የኹለቱ ዶክተሮች ወግ

0
828

በኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት የግለሰብ አሸናፊ ሳይሆን የፓርቲ አሸናፊ ብቻ እንደሚኖር ያስታወሱት ጌታቸው መላኩ በቀጣዩ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፓርቲያቸውን በማዋሐድ ይህንን ዕድል ለማስፋት ሲሞክሩ፥ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ደግሞ በተቃራኒው የፌዴራል ስርዓቱ ባለበት እንዲቀጥል በመጠየቅ የማሸነፊያ ዕድላቸውን ሊያሰፉ ይሞክራሉ ይላሉ።

‘የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል’ ይላል ተረቱ። በአንድ አጋጣሚ አንድ ወዳጄ ከዚህ ተረት ጋር በትርጉም የሚዛመድ በተለይ ደግሞ አሁን ለማነሳው ሐሳብ የሚመጥን የኦሮምኛ አባባል ነግሮኝ ነበር። ምን ያደርጋል ረሳሁት። ለማንኛውም ብዙ ወዳጆቼ እንደሚያስታውሱኝ ተስፋ አለኝ።

ይህንን ለማለት ያነሳሳኝ የኢሕአዴግ መሥራች አባል ድርጅቶች ባለፉት ኹለት ዓመታት በተለይ ልዩነታቸው በግልጽ አፍጦ እየታየ መቀበል ስለተሳናቸው ብቻ እየተሰበሰቡ “ሁሉ ሰላም ነው”፣ “ድርጅታዊ አንድነታችን የበለጠ ተጠናከሯል” እያሉ ማንን እያሞኙ እንደሆነ ባልገባቸው መልኩ ሲናገሩ ጊዜው ነጎደ።

አብዛኛው በተለይ “አብዮት” የሰለቸው፣ ግድያና መባረር የመረረው በኢሕአዴግ ክፍፍልም ይሁን ልዩነት የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መምጣትን እንደ ፈጣሪ ሥጦታ ነበር የተቀበለው። ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭው ዓለም፣ መላ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ደስታም ተስፋም ታይቶታል። አሁን ባለንበት ጊዜ በሚታዩት ክስተቶች እንዳንዶች ትንሽ ሥጋት እንደገባቸው ባይሸሽጉም፣ ተስፋቸው ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ላይ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በተለይ በነበረው የፖለቲካ ስርዓት ጫና አገራቸውን ለቀው ተሰደው የነበሩ ብዘኀን ወደ አገራቸው መግቢያ ቪዛ የሆኑላቸውን ዐቢይን የፈጣሪ መልእክተኛ አድርገው ሲስሏቸው ሰንብተዋል። የለመደብን አፍላ ቡረቃ (‘Early fantacy’) ይሁን ሌላ ባይረጋገጥም።

በዚህ ሁሉ ተስፋ መሐከል ባለፈው ድፍን አንድ ዓመት በአገራችን የነበረው አለመረጋጋት የማይቀር “የለውጥ ዋዜማ ጣር” አድርገው ለማስረዳት የሚጥሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ለውጡን (አንዳንዶች የመጣው ለውጥ አይደለም ብለው እንደሚከራኩ ሳንዘነጋ) በብቃት የመምራት ክፍተት ነው ሲሉ ይሰማል።

በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት አለመረጋጋቱ ያስከተለውን የሚያሳቅቁ መፈናቀል ዜናዎችን በሰፊው የሰማንበት ነበር። ይህም በአገራችን ታሪክ እጅግ አሳሳቢ የሆነውን ከ8 ሚሊዮን በላይ የውስጥ ተፈናቃይ አስከትሎብናል። ስደተኞችን በመቀበል ኩራት ኩራት የሚላትን አገር አንገት ያስደፋ ጉዳይ ሆኗል።

ሌላው ትኩሳት የአዲስ አበባ መጤ፣ ሰፋሪ፣ ነዋሪ እና ባለቤትነት ጉዳይ በቅርቡ እየናጠን ያለፈ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም የምጣኔ ሀብቱ ሁኔታ ክፉኛ መንገዳገድ፣ የሹመቱና ሽልማቱ ግራ አጋቢነት ጉዳይ ወዘተ. በስሜት ሲንጡን የቆዩ ጉዳዮች ሆነዋል።

መናጣቸውንም ቀጥለውበታል። ይህ ጉዳይ በአብዛኛው ትኩረታችንን ሲንጠው ምን ያህል ስሜታዊና ጥራዝ ነጠቅ እንደሆንን የተገነዘብንም ይመስለኛል። ምክንያቱም ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊኖራቸው የሚችል ጉዳዮችን ምን ያህል እንደዘነጋናቸው ሳስብ በዚህች ደሀ አገር (በሀብትም፣ በአስተሳሰብም ማለቴ ነው) አርቆ ማየት ችግር እንደሆነብን እየተገነዘብንም ይመስለኛል። የአገራችንን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት፣ እንዲሁም የወደፊት ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን ወሳኝ ስለሆነው ጉዳይ መመልከት ሲሳነን አስተውለንማል። ዛሬ ላይ ተንጠልጥሎ የራሱን ትክክለኛነት የሌላውን መሳሳት በጉንጭ አልፋ ክርክር ሊያሳስብ የሚፈልግ ስንት ሰው ታዘብን? አገር እኮ ዛሬ ብቻ፣ አሁን ብቻ፣ እኔ ብቻ አይደለም። ነገም አለ፣ ሌሎችም አሉ። ትውልድም ይቀጥላል።

ከዚህ በተለየ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከምንምና ከየትም (ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ማለቴ ነው) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያነሷቸው አገራዊ ፓርቲዎች የመቋቋማማቸውን አስፈላጊነት ጉዳይ ትኩረታችንን ለምን እንዳልሳበ፣ በተለይ ጸሐፍት ወዳጆቻችን በሚጠበው ያህል እንዳልተንቀሳቀሱ አልገባኝም። እኔ ይህ ጉዳይ ከሌሎች ጉዳዮች አንፃር ሊተኮርበት ይገባል ባይ ሆኛለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከእንግዲህ የኦሮሞ ፓርቲ፣ የአማራ ፓርቲ፣ የሶማሌ ፓርቲ ወዘተ. የሚባል አይኖርም፤… እንደ አንድ አገር ዐቀፍ ፓርቲ ማቋቋም አለብን” እያሉ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲናገሩ ብዙዎች በጭብጠባ ድጋፋቸውን ሲገልጹላቸው ተመልክተናል።

በሌሎች መድረኮች ደግሞ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በኢትዮጵያ የፌደራላዊ ስርዓት ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ይደመጣል። እንግዲህ ‘የእነዚህን ዓይነት ጉዳዮችን የምንከታተልበት አስተውሎት ምን ይመስላል?’ ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ሆኖ ይታየኛል። ለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‘አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም አለብን’ የሚለው ሐሳብና መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ‘የፌደራሊዝሙ፣ በተለይ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝሙ ጉዳይ መቀጠል አለበት’ የሚለው ዕሳቤያቸው ምን ማለት ይሆን? የአጭርና የረጅም ጊዜ፣ እንዲሁም በግልጽና፣ በኅቡዕ ያለው ፍላጎታቸውስ ምን ይሆን? እኔ ይህ ይመስለኛል።

ብርሀኑ ነጋ (ዶ/ር) በቅርቡ ለኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክ በሰጡት ቃለ ምልልስ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማም ሆኑ እነ ዐቢይ አሻጋሪዎቻችን ናቸው። ስለዚህ የያዙት ሥራ በራሱ ከባድ ስለሆነ ተጨማሪ ጉዳይ እያነሳን ባናስቸግራቸው የሚል አንድምታ ያለው ሐሳብ ሰንዘረዋል። ይህም የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት የሚባለውን በእነ እስክንር ነጋ የተቋቋመውን አካል አግባብነት በሞገቱበት ሐሳባቸው ያነሱት ነው። ለዚህ ጽሑፍ ግን በጣም ትኩረት ሳቢ ቃል “አሻጋሪዎቻችን” የምትለው ትመስለኛለች። ብርሀኑ ነጋ (ዶ/ር) ግልጽ ባያደርጉትም የምንሻገርበት የስርዓት ዓይነት ዘወትር ከሚባለው ከዴሞክራሲዊነት ባሻገር ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰቡ ጊዜው አሁን ይመስለኛል።

የዐቢይ አመጣጥ ምንም ዓይነት ትንቢት ቢሰጥበት፣ ተምኔት ቢወጠንለት የሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ከጊዜው ጋር መለወጥ ያለመቻል ክፍተት እንደሆነ የማያሻማ ሐቅ ይመስለኛል። ብዙዎች እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወደ ሥልጣን ያመጣው የመሪ ድርጅታቸው ድክመት፣ የእሳቸው ጥንካሬ ሆኖ ሊቆጠር አይችልም። በተለይ በርካቶች እንደሚከሱት እንዲውም ዐቢይ በመሪ ድርጅታቸው ድክመት ኀላፊነት ሊወስዱ የሚገባቸው ግለሰብ ናቸው። ግለሰቡ ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን ኢሕአዴግ ያለፈበትን ጊዜ የተገነዘቡ በመሆናቸው ቅቡልነታቸውን ይቅርታ በመጠየቅ ገንብተው ሥልጣናቸውን አደላድለዋል። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቅቡልነት ምን ያህል ስርዓት ተኮር (system based) ነው የሚለው አጠያያቂ ይመስላል።

ይህንን ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገባ የተገነዘቡት ይመስላል። ለዚህም ነው ሁላችንም የዘነጋነውን ጉዳይ አንስተው ለወደፊት ምርጫ የሚፈይድላቸውን ሥራ እየሠሩ የሚመስሉት። በእኔ ግንዛቤ አንድ ግልጽ ጉዳይ ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ምርጫ እንደግለሰብ በመወዳደሪያ ክልላቸው ሊያሸንፉ ይችላሉ። የምክር ቤት አባልም መሆን ይችላሉ። ይህ አሸናፊነታቸው ግን የመሪነት ሥልጣናቸውን ሊያረጋግጥላቸው አይችልም። ቀላሉ ምክንያት ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ስለማያሸንፍ ነው። በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት (ቀጥተኛ ያልሆነ ውክልና ማለቴ ነው) አሸናፊ ፓርቲ እንጂ አሸናፊ ግለሰብ የለም። በመሆኑም ዐቢይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ወይም በሌላ አግባብ የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን ይዘው ለመቀጠል የሚችሉበት ዕድል ጠባብ ነው።

በዚህ ሐሳብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ መሪነት የመምጣት ዕድል አብላጫ ወንበር በፓርላማ የሚኖረው ተቃዋሚ እንደግለሰብ ይሁንታ ከሰጣቸው ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የማይጠበቅ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ያላቸው አማራጭ አገር ዐቀፍ ፓርቲን መርተው ዳግም ወደ ሥልጣን በመምጣት ወይም በቀጥታ ዲሞክራሲዊ ምርጫ (direct representation) ወደ ሥልጣን መምጣት ተጨማሪ ቅቡልነት (added legitimacy) መፍጠር አለባቸው። ኹለተኛው የምርጫ ሕግን መቀየር የሚጠይቅ ጉዳይ ስለሚሆን ቢያንስ ባለው አጭር ጊዜ የሚቻል አይመስልም።

መረራን የመሳሰሉ ፖለቲከኞች የፌደራሊዝም በተለይ ደግሞ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች የበዙበትን የፓርቲ ስርዓት የአገሪቱ ሕልውና መሠረት አድርገው ሲያቀርቡ ይስተዋላል። ጉዳዩና ዓላማው ምንም ይሁን ምንም እነዚህ አካላት ወደ ሥልጣን ሊመጡበት የሚችሉበት መንገድ ይህ ብቻ እንደሆነ የሚያምኑ ይመስላል። ከላይ እንደተመለከትነው ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ያለውን ቅቡልነት በማጣቱ ምክንያት ዐቢይና ቡድናቸው ሌላ መንገድ እንደሚፈልግ ሁሉ፣ የእነመረራ ፓርቲና መሰሎቻቸው ኢሕአዴግ የሚያጣውን ድጋፍና ድምፅ በዚህ አግባብ ለመውሰድ እንደሚችሉ ያመኑ ይመስላል። ይህ እምነታቸው እውን ይሆን ዘንድ ምኞታቸውን አጠንክረው በሥራ ላይ ያለው ብሔር ተኮር የፌደራል ስርዓት እንዲቀጥል የመሟገታቸው ምስጢር ተንታኝ የሚያስፈልገውም አይመስልም፤ ምክንያቱም የኢሕአዴግ መገፋት ለእነርሱ ዕድል ይፈጥር ይሆን ይሆናል ብለው ያስባሉና።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here