ያደረጉትና ሰነዱን ያዘጋጁት በሙሉ ወንዶች መሆናቸው ፖሊሲው ለሴቶች በቂ ትኩረት እንዳይሰጥ ማድረጉን ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የስርዓተ ፆታ ባለሞያ ይገልጻሉ። “ስርዓተ ፆታ ያጠኑ ሴቶች በእንዲህ ያሉ ሥራዎች ላይ መሳተፋቸው ጉዳዩን በፆታ መነፅር እንዲያዩት ስለሚረዳ እንዲህ ያሉ ጉድለቶችን ለመሙላት ይረዳል” ብለዋል። ዘነበወርቅ የሚመለከታቸው አካላት የሴቶችን ችግር ተረድተው በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፖሊሲው መሻሻል እንዳለበት ያምናሉ። እስከዚያው ግን እንደመፍትሄ ከሚጠቁሟቸው ነገሮች መካከል የመምህራንን የስርዓተ ፆታ ዕውቀት ማሳደግ፣ ለሴቶች አርአያ የሚሆኑ በቂ ሴት መምህራንን መቅጠር፣ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አማካሪዎች ቢኖሩና ሴቶች ዩኒቨርስቲ ገብተው የሚማሩትን የትምህርት ዓይነት ከመምረጣቸው በፊት በሚመርጡት ዘርፍ ላይ በቂ ዕውቀት ቢያስጨብጥዋቸው የሚሉት ይገኙበታል። “ዩኒቨርስቲ ከገቡም በኋላ ሴቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የሚለውንም አክለዋል።

ሚኒስትር ሒሩት ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ሴቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪ ሴት ተማሪዎች ከኹለተኛ ደረጃ ዲግሪ ተማሪዎች የተሻለ ቢሆንም ወደላይ ከፍ እያለ ወደ ፒኤችዲና አሶሼት ፕሮፌሰርነት ሲኬድ ቁጥሩ እየተመናመነ እንደሚሔድ ይናገራሉ። ስለዚህ የሴቶችን አቅም የሚያጎለብትና በጥናትና ምርምር እንዲሳተፉ የሚያደርጉ ሥልጠናዎች አስፈላጊ እንደሆኑ ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሒሩትና ዘነበወርቅ ሴቶች ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በማለት ያነሱትን ሐሳብ ይደግፋል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 35 የሴቶች መብት በሚለው ሥር “ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው:: በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥትና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” ይላል::

ይህ የሚያሳየው ሴቶች በባለፉት በርካታ ዓመታት የደረሰባቸው በደልና ከትምህርት ገበታ መገለል ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሴቶች ልዩ ድጋፍ ማግኘት እንደሚገባ ነው:: በመሆኑም ሴቶች ትምህርት ቤቶችን በመሰሉ ተቋማት ከወንዶች እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ድጋፍ ማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አዋጅ አንቀፅ ስድስት ንዑስ አንቀፅ ሦስትም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ሴት፣ አካል ጉዳተኞችና ከታዳጊ ክልል የመጡ ተማሪዎች መግቢያ መስፈርትና ምዘና ከሌሎች ያነሰ እንደሆነ ገልጾ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራል።

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here