የእኩልነት እና መብቶች መከበር ጉዳይ ከውክልና ባሻገር ትኩረት ያሻዋል!

0
664

በዚህ ወር ከሚከበረው ዓለም ዐቀፉ የሴቶች ቀን መልካም ጎኖች አንዱ፥ በርካታ መረጃዎች የሚወጡበት ጊዜ በመሆኑ ኢትዮጵያ የስርዓተ ፆታን እኩልነት ለማስተካከል ምን ያህል ሥራ እንደሚቀራት ማስታወሻ መሆኑ ነው። በዚህ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመጀመሪያ ጊዜ እኩል ወንድና ሴት ምጥጥን ያለበት የሚኒስትሮች ካቢኔ አቋቁመዋል። ከዚያም በላይ ከሌላ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ሴቶች በፓርላማ ውስጥም በተሻለ ይሳተፋሉ/ተወክለዋል።

ይሁንና በተጻፉ ሕግጋትና በመንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች የሴቶች መብቶች የተከበሩ ቢመሥልም፣ እንዲሁም አንፃራዊ ውክልና ቢስተዋልም በኢትየጵያ ውስጥ ለሚገኙት አብዛኛዎቹ ሴቶች ሕይወት እምብዛም አልተለወጠም።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 35 መሠረት ለሴቶች ከተረጋገጡ መብቶች መካከል የመጀመሪያው በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ መብቶች እና ጥበቃዎች ከወንዶች እኩል ሴቶችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚያስታውሰው ነው። በንዑስ አንቀፅ 3፣ “ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” ይላል።

በእርግጥ ይህንን ግብ ለማሳካት ብዙ የተሠሩ ነገሮች አሉ። ቢያንስ በመርሕ ደረጃ ሴት ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ትምህርት ቤቶች ይዋቀራሉ። ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት ነጥብም የሚደርስባቸውን ጫና አመዛዝኖ ይመደብላቸዋል። ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም በየወረዳው የተቀመጡ መዋቅሮች አሉ። በመንግሥትና በፖለቲካ ስርዓቶች እንዲሁም በትምህርት የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ ነው። ይሁን እንጂ እስካሁን የተሠራው ወደፊት መሠራት ካለበት አንፃር በጣም ጥቂት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

እስካሁን የተሠራው በሕገ መንግሥቱ “ታሪካዊ ቅርስ ለማረም” የተባለውን የሚመጥን አይደለም። ከላይኛው የመንግሥት እርከን የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችም ወደ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር እንዲሁም ማኅበረሰብ ማውረድ አልተቻለም። አሁንም ሴቶች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ክፍሎች የሚገቡት ከወንዶች በጣም ባነሰ የቁጥር መጠን ነው። የሴቶች መብቶችና ችግሮች ያገባኛል በሚል በቂ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ ባለሥልጣኖች ያሉ አይመስልም። የተወራውን ያክል በተግባር ለውጥን በማምጣት ረገድ የታየው ጥረት አነስተኛ ነው።

ሴቶች ትልልቅ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎችን መውሰዳቸው ትዕምርታዊ መልዕክቱ ጠቃሚ ነው። የታችኛዎቹ የመንግሥት መዋቅሮች ማለትም በክልል፣ በዞንም ይሁን በወረዳ ደረጃ ያለው የተሳትፎ ደረጃ ግን ከቀድሞው ባልተሻለ ደረጃ አሁንም ዝቅተኛ ነው። ከሥር ያሉትን ሴቶች ለማሳተፍም ይሁን ለቀጣዩ እርከን ለማብቃት በቂ ጥረት እየተደረገ አይደለም። ስለሆነም ማኅበረሰቡ ውስጥ ለሴቶች ያለው አመለካከት ለውጥ አላመጣም። የተሠሩት ሥራዎች መንግሥት የሴቶችን መብቶች ማክበሩን ለይስሙላ ለማሳየት እንጂ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት አይመስሉም።

በመሠረቱ ውክልና እና ሹመት የመጨረሻ ግቦች አይደሉም፤ የስርዓተ ፆታ መድልዖን ለመቅረፍ መንገድ እንጂ! ስለሆነም፣ መንግሥት ከአሁን በኋላ የሚሠራውን ሥራ የሴቶችን ጉዳይ ለፖለቲካ ማሳመሪያነት (‘ዲኮሬሽን’) መጠቀም ብቻ ሳይሆን እውነተኛ፣ ማኅበረሰቡን የዘለቀ ለውጥ ለማምጣት ግብ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። አንድ፣ ኹለት ቦታዎች ላይ ሴት ተሾመች በሚል ብቻ ጥሩ ሥራ ተሠርቷል የሚል ግንዛቤ መጨበጥ የለበትም። በጉዳዩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል። ሴቶች ተምረው፣ በቅተው፣ በመንግሥት ሁሉም መዋቅራዊ እርከኖች ውስጥ የእውነት ተወክለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባቱ ሒደት ውስጥ ከወንዶች እኩል ሚና የሚያበረክቱበት ዘዴ መቀየስ አለበት።

#ከውክልና_ባሻገር
#BeyondRepresentation

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here