2 ጊዜ ተጀምሮ የተቋረጠው የፅዳት ዘመቻ ለ3ኛ ጊዜ ነገ ይጀመራል

0
439

ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት ኹለት ጊዜ በመሪዎች ተጀምሮ የተቋረጠው የፅዳት ዘመቻ ነገ ሚያዚያ 6 ለ3ኛ ጊዜ እንደሚጀመር ተገለፀ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት እሁድን በመልካም ተግባር ለመጀመር ሲባል በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በኅብረት ሊያፀዱ ይገባል። ይህን ተከትሎም ነገ ሚያዚያ 6 ጠዋት ከ1፡30 ጀምሮ ሁሉም ሰው አካባቢውን እንዲያፀዳ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ለኑሮ የተመቸ አካባቢን ለመፍጠር ሁሉም በፅዳት ዘመቻው ይሳተፍ ዘንድ መክረዋል።

በዘመቻው በአዲስ አበባም ይሁን በሌሎች ከተሞች የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ዐቢይ አህመድ ቆሻሻን ከማፅዳቱ ጋር መጥፎ እሳቤን ከአዕምሮ ማፅዳት እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ በ2008 የከተማዋ ከንቲባ በነበሩት ዲሪባ ኩማ ወርሀዊ የፅዳ ዘመቻ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ መቋረጡ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ዘመቻው ዘላቂ እንዲሆን በሚል በ2010 መጀመሪያ ወራት ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩት ኃይለማሪያም ደሳለኝ በየወሩ የመጨረሻው ሳምንት የሚካሔድ የፅዳት ዘመቻ ተጀምሮ ነበር። ይህም ዘመቻ ከኹለት ወራት ተግባር በኋላ ተቋርጧል።

ኢትዮጵያ በፅዳቱ ዘርፍ በተደጋጋሚ ተሞክሮ ለመቅሰም በሚል ወደርዋንዳ ኪጋሊና ወደ ደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተሞች ልዑኮችን ስትልክ ስለመኖሯ መረጃዎች አሉ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የርዋንዳን የዘር ማጥፋት አስከፊ ሁነት 25ኛ ዓመት ሳምንት ለመታደም ርዋንዳ እንደነበሩ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here