የዲቴል ጋላፊ መንገድ በመበላሸቱ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ታወቀ

0
1000

በጁቡቲ መንግሥት የሚተዳደረው የዲቴል ጋላፊ መንገድ በመበላሸቱ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንና ኮንቴነር ለጫኑ ተሽከርካሪዎችም የአደጋ መንስኤ እየሆነ መሆኑ ታወቀ። ይህ መንገድ ብልሽት ካጋጠመው ከ3 ዓመት በላይ የሆነው ሲሆን ወደ ጉድጓድነት በመቀየሩ ኮንቴነር የጫኑ መኪኖች የመገልበጥ አደጋ እየገጠማቸው መሆኑንና ጎማቸውም እየፈነዳ ለቀናት እንደሚቆሙ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ትራንስፖርት ኅብረት አስታውቋል።

ከሌሎች ጎረቤት አገሮች አንፃር ሲታይ ለመሐል ኢትዮጵያ ቅርብ የሆነው የጂቡቲ ወደብ ቢሆንም፣ በተለይ ከወደቡ እስከ ጋላፊ ድረስ ያለው 200 ኪሎ ሜትር መንገድ በመበላሸቱ፣ የተሽከርካሪዎችን ምልልስ ከማስተጓጎሉም በላይ፣ ለአላስፈላጊ የመለዋወጫ ዕቃዎች ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ትራንስፖርት ኅብረት ሊቀመንበር ብርሃን ዘሩ አስታውቀዋል። ችግሩ እንዲቀረፍ ለትራንስፖርት ባለሥልጣን በጊዜው ቢያሳውቁም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊገኙ እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከጂቡቲ አዲስ አበባ ድረስ ያለው ርቀት 907 ኪሎ ሜትር ነው። ከቅርበትና ከሌሎች ኢኮኖሚ ማኅበራያዊ ጉዳዮች በመነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት 85 በመቶ የገቢና ወጪ ዕቃዎችን የሚያመላልሰው በጅቡቲ ወደብ በኩል ቢሆንም፣ በተለይ ከጅቡቲ ወደብ የድንበር ከተማ እስከሆነው ጋላፊ ድረስ ያለው 200 ኪሎ ሜትር መንገድ በመበላሸቱ፣ ምልልሱን እያስተጓጎለ መሆኑን የጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ገልጸዋል።

መንግሥት የትራንስፖርት ምልልሱን ከስድስት ቀናት ወደ ሦስት ወይም አራት ቀናት ለማሳጠር ቢያቅድም ይህ ሊሆን ግን አልቻለም ሲሉ ብርሃን ተናግረዋል። በተለይ በጅቡቲ ክልል ውስጥ እስከ ጋላፊ ድረስ ያለው መንገድ እጅግ በመበላሸቱ ምልልሱ ከመስተጓጎሉ ባሻገር፣ ተሽከርካሪዎች ዕቃ እየሰበሩ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ እንደሆነ በማንሳት ብርሃኑ የችግሩን ውስብስብነት አስረድተዋል።

ይህ መንገድ ከተበላሻ ከሦስት ዓመት በላይ ቢሆንም፣ ያለምንም ጥገና የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች እየተመላለሱበት ነው። ይህንን መንገድ የመጠገን ኃላፊነት የጅቡቲ መንግሥት ቢሆንም መጠገን ባለመቻሉ የሚመለከታቸው ተዋናዮች ለመንግሥት ቅሬታ እየቀረቡ መሆኑ ታውቋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሙሴ ይሄይስ፥ መንገዱ የሚገኘው በጁቡቲ በኩል በመሆኑ ከሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው የመመለከታቸው ኃላፊዎች ቦታውን ሔደው መጎብኘታቸውን እንዲሁም ጁቡቲ በቅርቡ በተካሔደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በሚኒስትር ዳግማዊት አማካይነት እንዲጠገንና መፍትሔ እንዲሠጥ ጥያቄ ለጁቡቲ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቀርቦ ውይይት መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here