የድርጅት ውስጥ ዴሞክራሲ

0
807

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መተባበር ከማይችሉበት እና አልፎ ተርፎም ከሚሰነጣጠቁበት ምክንያቶች አንዱ ውስጠ ዴሞክራሲ የሌላቸው መሆኑ ሳይጠቀስ አይታለፍም። በመሠረቱ በፓርቲያቸው የውስጥ አሠራር እና ባሕል ዴሞክራሲያዊ አካሔድን ያልገነቡ ፓርቲዎች የመንግሥትን ሥልጣን ቢቆጣጠሩም ዴሞክራሲ የመገንባት ችግር ይገጥማቸዋል። ከሁሉም በላይ ግን መንግሥት መገንባት የሚያስችላቸው አቅም መገንባት ከነአካቴው የሚቸገሩ መኾኑ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የግለሰብ ፓርቲዎች ይመስላሉ። ብዙዎቹ ፓርቲዎች ከአንድ ግለሰብ ጋር ተያይዘው የሚታወሱ ናቸው። የፈረሱት ፓርቲዎች ባብዛኛው ምክንያታቸው የአመራሮች ፀብ ነው። ለረዥም ዓመታት ኅልውናቸውን ያስቀጠሉት ፓርቲዎች ደግሞ አመራር ሳይቀይሩ ነው ለዓመታት የሚዘልቁትት። አንጋፋዎቹ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እና በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ለዚህ ሁነኛ ምሣሌዎች ናቸው። ፓርቲዎቻቸው ከተመሠረቱ በኋላ አመራር ኾነው ለኹለት ዐሥርት ዓመታት ዘልቀዋል። በርግጥ የድርጅት ውስጥ ዴሞክራሲ በሊቀ መንበሮቹ መቀያየር ብቻ አይወሰንም። የሐሳብ ብዝኀነት በማስተናገድ ችሎታቸው፣ በመደበኛ ስብሰባቸው በሚደረጉ ፉክክር የተመላባቸው የሊቀ መንበር እና ሥራ አስፈፃሚ ምርጫዎች፣ በሥራ ክፍፍል፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና ሌሎችም መሥፈርቶች ጭምር መኾን ይኖርበታል።

ቲም ሚስበርግ የተባሉ የምርጫ ዴሞክራሲ ባለሙያ “በፓርቲዎች ውስጥ ዴሞክራሲያዊነትን ለማረጋገጥ ኹለት ዘዴዎች አሉ” ብለዋል። ከእነዚህም አንዱ ‘አድቮኬሲ’ (የፖለቲካ ውትወታ እና ግፊት ሲሆን)፣ ሌለኛው ደግሞ ሕጋዊ የቁጥጥር መንገድ ነው። ጸሐፊው እንደምሳሌ የስፔንን ሕገ መንግሥት አንቀፅ 6 ይጠቅሳሉ፦ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ብዝኀነት መገለጫ ናቸው፤ የሕዝቦችን ፈቃድ ለመመሥረት እና ለመግለጥ እንዲሁም ለፖለቲካዊ ተሳትፎ መሠረታዊ መንገድ ናቸው።

አመሠረራታቸውም ይኹን ተግባራቸው ሕገ መንግሥቱን እስካከበሩ ድረስ ነጻ ነው። የውስጥ መዋቅራቸውም ይኹን አሠራራቸው ዴሞክራሲያዊ መኾን አለበት።”

በኢትዮጵያ ግን ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊነታቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥብቅ መመሪያ የለም። ሌላው ቀርቶ በዘውግ ማንነት የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማንነት ምክንያት የማግለል ሥራ እስከመሥራት ይደርሳሉ። በማንነት ምክንያት አባላት የማይቀበሉ፣ የተቀበሉትን አባላት በይፋ የሚያገሉ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ መሠረታዊ መብቶች እንዳይጣሱ፣ እንዲሁም በፓርቲዎች ውስጥ ዴሞክራሲያዊነት በተግባር እንዲታይ የሚመለከተው አካል የሚከታተልበት እና የሚቆጣጠርበት ሕጋዊ ኀላፊነት ሊሰጠው ይገባል። አለበለዚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ባሕልን ማስረፅ ይቸግራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here