8 ድርጅቶች 245 መኪኖችን የሚይዝ የመኪና ማቆምያ ለመገንባት እየተወዳደሩ ነው

0
542

– በከተማዋ እየጨመረ የመጣውን የመኪና ማቆምያ እጥረት በመጠኑም ቢሆን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል

በአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ 3 ሺሕ 600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 245 መኪኖችን የሚይዝ የመሬት ውስጥ የመኪና ማቆምያ ቦታ ለመገንባት ስምንት ድርጅቶች እየተወዳደሩ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት አስታወቀ።

በአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መጋቢት 12 በተከፈተው ጨረታ 37 ድርጅቶች የጨረታ ሰነዱን ሲገዙ የመወዳደሪያ ሰነዱን አስገብተው ለውድድር ከቀረቡት ስምንት ድርጅቶች ውስጥ ተክለ ብርሀን አምባዬ ኮንስትራክሽን፣ ዩናይትድ ኮንስትራክሽን፣ ዛምራ ኮንስትራክሽን፣ ኤቲኤስ ኢንጂነሪንግ፣ ታወር ፒ.ኤል.ሲ፣ ሰለሞን ጥላሁን ሕንፃ ሥራ ተቋራጭ፣ አሺቱ ኢንጂነሪንግ እና ቻይና ቲስሲጂ የሲቪል ኢንጂነሪን ግሩፕ ተሳትፈውበታል።

ውድድሩን ለመጀመር ሰነዱን ካስገቡት 10 ድርጅቶች ውስጥ ብራይት ኮንስትራክሽን እና ኤን ኬ ኤች ኮንስትራክሽን የጨረታ መዝግያውን ሰዓት አሳልፈው በመምጣታቸው ከጨረታው ተሰርዘዋል።

የኮንትራት አስተዳደር የግንባታ ክትትል ዳይሬክተር ሰለሞን ዓለሙ እንደገለፁት አንድ አሽከርካሪ ደኅንነቱ የተጠበቀ ማቆምያ ለማግኘት ብቻ ከመነሻ ቦታው ተነስቶ ብዙ ኪሎ ሜትር ይሽከረከራል። በመሆኑም በከተማዋ በብዛት የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ እና የመኪና ማቆምያ ችግር ለመቅረፍ ከዚህ በፊት መገናኛ እና አንዋር መስኪድ ጋር መኪና ማቆሚያዎቹ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ዋቢ ሸበሌ ሆቴል እና ቸርችል ሆቴል ጋር እየተገነቡ ያሉት የመኪና ማቆሚያዎች በቅርቡ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ። እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ከተገነቡት የመኪና ማቆሚያዎች በተጨማሪ ቦሌ ቢር ጋርደን አካባቢ እና ካሳንቺስ ቶታል አካባቢ በቅርቡ የመኪና ማቆሚዎች ሊገነቡ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የጋራ መኪና ማቆምያ ቦታ በተለየ ሁኔታ የመኪናውን ደኅንነት የሚጠብቅ እና በከተማዋ ላይም የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር ከማድረጉም ባሻገር በመኪና ማቆምያ ውስጥ የሚኖረውን ብክለት ለመቀነስም የተለየ ጥቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ለግንባታውም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊደረግ እንደሚችል ይገመታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here