ውርድወት ነሽ?

0
459

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ቢቢሲ አማርኛ በቅርቡ ባስነበበው ዘገባ የተለያዩ ጥናቶችን መሰረት አድርጎ እንዳሰፈረው፤ በርካታ ሴቶች ʻፌሚኒስትʼ ተብሎ መጠራትን አይወዱትም። የሚገርመው ይሔ አይደለም፤ ዘገባው እንዳጣቀሰው ጥናት ከሆነ ለሴቶች መብት ቀንደኛ ተሟጋች የሆኑ ሴቶችም ʻፌሚኒስትʼ እንዲባሉ አይፈልጉም። ወደ አገራችን መለስ ስንል ደግሞ ቃሉን ፈፅሞ መስማት እንኳን የማይሹ አሉ።

ʻፌሚኒዝምʼ የጾታ እኩልነትን መሠረት ያደረገ የሴቶች መብት ጥያቄ ወይም የሴቶችን መብት ለማስከበር የሚደረግ እንቅስቃሴና የተከናወነ ንቅናቄ መጠሪያ ነው። ይህን እንቅስቃሴ የተቀላቀሉ ሰዎች ናቸው እንግዲህ ፌሚኒስት ወይ መደበኛ ባልሆነ አተረጓጎም ʻየሴትነት አቀንቃኝʼ የሚባሉት።

ሥያሜውን የሚጠሉት ጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ይልቅ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና አነስተኛ ገቢ ያለው ሥራ ላይ የተሠማሩት ናቸው። ከዛም ባለፈ ነባር አስተሳሰቦች ባለመቀየራቸው ነው ይላል ጥናቱ። ይህም በ1920ዎቹ ፌሚኒስት የተባሉ ሴቶች ትዳር ያልቀናቸው፣ ወንድ የሚጠሉ፣ በወሲብ ምርጫቸው አፈንጋጭ የሆኑና ወንዳወንድ ተደርገው መቆጠራቸው ዛሬም ድረስ ዘልቆ ቆይቷል።

˝በኢትዮጵያስ? ̋ በዚህ ረገድ በእኛም ዘንድ የአውሮፓውያኑ የ1920ዎቹ አስተሳሰብ አለ። ደግሞም እንደቀሪው የአፍሪካ አንድ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የʻፌሚኒዝምʼ አቀባበል የተደበላለቀ ነው። ለሴቶች መብት ተሟጋችና ጠበቃ የሆኑ ነገር ግን ʻፌሚኒስትʼ መባልን የማይፈልጉ ሰዎችን እናውቃለን። ˝ሥያሜውን ለምን አንወደውም? ̋ ብዙዎችስ ʻፌሚኒስት ነኝʼ የሚልን ሰው ̋በደኅና ነው?˝ በሚል አስተያየት ለምን ያዩታል? ለምን እንደቅንጦት እንጂ እንደሰው ልጅ የመብት ጥያቄ አልተቆጠረም?
በአገራችን የሴቶች መብት ትግልና ጥያቄ ዛሬ በʻፌሚኒዝምʼ የጀመረ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ባይልልን ለራሳችን ጀግኖች የምንሰጠው ደረጃ ዝቅ ያለ በመሆኑ እንጂ፤ እንደው በጥበብ መድረክ በመቅረቡ ትኩረትን ያገኘው የውርድወትን /የቃቄ ውርድወት/ ትግል ማንሳት ይቻላል። እንደውርድወት ያሉ ሴቶች እንግዲህ ፌሚኒስት እንደነበሩ ልብ ይሏል።

ምንአልባት ስያሜ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለበትም ይሆናል፤ ነገር ግን ስም ወካይ መሆኑ አይቀርም። እናም ፌሚኒስት ነኝ ብላ ንግግሯን የምትጀምር ሴት ምን ያህል ሰሚ አላት? ለውጥ ለመፍጠርና ለማምጣት መጀመሪያ ተቀባይነት ያስፈልግ የለ? እኔ የምለው፤ ለምሳሌ ከውርድወት በላይ ለሴቶች መብት የታገለ እስክናውቅ ድረስ ˝ውርድወት ነሽ?˝ ብንባባልና ትግሉን አገርኛ ብናደርገው፤ ቅቡልነቱም ይቸግረናል?

በጨለማ ለሚደፈሩ፣ ባመኑት ሰው ጥቃት ለሚደርስባቸው፣ ሕግ አለሁ ለማይላቸው፣ ማኅበረሰብ ለሚፈርድባቸው፣ አትችሉም አታውቁም ለሚባሉ ሴቶች የሚደረገው ትግል ቀልድ አይደለም። የሰብኣዊነት ጉዳይ ነውና የሴቶች መብትና ጥያቄ በአገራችን ለውጥ እንዲያመጣ፤ መጀመሪያ ማኅበረሰቡ የእኔ ሊለው ይገባል። እናስ ከሥሙ ብንጀምር ለማለት ሁሌም አስብ ነበርና አሁን አልኩት…የጣይቱ ብጡልና የቃቄ ውርድወት አገር ላይ ነን’ኮ!

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here