የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል ሊገነባ ነው

0
763

በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለለት የድንገተኛ አደጋ ህክምና መስጫ ሆስፒታል በአለርት የህክምና ማዕከል ሊገነባ ነው።
በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን ድንገተኛ አደጋ ታሳቢ በማድረግ ሆስፒታሉን መገንባት እንዳስፈለገ ያሳወቁት የጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን ሆስፒታሉን ከሚገነባው እቴቴ ኮንስትራክሽን ጋር ረቡዕ ሚያዚያ 2 የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሆስፒታሉ 800 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ የመንግሥት ወጪ እንደሚገነባ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፃቸው ያስነበቡት ሚንስትሩ፣ ባለ ስምንት ፎቅ እንደሆነም አመልክተዋል።

ይሁንና የሆስፒታሉ ንድፍና ሚንስትሩ ባለ 8 ፎቅ እንደሆነ ቢያመልክቱም በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን በኩል ባለ 12 ፎቅ እንደሆነም ሲዘገብ ተስተውሏል።

ሆስፒታሉ ከ500 በላይ የሚሆኑ አልጋዎች የሚኖሩት ሲሆን በቀን ከኹለት ሺሕ እስከ አምስት ሺሕ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድም ተነግሮለታል።

በ3 ዓመት ግንባታውን ለማጠናቀቅ ውል የተገባለት ሆስፒታሉ የደም ባንክ አገልግሎትን ጨምሮ ሁሉምንም የምርመራ መሣሪያዎች የሚያሟላ እንደሚሆንም ሚንስትሩ ተናግረዋል።

የአደጋ ጉዳት ላይ አትኩሮ ይሰራል የተባለው ሆስፒታሉ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ይባል እንጂ ከዚህ ቀደም በጳውሎስ ሆስፒታል ስር ተገንብቶ አገልግሎት የሚሰጠው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የሕክምና ማዕከል ወይም በምህፃሩ ‹‹አቤት›› የሚሰኘው ማዕከልም ከድንገተኛ አደጋዎች ጋር የተያያዙ ህክምናዎችን የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል።

በተመሳሳይ ዜና በአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ የህፃናት ሆስፒታልን በአዲስ አበባ ለመገንባት የጤና ሚንስቴር ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር ተስማምቷል። በአለርት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የሚገነባው ሆስፒታሉ በኔዘርናልድ መንግሥት ድጋፍ የሚሰራ ነው ተብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here