ሱዳን ለ2 ዓመት በአገሪቱ ጦር ትመራለች

0
507

ከሰኔ 23/1981 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የቆዩት የሱዳኑ ፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽር ከአራት ወራት ጠንካራ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ጦር ኮሚቴ ሱዳንን ለኹለት ዓመት እንደሚመራ አሳወቀ።

ከአራት ወር በፊት በሱዳን የዳቦ ዋጋ በሦስት እጥፍ መጨመሩን ተከትሎ ተቃውሞ ያነሱት ሱዳናዊያን ቀስ ብለው ጥያቄውን ወደ ጥቅል ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ እና አልበሽር ከሥልጣን ይውረዱ ወደሚል ከፍታ መውሰዳቸው ይታወሳል።

ፕሬዘዳንቱ ተቃውሞውን ለማፈን ካቢኔያቸውን በትነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ቢያውጁም ሊሳካላቸው አልቻለም። ይልቁንም ሐሙስ ሚያዚያ 3 በወታደራዊ ኃይል መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎባቸው ሥልጣናቸውን ተነጥቀዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱ በአገሪቱ ሁሉም ጦር የተናበበ አካሔድ መከወኑ የተገለፀ ሲሆን አልበሽር በፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ ስር ወድቀዋል። የተለያዩ ባለሥልጣናትም እየተሰሩ ነው።

የአገሪቱ ጦር ለቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት ሱዳንን በሽግግር መንግሥት ለመምራት ከመወሰኑም በላይ ለሦስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አውጇል። ይህም ተቃውሞውን ለወራት በአስተባባሪነት ሲመራ የቆየውን የሱዳን የባለሙያዎች ምኅበር ያስቆጣ ሲሆን ሕዝቡ በተቃውሞው እንዲገፋም እየጠየቀ ነው።

የአልበሽር አስተዳደር በአሜሪካ ለረጅም ዓመት ተጥሎበት የነበረው ማዕቀብ ቢነሳለትም እዚህ ግባ የሚባል የምጣኔ ሀብት ማንሰራራት ባለማሳየቱ በዜጎቹ በኩል ጥርስ ውስጥ ገብቶ ከርሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here