ብልጥ ልጅ የሰጧትን ይዛ ለመብቷ ትሟገታለች

0
520

“መቼስ ሴት ሴት ብለው ገደሉን”፣ “ከዚ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ብቻ ቀራችሁ”፣ “አሁንስ ጳጳስ ሆናችሁ ልትመጡ ነው!”፣ “ግን የመከላከያ ሚኒስትር እኮ እስከ ማዕረጉ ጎምለል ጎምለል ሲል ነው ደስ የሚለው!” – ይኼን የመጨረሻውን የምትለኝ ሰው በኢፌዴሪ ታሪክ ወታደር የመከላከያ ሚኒስተር ሆኖ እንደማያውቅ አታውቅም፤ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሚንስትሮች ሥም ጥቀሺ ብትባልም ይቸግራታል።

ነገር ግን የዘንድሮ ሹመት አካሔድ ሁላችንንም ፈታሽ፣ ሁላችንንም ጠያቂ አድርጎናል። ይህ ‘ሴቶች በዙ’ የሚለው ተረት በጣም ተደጋግሞ ስንሰማው እውነት እየመሰለን መጣ። ባለፈው ጥቅምት በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተካሔደው የካቢኔ ሹመት በአገር ዐቀፍ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም አነጋጋሪ ሆኗል። ከሚኒስትሮች አመራር ሃምሳ በመቶ ለሴቶች ሲወሰን፥ ኢትዮጵያን በዓለም ካሉ ጥቂት አገራት ጎን አሰልፏታል። ከሚኒስትሮች ሹመት ባሻገር፥ የዐቢይ አስተዳደር የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና የመጀመሪያ ሴት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሰጥቶናል።

እንደ አንድ የእኩልነት ንቅናቄ፥ ሴታዊት ይህንን ለውጥ እንደ ቀላል አታየውም፤ በዘመናት የማይገኝ ዕድል እንደሆነ እና በሕይወት ዘመናችን ያልጠበቅነው ክስተት እንደሆነ እንረዳለን። ነገር ግን ለዘመናት የኖረው የፆታ ኢፍትሐዊነት በአንድ ቀን እንደማይፈታም እናውቃለን።

ክብርት ፕሬዚደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ወር በጠሩት አንድ ታላቅ የውይይት መድረክ ላይ በተናገሩት ንግግር ነጥባችንን እናስረግጥ፦ “የአስተሳሰብ ለውጥ በአዋጅ አይመጣም”። ሲጀመር እኩል ውክልና በሚለው ሐሳብ ዙሪያ ውይይት የሚያስፈልግ ይመስለናል። አዎ! በከፍተኛ የመንግሥት አመራር ላይ ያሉትን ብቻ ካየን ለጊዜው የፆታ እኩልነት ይንፀባረቃል። ይሁን እንጂ የሴቶች ውክልና የተሟላ የመሰለን በፍጥነት የተደረገ ስለሆነ ነው፤ እውነታውን ለመረዳት ግን ሴቶች በሁሉም የአመራር ቦታዎች ላይ መኖር አለመኖራቸውን መፈተሽ ያስፈልጋል። ስንቶቹ ባንኮቻችን በሴቶች ይመራሉ? ከአርባ አምስት የመንግሥትና መቶ ሰባ የግል ዩኒቨርስቲዎች ስንቶቹ የሴት ፕሬዘዳንት አላቸው? በመንግሥት አስፈፃሚ አካል በኩልስ ከሚንስትርነት ባሻገር ስንት ሚንስትር ዴኤታ፣ ከዛም ወረድ ስንል ስንት የቢሮ ኃላፊና ስንት የወረዳ ብሎም የቀበሌ ሹሞች ሴቶች ናቸው? የስንት ከተሞች ከንቲባዎች ሴቶች ናቸው? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎች ጠንከር ብለን ስንጠይቅ፥ ይህ ብዙ ጮቤ ያስረገጠን የውክልና ጉዳይ ብዙ ያልተደላደለ ሆኖ እናገኘዋለን።

ይህ በቅርብ የሆነው የሥልጣን ሹመት የእኩልነት ንቅናቄ ማብቂያው ሳይሆን ገና መጀመሪያው መሆኑን እንረዳለን። ቀደም ብለን በጠቀስነው ስብሰባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሒሩት ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት “የወንዶችንም የሴቶችንም ብልሐት መጠቀም ለኢትዮጵያ ነው”፤ ኮታ ስለተሰጠን ሳይሆን ችሎታችንን ወደ ምንጠቀምበት መገስገስ ግድ ይለናል።

የሚጠበቅብን ሥራ ብዙ ነው። በአንድ ጀምበር የተሰጠን ፀጋ ካልሠራንበት፥ በአንድ ቅፅበት ሊጠፋ እንደሚችል ስለምንረዳ የተከፈተውን ልዩ አጋጣሚ ተጠቅመው አመራሮቻችን ለኢትዮጵያ ሴቶች እና ለኢትዮጵያ ወንዶች የሚበጀውን እንዲተገብሩ እንጠይቃለን። የፖሊሲዎች መሻሻልና መፅደቅ የሴቶችን ሕይወት እያደናቀፈ ያለውን ጥቃት እንዲቀንስ፣ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት እንዲሻሻል፣ እንዲሁም የሴቶች የጤና አጠባበቅ እንዲጨምር ያደርጋል። የሴቶች መብት ሲከበር ወደ የሚለካ እኩልነት እንደርሳለን።

እንደ ዐቢይነት ለመግለጽ፣ የሰላም ሚንስትራችን የኅብረተሰቡን ሰላም ሊያስከብሩ ላይ ታች ሲሉ፥ የሴቶች ሰላም በፆታዊ ጥቃትና በፆታዊ ትንኮሳ ምክንያት ከደፈረሰ ውሎ ያደረ መሆኑን በማገናዘብም ጭምር እንደሆነ እናምናለን። እንዲሁም የትራንስፖርት ሚንስትራችን ሴቶች በየከተሞቻችን በሚገኙት የትራንስፖርት መስኮች ላይ በሚገጥማቸው አካላዊ እና ወሲባዊ ትንኮሳዎች መፍትሔ እንደሚሰጡን እናምናለን። በመጨረሻም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትራችን የዩኒቨርስቲ ቦርድ አባላት የፆታዊ እኩልነት ይዘት እንዲኖርባቸው ያስተላለፉትን መመሪያ እያደነቅን ፍትሐዊ ውድድር እስኪኖር ድረስ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እናስተጋባለን። “አትችሉም” ሲባሉ ለኖሩት የኢትዮጵያ ሴት ልጆች “ትችላላችሁን” ለማምጣት ሥራ እንደሚያስፈልግ እናምናለን።

እንደ አንድ የሲቪል ማኅበረሰብ አካል ሴታዊት ከሁሉም የመንግሥት አመራሮች ጋር በመቆም ፆታዊ ፍትሐዊነት የተሻሻለባት፣ ሰላም፣ ልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ሰፈነባት ኢትዮጵያ ለመጓዝ በአጭሩ ታጥቃለች። በለውጥ ሒደቱም ተስፋን ሰንቃለች፤ እኩልነትን ባማከለ የዕድገት መሥመር ትተማመናለች። በአጋርነትም እንደምትታገል ቃል ትገባለች። ሴታዊት ዛሬም ወደ ፊትም የሴቶች መብት መጠበቅን ትሞገታለች።

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here