ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ምፅዋ ላይ ትመሰርታለች መባሉን ኤርትራ አስተባበለች

0
719

ኢትዮጵያ አዲስ የምታቋቁመውን የባሕር ኃይል በኤርትራ ምፅዋ ትመሰርታለች መባሉን የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል አስተባበሉ።

የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንደገና ለማቋቋም በፀደቀው አዋጅ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እንዲኖራት መፍቀዱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ፈረንሳይ በኤርትራ የሚቋቋመውን የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል በመመስረት እንደምትሳተፍ ኤርትራ ፕሬስ ዘግቧል። መረጃውን ያሰፈረው የመገናኛ ብዙኃን አውታሩ የጅቡቲው ፕሬዘዳንት እስማኤል ዑማር ጉሌህ መረጋገጫው እንደሆኑም አክሏል። የማስታወቂያ ሚንስትሩ ግን ‹‹የጂቡቲው ፕሬዘዳንት ከመቼ ወዲህ ነው የኤርትራ ቃል አቀባይ የሆኑት በማለት ውሸት ነው›› ብለዋል።

ፕሬዘዳንት ዑመር ጉሌህ ከፈረንሳዩ ጂዩን አፍሪክ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል እንደምትገነባ መግለፃቸው ታውቋል። የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለጂቡቲው መሪ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ግንባታ እንደምታከናውን መናገራቸውን ነው መጽሔቱ ጽፏል የተባለው።

የፈረንሳይ ድጋፍ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ ኃይልና ምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎች ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደምትፈልግ ማሳያ እንደሚሆን የገለፁት ማክሮን፣ የባሕር በር አልባዋን አገር ኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በምፅዋ የማቋቋሙ ስምምነት በኤርትራ መንግሥት ይሁንታ ላይ መመስረቱንም አክለዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የፈረንሳዩ መሪ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በወታደራዊ ኃይል ለመተባበር መስማማታቸው እንዳስደሰታቸው መግለፃቸውንም ዘገባው አስታውሷል።

በተመሳሳይ ዜና ኢትዮጵያና ጣሊያን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ረቡዕ ሚያዚያ 2 ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here