አዳዲሶቹ ፓርቲዎች እጃቸው ከምን?

0
898

ወቅቱ የፖለቲካ ምኅዳሩ የተከፈተበት እንደመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መነቃቃት የሚያሳዩበት ነው። ይህንንም ተከትሎ አዳዲስ ፓርቲዎች እየተደራጁ እና ነባሮቹም እየተጠናከሩ ነው። ለመኾኑ አዳዲሶቹ ፓርቲዎች ነባሮቹን ለምን አይቀላቀሉም? ለምንስ ውሕደት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አስቸጋሪ ጉዳይ ሆነ? የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ፖለቲከኞችንና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን በማነጋገር የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቷቸው በይፋ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታት አዳዲስ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲደራጁ፥ አንዳንዶቹ ሲቀናጁና ሲዋሐዱ እንዲሁም ደግሞ ተሰነጣጥቀው ሲለያዩ ይስተዋላል። ጥቂት የማይባሉ ደግሞ ከናካቴው ከስመዋል። ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ሲቃኝ ከጥንካሬው ይልቅ ድክመቱ የጎላ መሆኑን የሚናገሩ የመኖራቸውን ያህል፥ ከተጨባጩ ሁኔታ አንፃር የአቅማቸውን ያህል እየሠሩ ነው ብለው የሚከራከሩላቸውም አሉ። ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ የተናጠል ጉዞ መምረጣቸው፣ በኅብረት መሥራት ቢጀምሩም ብዙም ሳይራመዱ መለያየታቸው በየፓርቲዎቻቸው ውስጥም በመከፋፈልና መናቆራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚተቹ ወገኖች በድክመትነት የሚያነሱባቸው ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ለእንቅስቃሴያቸው መገደብ መንግሥት ይፈፅምብናል የሚሉትን ወከባ እንደዚሁም ገዢው ፓርቲን ደጋግመው በምክንያትነት ያቀርባሉ።

ኢትዮጵያን ያስቸገራት የፓርቲ ማነስ ሳይሆን መብዛት ነው የሚሉ ምሁራን አሉ፤ ይሁን አንጂ አሁንም ድረስ ፓርቲዎች በምስረታ ላይ ናቸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አገሪቱ የምትከተለው ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓት እንደሆነነና ሁኔታው እያንዳንዱ ብሄር ይወክለኛል የሚለውን አንድና ከዚያ በላይ ፓርቲ እንዲመሰርት የሚያበረታታ ስርዓት መሆኑ ነው ይላሉ፡፡ 76 ብሔር ባለበት አገር ይህ ምን ማለት እደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለመሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴና አቅም እንዴት ይመዘናል? ፓርቲዎቹ ለምን አይተባበሩም? አዳዲሶቹስ ምን አዲስ ነገር ይዘው መጡ?

ፓርቲዎቹ ለምን አይተባበሩም?
የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር የመፍጠር ታሪክ የክሽፈት ታሪክ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከ1983 በፊት በነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተደረጉ ትብብሮች ዋና ማጠንጠኛ የነበረው የደርግን ስርዓት በትጥቅ ትግል ወይም በፕሮፖጋንዳ በመፋለም ዙሪያ ነበር። ከ1983 በኋላ ደግሞ የነበሩት ትብብሮች ገዢውን ፓርቲ ኢሕአዴግን በምርጫ ፖለቲካ፣ አሊያም በትጥቅ ትግል መታገል ነበር። ኢሕአዴግ ደርግን በትጥቅ ትግል አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝም ከዚያ ቀጥሎ በመጡ አገሪቱን መልሶ በመገንባት፣ የዴሞክራሲ ስርዓትን በመዘርጋት፣ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ ፈተናዎች ወድቋል።

ከ1983 ወዲህ ከተደረጉ የተቃዋሚ ትብብሮች ደግሞ የ1997ቱ አገር ዐቀፍ ምርጫ ክስተት የሆነው ቅንጅት ቅድሚያ እንደሚይዝ የሚያወሱት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር)፥ “ምንም እንኳን የድኅረ ምርጫ 97 ታሪክ አንገት የሚያስደፋ ቢሆንም፣ አገራችንን ከተጫናት የፍርሐት ፖለቲካ ሰብሮ በመውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ታሪክ የዴሞክራሲ ምርጫ ሒደትን እንድናይ አድርጎን ነበር” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ከላይ ከተጠቀሱት ውጤቶች ባሻገር፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተደርገው የነበሩ ትብብሮች ውጤት ከማምጣትና ያመጡትን ውጤት ከማስጠበቅ አንፃር ደካሞች መሆናቸውንም አልሸሸጉም።

እንደሚታወቀው በአገራችን የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አገር ዐቀፍ እና በብሔር ዙሪያ የተደራጁ ናቸው። በአገር ዐቀፍ ዙሪያ የተደራጁ ፓርቲዎች በግለሰብ መብቶች ላይ ቅድሚያ ሰጥተው ለቡድን መብቶች ዕውቅና የሚሰጡ ሲሆን፥ በብሔር የተደራጁት ደግሞ የቡድን መብቶች መከበርን ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው። ይህ የአስተሳሰብ ልዩነት በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በአገር አወቃቀር (state structure) ላይ ያላቸው ልዩነት ምንጭ ነው። ይህ ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ በአገር ዐቀፍ ዙሪያ የተደራጁ ፓርቲዎች እርስ በርስ ያላቸው ልዩነት ሆነም በብሔር ላይ የተደራጁ ፓርቲዎች መካከል ያለ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት ይህን ያህል ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር የማያስችል እንዳይደለ በቅርቡ ከቱርክ በፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት መስክ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተው የተመለሱት አብዱልቃድር ይናገራሉ፥ ይሁን እንጂ ከታሪክ እንደምንረዳው የስብስቡን ውጤታማ አለመሆን ስለሆነና ስለስብስቡም በደንብ ማወቅ ስላለብን፣ ሕጋዊነቱንም ማወቅ ስለሚገባን ለቀረበልን ጥያቄ የሰጠነው ምላሽ አለመቀበልን ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ፣ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ለመገንባት ብሎም የፓርቲያቸውን ራዕይና ዓላማዎች በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት የሚያግዝ ሆኖ ሲገኝ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቅና ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀትና ግምባር በመፍጠር እንደሚሠራ አብዱልቃድር (ዶ/ር) ይናገራሉ። ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚፈጠሩ የትብብር መድረኮችና ቅንጅቶች የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ሕጎችና ደንቦች መሠረት ያደረገ እንደሚሆንም አክለው ነግረውናል።

ከፍጥጫ፣ ከሴራና መጠላለፍ የራቀ የፖለቲካ ትግል እንደሚከተሉ የሚናገሩት አብዱልቃድር፥ ፓርቲያቸው ከማናቸውም የፖለቲካ ኃይል ወይም ድርጅት ጋር በኃላፊነትና በአገር ፍቅር ስሜት እንደሚሠራ አውስተው፥ አገርንና ሕዝብን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፕሮግራም ካለው የፖለቲካ ድርጅት ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

በግለሰቦች ስብእና ዙሪያ የተገነቡ ፓርቲዎች
ድርጅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአገራችን የተፈጠሩ ፓርቲዎች ተቋማዊ ቅርፅ ይዘውና ከግለሰቦች ስብእና በላይ ሆነው መሥራት አለመቻላቸው አጠቃላይ እውነታ ነው። ይህም የሐሳብ ብዝኀነትን ማስተናገድ የማይችለው የአገራችን ፖለቲካ ነፀብራቅ እንደሆነ ብዙዎች ያነሳሉ። የፖለቲካ ትብብሮች በአጭር እንዲቀጩና ውጤት አልባ እንዲሆኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ በፖለቲካ መሪዎች መካከል ያለ የሻከረ ግንኙነት ነው። ይህም የሻከረ ግንኙነት ከጊዜያዊ ትብብር ባሻገር በመርሕ ላይ የተመሠረት አንድነትን መፍጠር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጣም ትናንሽ በሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሞላቱ የሚያመላክተው ቁም ነገር ፓርቲዎች የተቋቋሙት በግለሰቦች ስብእና ዙሪያ እንጂ በመርሕና ፖለቲካዊ አጀንዳ ላይ አለመሆኑን ነው። በዚህም የተነሳ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጤት አልባ ከመሆናቸውም በላይ ልምድ ያላቸውና ጠንካራ አመራሮችም እንዲበታተኑ ሆነዋል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞቹ።

በእኛ እምነት የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ከፓርቲና ፓርቲን ከሚመሩ ግለሰቦች ፍላጎት በላይ ነው ብለን እናምናለን የሚሉት የኢትዮጵያተራማጅ ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ አመራር ሞሐመድ አሊ ሞሐመድ፣ የፓርቲንና ግለሰብ መሪዎችን ፍላጎት ከማርካት ባለፈ መሠራት እንዳለበት ኢትዮ ሪፈረንስ በሚባል በይነ መረብ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ጠቁመዋል፥ “የተሻለ አማራጭ ሆነን፣ ይዘን ለመውጣት ጠንክረን በትጋት መሥራት እንዳለብን እናምናለን። እናም አገርና ሕዝብን መምራት በሚያስችል ቁመና ላይ መሆናችንን ማረጋገጥና በተግባር ማሳየት እንዳለብን በግልጽ እንገነዘባለን። ስለሆነም በተገኘው መንገድ ሁሉ የፖለቲካ ሥልጣን ከመያዝ ባለፈ፣ አገርና ሕዝብ የሚመካበት ፓርቲ፣ ተቋም የመገንባት አገራዊ ግብና ራዕይ አለን” ሲሉም የፓርቲያቸውን ፕሮግራም ይናገራሉ።

አብዱልቃድር በፓርቲዎች መካከል የነበረው ሳይንሳዊ ያልሆነ ውሕደትና በግለሰቦች ግፊትና ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ ጥምረቶችና ውሕደቶች እንደነበሩ ያምናሉ፤ በዚህም ምክንያት ሕዝብ የሚፈልግባቸውን ማድረግ ሳይችሉ ተንኮታኩተው መቅረታቸውን ይናገራሉ።

በመሆኑም በፖለቲካ እንቅስቃሴአቸው ከድርጅታዊና ግለሰባዊ ድል እና ስኬት ይልቅ የአገርንና የሕዝብን ድልና ስኬት እንደሚያስቀድሙ በፕሮግራማቸው ማስቀመጣቸውን የመሚናገሩት አብዱልቃድር፥ የፓርቲያቸው ውጤታማነትና ስኬት በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድቀት ላይ ሳይሆን፣ አብሮ በማደግ እውነተኛ የአጋርነት ስሜት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያወሳሉ።

እንደተለመደው በትንሽ በትልቁ የፖለቲካ እንካ ሰላንቲያና አተካራ ውስጥ በመግባት አጉል ትኩረት ለመሳብ በመሞከር ላይ የተመሠረተና ግልብነት የሚያጠቃው የትግል ስልትና ስትራቴጂ የለንም የሚሉት ሞሐመድ አሊ ሞሐመድ፣ ምርጫን ተደግፈን መድረክ በማግኘት “በአቋራጭ ዕውቅናን ማትረፍ” በሚል አጭር ዕይታ የተገደበ ግብ እንደሌላቸው ጠቁመው፥ “የገዥውን ፓርቲ ድክመቶችና ክፍተቶች ነቅሶ በማውጣት፣ አጉልቶ በማሳዬትና በመተቼት ብቻም ሕዝብ እንዲመርጠን አንሻም። እኛ ከዚያ ባለፈ፣ የራሳችን የፖለቲካ አጀንዳና፣ ከገዥው ፓርቲ ላይ ነቅሰን ላወጣናቸው ችግሮችም አማራጭ መፍትሔ ይዘን መቅረብ እንፈልጋለን። ስለሆነም ገዥው ፓርቲ የሚጥልልንን የአጀንዳ ፍርፋሪ እየጠበቅን እንደዶሮ በመንጫጫት ሕዝብን ማደንቆርና እንደዋዛ ጊዜ ማጥፋት አንፈልግም” በማለት ሐሳብ ያቀርባሉ።

ሙሉጌታ አበበ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የፓርቲዎችን ቁጥር ለመቀነስ ተዋሐዱ፥ ተሰባሰቡ ከማለት ይልቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ ስርዓት መዘርጋት አለበት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሁን ላይ “ልጆቹን የማያውቅ አባት ነው” በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሙሉጌታ ለዚህ ማሳያነት የሚያቀርቡት ምርጫ ቦርድ ልጆቹ የሆኑ ፓርቲዎችን ቁጥርና ማንነት አለማወቅ እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ አለማድረጉን ነው። በአንድ አባል (ሊቀ መንበር ወይም ፕሬዝዳንት) ብቻ ያለው ፓርቲ መኖሩም የአደባባይ ሚስጥር እንጂ የተደበቀ ገመና አይደለም። አባላቱን በ50 ብር ጉቦም ያስፈረመ ፓርቲ አለ እየተባለ ይታማል። ጠቅላላ ጉባዔ የማያደርጉ፣ ጽሕፈት ቤት የሌላቸው፣ የተሟላ ሥራ አስፈፃሚ የሌላቸው በርካታ ፓርቲዎች ስለመኖራቸውም ራሳቸው ፓርቲዎች ገመናቸውን ያምናሉ ባይ ናቸው ሙሉጌታ።

ለዚህ ትችት መልስ እንዲሰጡ የጠየቅናቸው በምርጫ ቦርድ የኮምኒኬሽን አማካሪዋ ሶልያና ሽመልስ ሲመልሱ፥ “ምርጫ ቦርድ ሪፎርሙን ከጀመረ ገና አምስት ወር አልሞላውም። ከሥራዎቹ ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ ያለው የሕግ እና የፖለቲካ ማዕቀፉን እንዲሁም ቦርዱን እንደተቋም ለሁሉም ፓርቲዎች እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የሚጠቅም አድርጎ ማሻሻል ነው። ሕግና መዋቅራዊ ማሻሻያዎቹን ተከትሎ የተሻሻሉትን ሕጎችና አዳዲስ ተአማኒነት ያላቸው የቦርድ አመራሮችን ካሟላ በኋላ፥ የቁጥጥር ሥራውን ማጠናከር ቀጣይ ሥራ ይሆናል። ቅሬታዎች ይቀርቡበት የነበረ ተቋም ከመሆኑም የተነሳ የተደላደለ የሕግና የአሠራር መደላድል ላይ ተቋሙን ማድረስ የቁጥጥር ሥራውን ተቀባይነት እንዲኖረው ይረዳል ብለን እናምናለን” ብለዋል።

ደካማ ድርጅታዊ አቅም
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ መዋቅራቸው ከላይ ወደ ታች (vertical) የተዋረድ የሥልጣን ክፍፍል ያለበት፣ እንዲሁም በተለያዩ ክፍሎች መካከል የጎንዮሽ (horizontal) የሥራ ግንኙነት ደካማ የኾነበት መሆኑን የሚናገሩት በጀርመን የፓሳው ዩኒቨርሲቲ ‘ገቨርናንስና ፐብሊክ ፖሊሲ’ ድኅረ ምረቃ ተማሪ የነበሩት ዳዊት ዓለሙ በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ በጻፉት መጣጥፋቸው፣ የሰው ኃይል (በከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራር) አቅማቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ የፋይንንስ ምንጫቸው ከአገር ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ የፓርቲዎቹ ማኅበራዊ መሠረት ጠቦ በፓርቲዎቹ ውስጥ የሚሳተፉ የፖለቲካ ልኂቃን ምሁራን (‘party-based elites’) የሆነ ነው። በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣም ምስጢረኝነት የበዛባቸው፣ ኀላፊነትንና ተጠያቂነትን አብሮ የማያሰፍን ውስጣዊ አሠራር ያላቸው በመሆኑ ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ባሕል የጎደላቸው እንዲሆን አድርጓቸዋል። ይህም በፓርቲዎች መካከል ሊኖር የሚገባው ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት እንዳይኖር ሲያረግ፣ ትብብር ቢፈጥሩም ትብብሩ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ እንዲሆን ሆኗል። በዚህም የተነሳ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅማቸው ደካማ ስለሆነ በአብዛኛው ከነመኖራቸው ራሳቸውን ለማኅበረሰቡ የሚያስተዋውቁት ምርጫ የተወሰነ ጊዜ ሲቀረው ብቻ ነው:: ከምርጫ በኋላ እንቅስቃሴ ቢኖር እንኳን መሪዎቹ ጎልተው የሚወጡበትና እንደ ድርጅት ፖለቲካ ፓርቲዎች የማይታዩበት ነው:: በዚህም ባሕሪያቸው “የምርጫ ፖለቲካ ፓርቲ” የሚለው ሥያሜ እንደተቸራቸው “ድርጅታዊ ጥንካሬና የመደራደር አቅም ውሱንነት” በሚል ርዕስ በበይነ መረብ ላይ ባሰራጩት ጽሑፍ ያወሳሉ።

ድርጅታዊ አቅም የተለያዩ ፍቺዎች ቢኖሩትም በሦስት ቁምነገሮች ላይ እንደሚያተኩር የሚናገሩት ዳዊት፣ የሰው ኃይል፣ አደረጃጀት እና አሠራር መሆናቸውን ጽፈዋል::

ኢትዮጵያ በፖለቲካ ፓርቲ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ባሕል ውስጥ የገባችው የ1960ዎቹን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ነው:: ይህም ሁናቴ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሠረቱት ፖለቲካ ፓርቲዎች በግራ ዘመም የፖለቲካ አተያይ ላይ የተመሠረቱ ናቸው:: ይህ ግራ ዘመም የፓርቲ ፖለቲካ አተያይ በፓርቲዎች ርዕዮተ ዓለማዊ አቋም ብቻ የሚንፀባረቅ ሳይሆን እንደብረት በጠነከረ የፓርቲ ሥነ ስርዓት፣ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ ጥብቅ ከላይ ወደታች የሚፈስ የዕዝ ሰንሰለት ጭምር የሚታይ ነው:: ምንም እንኳን የአገራችን ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ርዕዮተ ዓለምን የሚከተሉ ቢሆንም ይህ የግራ ዘመም የፖለቲካ አስተሳሰብ በከፍተኛ ሁኔታ የተጫናቸው እንደሆኑ ዳዊት ይተነትናሉ::

በሌላ በኩል፣ በተለይ የአንድነት/የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ነን የሚለው ኃይል የተበታተነበትና የተዳከመበት ሁኔታ ላይ አገሪቱ እንደምትገኝ የሚያምኑት መሐመድ፣ በቁጥር ብዙ ፓርቲዎች አሉ ቢባልም እንደ አማራጭ ግን ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው፣ ግልጽ የሆነ አጀንዳ፣ ስትራቴጂ ያላቸውን ፓርቲዎች ብዙ መዘርዘርና መቁጠር ባለመቻሉ አማራጭ ኃይል ሆነን መጥተናል ማለታቸውን በኢትዮ ሪፈረንስ ድረ-ገጽ ላይ ከሰፈረው ጽሑፋቸው ላይ ማየት ይቻላል። የህግ ምሁርና ጠበቃው መሐመድ አሊ የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የተለያየ ሃይማኖት፣ ብሔርና ፆታ ተዋጽኦ የተውጣጡ ግለሰቦች ያሉበት ፓርቲ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አብዱልቃድር በበኩላቸው ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት፣ ድርጅታዊ አቅሙን አጠናክሮ አገራዊ መግባባትን ለማጠናከር፣ ጤናማ የፖለቲካ ውድድርን እውን ለማድረግ፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ለመገንባት የራሱን ሚና እንደሚጫወት በፕሮግራማቸው ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።

የምስረታ ሂደት ላይ ያለው ሌላው ፓርቲ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ሊበራ ፓርቲ በበኩሉ በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና በማህበራዊ ፍትህ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ከፓርቲው አስተባባሪዎች አንዱ ውባለም ታደሰ (ዶ/ር) ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት ከሆነ የተለያዩ ታዋቂ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ምሁራን የተካተቱበት ይህ ፓርቲ በሀገሪቱ የሚታየውን ስር የሰደደ ድህነትና ማህበራዊ ፍትህ ዕጦት ለመቅረፍ ፓርቲው መፍትሄ አለው። ይሁን እንጂ የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሙራድ መሀመድ የፓርቲውን ዝርዝር ፕሮግራም ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉት ወደፊት ከምስረታ በኋላ እንደሆነ በመናገራቸው ስለፓርቲው ሰፋ ያለ መረጃ ለማቅረብ አዲስ ማለዳ አልቻለችም፡፡

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አለን?
አብዱልቃድር (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከነችግሩ መታየት የጀመረው ከ1983 ወዲህ መሆኑን ያወሳሉ። ምክንያቱም በቀዳሚነት ሕገ መንግሥቱ የመደራጀት፣ የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽና የተቃውሞና ድጋፍ ሰልፍ ማድረግን ፈቅዷል። ይሁን እንጂ አፈፃፀም ላይ ያሉት እንቅፋቶች ቀላል እንዳልነበሩ ጨምረው ጠቅሰዋል።

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማለት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በአገራዊ ምርጫ ለሥልጣን የሚወዳደሩበት ስርዓት ነው። በተናጠል ወይም በጥምር ደረጃ የሕዝብ ሥልጣን ፓርቲዎች የሚረከቡበት ሒደትም ነው። ለአብነት ያህል በጀርመን ከ2013 ምርጫ በኋላ በክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን እና በሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተፈጠረው ጥምረት ዓይነት ነው።

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የእነ አሜሪካን ከመሰለው ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት ይልቅ በፓርላሜንታዊ ስርዓቶች የተሻለ ዕድል እንዳለው ይታመናል። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ በሕግ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ሳይሸራርፉ በኃላፊነት ስሜት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከተቻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ብዙ ናቸው።

እነዚህ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ፓርላሜንታዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አራማጅ አገሮች ያለው የምርጫ ፉክክር ግን ከአምስት ባነሱ የፖለቲካ ማኅበራት የሚፈፀም ነው። በፓርቲዎቹ መካከል ያለው የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነትም ግልጽና የማያሻማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዐቀፍ ገጽታንም የተላበሰ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ወደርና አቻ ያለው አይደለም። ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር በአንድ ወቅት “ለማያ ጋዜጣ” እንደተናገሩት፣ “በምርጫ ወቅት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ገቢ መሰብሰብያ ፓርቲ ከሚመሠረቱ ተለጣፊ ድርጅቶች እስከ ግልጽ ፖሊሲና የፖለቲካ ልዩነት ማሳያ አልባ የብሔር ፓርቲዎች ድረስ እንደ አሸን የፈሉባት አገር ኢትዮጵያ ነች።” ብለዋል፡፡

ይህ አባባል እውነት አይደለም ብሎ መከራከር ያስቸግራል። ምክንያቱም በየአምስት ዓመቱ ከ50 እስከ 70 የሚደርሱ ድርጅቶች “ፓርቲ” ተብለው አባላትና ደጋፊዎቻቸው ሳይታወቁ፣ ግልጽ ሥያሜያቸውና የፖሊሲ አማራጮቻቸው እንኳን ሳይታወቁ በምርጫው ይወዳደራሉ። እንደ ዳኛቸው ገለጻ ይኼ ደግሞ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካን ከማሳደግ ይልቅ የገዥውን ፓርቲ አውራነት የሚያጠናክርና የዴሞክራሲ ባሕሉን የማይገነባ ነው።

የአብዱልቃድር መልስ ከዚህ የተለየ ነው፤ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ መኖሩን ገልጸው፥ አፈፃፀም ላይ ግን ከወረቀት ባለፈ አለመሆኑንና ለዚህም ቀዳሚ ተጠያቂው መንግሥት መሆኑን በማንሳት፣ ፓርቲዎች እንደፈለጉ የመንቀሳቀስ ዕድሉን ባለማግኘታቸው አንድ ፓርቲ ብቻውን የሚወዳደርበትና የሚያሸንፍበት ሁኔታዎች እንደነበሩ ይናገራሉ።

የአዲሶቹ ፓርቲዎች ዕይታ
የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ አሁን በአገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በጣም አሳሳቢና በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ ከባድ በመሆኑ አማራጭ ሆኖ መምጣቱን አውጇል።

አሁን በአገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በጣም አሳሳቢና በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ማወቅ አይቻልም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የፓርቲ የአደራጆች አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ አሊ መሐመድ፣ በዚህ ሁኔታ አማካይ ቦታ ያለው ሁሉን ዐቀፍና በአንፃራዊነት ሁሉም ወገን የኔ ነው ሊለው የሚችል አንድ የተደራጀ ኃይል መኖር አለበት ብለን ስላመንን ከአንድ ዓመት በላይ ተከታታይ ውይይቶች ተደርገው አገራዊ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የተመሠረተ ፓርቲ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።

የአገሪቱና የሕዝቡ ችግሮች ምንጭ በዋናነት ፖለቲካዊ እንደሆነ እና መፍትሔውም ባብዛኛው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መሆኑን የሚናገሩት አብዱልቃድር፥ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ አግላይ የፖለቲካ ስርዓት፣ ፖለቲካዊ ፍትሕ መጥፋት፣ አድሎ፣ ወገንተኛነት፣ ብሔርንና እምነትን መሠረት ያደረጉ ልምዶችና አሠራሮች የአገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት መገለጫዎች ሆነው ማለፋቸውን በመግለጽ፥ የዘር፣ የጎሳና የሃይማኖት ብሔርተኝነት ሕዝባችንን ከፋፍሎ አንድነታችንን አላልቶታል ይላሉ። ለታሪካችን ያለን ቦታና አረዳድ እጅግ የተራራቀ ሲሆን ታሪካዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነቶች እየሰፋ መምጣቱን ለአዲስ ማረዳ ጨምረው አስረድተዋል።

ነጻና ገለልተኛ የፍትሕ ስርዓት መጥፋት፣ ሥራ አጥነትና ድህነት፣ የመሠረተ ልማት እጥረት፣ ማኅበራዊ ቀውስ፣ የአገርና የሕዝብ ፍቅር መሸርሸር፣ በዜጎች መካከል መተማመን መጥፋት እና ጥርጣሬ መንገሥ ከአገራችን አንኳር ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን የሚያነሱት አብዱልቃድር፥ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎት፣ በቂ ትራንስፖርትና መገናኛ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የሕዝብ አስተዳደር የአገራችን ሕዝብ ሕልም እና ምኞት መሆናቸው ዛሬ ድረስ እንደቀጠለ ይገኛል ባይ ናቸው።

የአንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የፖለቲካ ሥልጣን ትልቁና የመጨረሻ ግብ አገርንና ሕዝብን ማገልገል መሆኑን የሚናገሩት አብዱልቃድር (ዶ/ር)፥ ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ የሚወከሉ የፓርቲና የመንግሥት ኃላፊዎች፣ አስተዳዳሪዎችና ቢሮክራቶች ከድሃው ሕዝብ ላብ ተቀንሶ ከሚሰበሰብ ግብር የሚከፈላቸው በመሆናቸው፣ በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃ የሚገኙ ሹመኞች የሕዝብ አገልጋይ ሆነው የመሥራት ግዴታ እንደሚኖርባቸው ቢታወቅም፣ በዚህ ደረጃ በአገራችን ሥር የሰደደ ችግር በመኖሩ ፓርቲያቸው ለዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መምጣቱን ይጠቁማሉ።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት፣ አገራዊ መግባባትን ለማጠናከር፣ ጤናማ የፖለቲካ ውድድርን እውን ለማድረግ እንደሚሠራም ፕሮግራማቸው አስቀመጧል።

የአንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የፖለቲካ ሥልጣን ትልቁና የመጨረሻ ግብ አገርንና ሕዝብን ማገልገል እንደሆነ የነገሩን መሐመድ፣ ሕዝብን እንዲያስተዳድሩ የሚወከሉ የፓርቲና የመንግሥት ኃላፊዎች፣ አስተዳዳሪዎችና ቢሮክራቶች ከድሃው ሕዝብ ላብ ተቀንሶ ከሚሰበሰብ ግብር የሚከፈላቸው እንደመሆናቸው፣ በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃ የሚገኙ የድርጅታቸው አባላት የሕዝብ አገልጋይ ሆነው የመሥራት ግዴታ እንደሚኖርባቸው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here