‘ባላደራው’ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ከነዋሪው የተለየ አቋም ያለው ፓርቲ እንዳይመረጥ እሠራለሁ አለ

0
493

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ አለው የሚባለውን ልዩ ጥቅም አስከብራለሁ የሚል ማንኛውም ፓርቲ በከተማዋ ነዋሪዎች እንዳይመረጥ ለማድረግ እንደሚሠራ ʻየአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤትʼ ገለጸ።

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው ብሎ በማመን ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚሠራው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አቋሙን ካልቀየረ በቀጣዩ ምርጫ አይመረጥም የሚል እምነት ያለው ምክር ቤቱ፥ ይህ መሰሉ አቋም ያለው የትኛውም የፖለቲካ ኃይል በመጪው ምርጫ እንዳይመረጥ በሰላማዊ መንገድ ሕዝቡን የመቀስቀስና የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰራ ገልጿል።

የባለአደራ ምክር ቤቱ አባል እስክንድር ነጋ በመጪው ምርጫ በግሉም ሆነ ምክር ቤቱ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልፆ ዋነኛ ኃላፊነታቸውም በመጋቢት 1 ዱ የባልደራስ ስብሰባ ነዋሪውን ወክለው ጥያቄ እንዲያቀርቡ በተነሱላቸው ነጥቦች ላይ ምላሽ ለማግኘት እንደሚሠሩ አሳውቋል።

ባለአደራው መጋቢት 25/2011 በሰጠው መግለጫ የትኛውም ብሔር ወይም ክልል በአዲስ አበባ ላይ ምንም ዓይነት የልዩ ጥቅም ጥያቄ እንደሌለውና ከተማዋም የነዋሪዎቿ እና የመላው ኢትዮጵያዊያን መሆኗን ያምናል። በመሆኑም ይህንኑ ማረጋገጥ የመጀመሪያው ኃላፊነት መሆኑን አስታውቋል።

˝የትኛውም ፓርቲ፣ ተፎካካሪዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ የሚያስጠብቅ ከሆነ በቀጣዩ ምርጫ ላይ እንዳይመረጡ የመቀስቀስ ኃላፊነት ኮሚቴው እንዳለበትና ይህም ከሕዝቡ የተሰጠው አደራ መሆኑን˝ እስክንድር ተናግሯል። ይህም መጋቢት 1/2011 በባልደራስ በይፋ ኮሚቴው ሲመሰረት ሕዝቡ ˝በሚቀጥለው ምርጫ ልዩ ጥቅም የሚል ሐሳብ ይዞ ለሚመጣ ፓርቲ የአዲስ አበባ ሕዝብ ድምፅ እንዳይሰጥ˝ የሚል ውሳኔ ከወቅቱ ተሳታፊዎች መተላለፉን ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል። ይሁንና ይህ የሚሳካው በነዋሪው ፍላጎት መሆኑም ተመልክቷል።

ባለአደራው ይህን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት መቀበሉን ያነሳው እስክንድር፤ ˝ይህንም ተከትሎ ከሕዝቡ የተቀበልነውን ኃላፊነት እስከ ሕይወታችን ፍፃሜ ከግብ እናደርሳለን ሲል˝ ተደምጧል።

በተያያዘም ባለአደራ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደርና ወሰን ድርድር የሚቀጥለው ምርጫ ተደርጎ በሕዝብ የተመረጡ ሰዎች እስኪረከቡት ድረስ እንዲቆምም አቋም ይዟል።

˝የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም መቃወም ሕገ መንግሥቱን መቃወም አይሆንም ወይ?˝ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ እስክንድር ˝መጀመሪያውኑ ሕገ መንግሥቱ የማን ነው?˝ የሚለው መፈተሸ እንዳለበት ይጠቅሳል። በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በፀደቀበት ወቅት የሕዝብ ተሳትፎ እንዳነበረበት ይልቁንም በሕወሓት የበላይነት እንደተዘጋጀም ያምናል።

ከምክር ቤቱ ሕጋዊነት ጋር ተያይዞ ለሚነሳበት ጥያቄ አሁን ላይ በመንግሥት በኩል የሕግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ በመሆኑ አዲስ የሚመሰረቱ የሲቪል ማኅበራትም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በሚሔዱበት አግባብ እየተጓዘ እንዳለ በማስታወስ በመንግሥት በኩል ሚሰነዘርበት ወከባ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል። የሚነሳቸው ትያቄዎችም ነዋሪው ያሉትን ትያቄዎች በመሆኑ መንግሥት ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባው ጠይቋል። ምክር ቤቱ በመጋቢት 1ዱ ስብሰባ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው ለአዲስ አበባ ከንቲባ እና ጠቅላይ ሚንሥትር ጽሕፈት ቤቶች ጥያቄዎቹን በጽሑፍ ቢያቀርብም እስካን ምላሽ አለማግኘቱንም አሳውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here