የ40/60 ቤቶች ለእድለኞች እንዳይተላለፉ ፍርድ ቤት አገደ

0
586

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት በቅርቡ እጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለእድለኞች እንዳይተላለፉ አግዷል፡፡

እገዳው የመጣው የጋራ መኖሪያ ቤቱን ለማግኘት ከተመዘገቡት ውስጥ 100 በመቶ የከፈሉ 98 ተመዝጋቢዎች ክስ መመስረታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ከሳሾቹ በ2005 የጋራ መኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ዳግም ምዝገባ ወቅት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የቤቶቹን ዋጋ መቶ በመቶ በመክፈል ቅድሚያ ለማግኘት የገቡት ውል ተጥሶ ቤቶቹ እጣ እንዲወጣባቸው ተደርጓል በሚል ተቃውሞ ነው ክስ የመሰረቱት፡፡

98ቱ ተመዝጋቢዎች የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒቴርን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከሰዋል፡፡

በመመሪያው መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕጣ አውጥቶ ለእድለኞች ማከፋፈል ሲገባው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያን ጥሷል ሲሉም ከሰዋል፡፡ ተቃውሟቸውም 100 በመቶ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች እያሉ ከ40 በመቶ ጀምሮ የቆጠቡትን በእጣው አካቶ ማውጣት ከሕግና ውል ውጪ በመሆኑ ተገቢ አይደለም የሚል ነው።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ፕሮግራሙ 40/60 በመሆኑ ትንሹን ማለትም 40 በመቶ የቆጠበ እጣው ውስጥ መግባት አለበት የሚል አቋም እንደያዙ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የተከሳሽ ተቋማትን ምላሽ ለመስማት ለግንቦት 29 ቀጠሮም ተሰጥቷል፡፡ የካቲት 27 እጣ የወጣባቸውን 18 ሺሕ 576 የ40/60 ቤቶች ለባለእድለኞች ለማስተላለፍ የከተማዋ ቤቶች አስተዳደር ዝግጅት ላይ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here