ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮች እንደ አማራጭ

0
887

ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች መጠቀምን የሚያስገድደው አረንጔዴ የልማት አቅጣጫ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሆነ ለአፍሪካ ይበጃል ወይ የሚለውን ጥያቄ በማንሳት፥ ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ወሳኙ መፍትሔ በከፊልም ቢሆን ከፍተኛ ወጪና የተማረ የሰው ኃይል ወደማይጠይቁት ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን ፊታችንን ማዞር ነው በማለት ሳምሶን ኃይሉ ይሞግታሉ።

 

በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ 80 ከመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ዝቅተኛ ምርታማነት ባለው በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ግብርና ከጠቅላላውን ኢኮኖሚ ወደ 40 በመቶ አካባቢ ድርሻ ቢኖረውም ከዐሥር ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በየአመቱ የምግብ እርዳታ ይሻል። በአገሪቱ የሚገኘውም የኢንደስትሪ ክፍል ከአገሪቱን ዓመታዊ ጥቅል ምርት 15 በመቶ በታች የሚሆን ድርሻ ይዞ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ከአፍሪካ መለኪያ እንኳን ሲታይ በጣም ያነሰ የፋብሪካዎች ክምችት በኢትዮጵያ ይገኛል። በእነዚህ ፋብሪካዎች የሚመረተው ምርትም ከዓመታዊ ጥቅል ምርት ከ5 በመቶ በታች ድርሻ አለው። ከዓመታዊ ጥቅል ምርት ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው የአገልግሎት ክፍል እንኳን ሳይቀር ኋላ ቀረ በሆኑና ዝቅተኛ ምርታማነት ባላቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነው።

ይህ የሚያመለክተው ኢትዮጵያ ፈጣን በሚባል ሁኔታ መሰረታዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ማምጣት እንደሚገባት ነው። መሰረታዊ ለውጥ መጣ የሚባለው በግብርና ላይ ተመስርቶ የነበረን ምጣኔ ሀብት በኢንዱስትሪ እና በዘመኑ የአገልግሎት ዘርፎች እንዲመራ ማድረግ ሲቻል ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን ለውጥ የሚቋቋም የአረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ግንባታ ዕቅድ (Climate Resilient Green Economy Startegy) ከ15 ዓመት በፊት ተቀብላ ለምዕተ ዓመታት በግብርና ላይ የተመሰረተውንና ኋላ ቀር የሆነውን የምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግና ለማዘመን ወደ ሥራ ገብታለች። የአረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ዋናው ግብ የተፈጥሮ ሁኔታን በማያዛባ መልኩ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ መሰረታዊ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ማምጣት ነው። የኢትዮጵያን እግር ተከትለውም በዛ ያሉ የአፍሪካ አገሮች የአረንጔዴውን የልማት አቅጣጫ ተቀብለው ዋነኛው የዕድገት ፖሊሲያቸው አካል አድርገውታል።

አረንጔዴ የልማት አቅጣጫ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሆነ ለአፍሪካ ይበጃል ወይንስ ጉዳት ያስከትላል የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ግን እንዴት ፖሊሲው እንደመነጨና በስፋት ተቀባይነት እንዳገኘ ማየት ያስፈልጋል። በመሰረታዊነት አረንጔዴ የልማት አቅጣጫ የሚመነጨው የዓለም የሙቀት መጠን በሰው ሰራሽ ምክንያቶች እየጨመረ ነው ከሚለው በአሁኑ ወቅት ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያገኘ አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ ከ1970ዎቹ ጀምሮ እስከ ሚሊኒየሙ መባቻ ድረስ ሲንሸራሸር ቢቆይም በሥፋት መቀንቅን የጀመረው ግን በ2001 በኮፐንሀገን ከተካሔደው ዓለም ዐቀፋዊ የአየር ንብረት ስብሰባ በኋላ ነው።

የዚህ ሐሳብ አቀንቃኞች የዓለምን ሙቀት መጨመር ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቀውና እየጨመረ ከመጣው የካርቦን መጠን ጋር ያያይዙታል። ካርቦን ደግሞ በዋናኘት የሚመነጨው በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ማለትም ፋብሪካዎች ከሚጠቀሙት የኃይል ምንጮችና ከእነርሱም ከሚወጣው የተበከለ ጭስ ነው። ስለዚህም በሙቀትና የካርቦን መጠን መጨመር መካከል ቀጥተኛ የሆነ ትስስር አለ ማለት ነው። ስለዚህም ምድርን ከተጋረጠባት አደጋ መታደግ የሚቻለው ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት የኃይል ዓይነቶችን በሌላ ተስማሚ የኃይል ምንጮች መቀየርና ሰፋ ያለ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት ነው ብለው ይሞግታሉ።
ሊቃውንት የዓለምን ሙቀት መጠን እየጨመረ እንደመጣ ይስማማሉ። ባለሙያዎችም እንዳረጋገጡት አማካኝ የዓለምን ሙቀት ባለፈው መቶ ዓመት እያደገ መጥቶ አሁን 1.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ደርሷል። የየካርቦን መጠንም ቢሆን ባለፉት ኹለት መቶ ዓመታት በ30 በመቶ ጨምሯል። ነገር ግን ሁሉም ሊቃውንት በሙቀትና የካርቦን መጠን መጨመር መካከል ቀጥተኛ የሆነ ትስስር አለ ብለው አያምኑም።

የተባበሩት መንግሥታት አካል የሆነው Inter-Governmental Panel on Climate Change (NIPCC)ከቀረቡለት 2000 ከሚጠጉ ጥናቶች መርጦ እስከአሁን ድረስ ወደ 50 የሚጠጉ በሙቀትና የካርቦን መጠን መጨመር መካከል ቀጥተኛ የሆነ ትስስር አለ ብለው የሚሞግቱ ጥናቶችን አሳትሟል። በተቃራኒው ደግሞ የተወሰኑ ተቀባይነት የተነፈጋቸው ጥናቶች ገለልተኛ በሆነው NIPCC አማካኝነት ለሕትመት በቅተዋል። በነዚህ ጥናቶችን መሰረት እስከአሁን ድረስ የዓለም የሙቀት መጠን በሰው ሰራሽ ምክንያቶች እየጨመረ ነው የሚለው አመለካከት ከፅንሰ ሐሳብ ደረጃ በዘለለ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ አልተገኘለትም። NIPCC ʻNature Not Human Activity, Rules the Climateʼ በሚል ርዕስ ያሳተመውን ጥናት ማንበብ ከኹለቱም ወገኖች የሚነሳውን ሐሳብ ሚዛናዊ በሆነ አዕምሮ ለመመዘን ይረዳል።

ከእነዚህን ኹለት ተቃራኒ ሐሳቦች የትኛው ትክክል እንደሆነ ማረጋገጥ ለአፍሪካዊያን ብሎም ለኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመን የማይቻል ብሎም ብዙም አስፈላጊ ጉዳይ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ወደ ከባቢ አየር በሰው ሰራሽ መንገድ የሚለቀቀው የካርቦን ልቀት ነው ከሚለው አስተሳሰብ የሚመነጨው የአረንጔዴ የልማት አቅጣጫ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣት እንደሚችል ወይንም እንደማይችል መገምገም ይገባል።

ታሪክ እንደሚመሰክረው የትኛውም አገር ያለተቆራረጠ በቂ ኃይል አቅርቦት ማደግ አይቻለውም። የኃይል ምንጮች ኹለት ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮች ሲሆኑ በዋናኘትም ከድንጋይ ከሰል፣ ኒክሌር፣ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ሊገኙ የሚችሉትን ኃይል ያጠቃልለሉ። እነዚህ ምንጮች በምድር ላይ በተወሰነ መጠን የሚገኙ ስለሆኑ አቅርቦታቸው የተገደበ ነው። በሌላ በኩል ድግሞ እንደ ፀሐይ ብርሃን፣ ንፋስ፣ ውሃ እና የተፈጥሮ እንፋሎት አላቂ ያልሆኑና ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች ይባላሉ። ካለነዚህ የኃይል ምንጮች አገራት የኢኮኖሚ ሽግግር ማሳለጥ አይችሉም።

የአረንጔዴ የልማት አቅጣጫ አላቂ ያልሆኑና ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች መጠቀምን ያስገድዳል። ይህም መንገድ ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብሎም ይታመናል። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪካ አገራት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች መሰረተ አውታሮችን በመገንባት ተጠምደዋል።

ባለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ከ400 ሜጋ ዋት ወደ 4500 ሜጋ ዋት አድጓል። በየትኛውም መስፈርት ሲመዘን ይህ ትልቅ እመርታ ነው። ነገር ግን እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት አልተቻለም። ሌላውን ትተን እንኳን የፋብሪካዎችን የኃይል ፍላጎት በከፊልም ቢሆን እንኳን መሸፈን አልተቻለም። በአሁን ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት በኢትዮጵያ 40 በመቶ አካባቢ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የኃይል ፍላጎት በኢትዮጵያ በ25 በመቶ በየዓመቱ ያድጋል። ያልተቆራረጠና በቂ የኃይል አቅርቦት የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ለማረጋገጥ ውሳኝ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮጵያ በጣም አነስተኛ ነው። እዚህ ላይ በዋናነት መነሳት የሚገባው ጥያቄ ኢትዮጵያ ለምን የሃይል አቅርቦትን ከዚህ በላይ አሳድጋ ፋብሪካዎችን በሙሉ አቅም እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ተሳናት የሚለው ነው።

በምትከተለው አረንጔዴ የልማት አቅጣጫ ምክንያት ኢትዮጵያ በዋነኛነት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች በተለይም ከውሃ ግድቦችና ከንፋስ ነው። ይህም ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኃይል አቅርቦት ይሸፍናል። እስከ አሁን ድረስ ከአምስት በላይ የሚሆኑ የተለያየ አቅም ያላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ግድቦች ገንብታለች። በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብንም እየገናባች ነው። ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ እያለ ግን አገሪቱ በከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ነውጥ ውስጥ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የውሃ ማማ ተብለው ከሚጠሩ ጥቂት አገሮች አንዷ ነች። እንዲያውም ኢትዮጵያ ከኮንጎ ለጥቃ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ከውሃ ግድቦችን ለማመንጨት እምቅ ሀብት አላት ሀገር ነች። ነገር ግን ታዳሽ ከሆኑ የኃይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። የአገሪቱ አቅም የተወሰነ በመሆኑና በብድርም ሆነ በእርዳታ የምታገኘው ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ በሚያስፈልገውን መጠን ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ የውሃ ግድቦችን መገንባት አልቻለችም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ እስከ 2023 ለመገንባት እቅድ ውስጥ ላካተቸቻቸው ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያመነጩ የውሃ ግድቦችን ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት መሰረት 40 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ ሀገሮች አረንጔዴ የልማት አቅጣጫን ሲቀበሉ ካደጉትና በከፍተኛ ደረጃ ለካርቦን መጠን መጨመር አስተዋፆ ካላቸው አገራት በመዋዕለ ነዋይ ፍሰት፣ በእርዳታና በብድር መልክ ሊመጣ የሚችለውን ገንዘብ ታሳቢ አድርግው መሆኑን እሙን ነው። በተለይም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአፍሪካን ድምፅ በቅጡ ባሰተጋቡበት የኮፐንሀገንኑ ዓለም ዐቀፋዊ የአየር ንብረት ስብሰባ ያደጉት አገራት ለአፍሪካ በመጀመሪያውቹ ሦስት ዓመታት ብቻ በዓመት 30 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መስማማታቸው ከፍተኛ ተስፋ ያጫረ ነበረ። የዚህ ገንዘብ መጠን በ2014 በዓመት መቶ ቢሊዮን ዶላርም እንዲድርስ ስምምነት ነበረ።

ነገር ግን የኮፐንሀገንኑ ስምምነት አንድ ትልቅ ክፍተት ነበረው። ይኸውም ስምምነቱ አስገዳጅነት አልነበረውም። ስለሆነም የአፍሪካ አገራት ቃል ከተገባላቸው አንድ አራተኛውን እንኳን ማግኘት አልቻሉም። ከኹለት ዓመት በፊት በ179 አገሮች የተፈረመው የፓሪሱ ስምምነት አስገዳጅነት ቢኖረውም ወደ አፍሪካ አገሮች ፈሰስ ይደረጋል ተብሎ ከታቀደው ገንዘብ ውስጥ 30 እስከ 40 በመቶ ትሸፍናለች የተባለችው አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን በማግለሏ የአፍሪካ ተስፋ ጨልሟል።

ካደጉት አገራት በመዋዕለ ነዋይ ፍሰት፣ በእርዳታና በብድር መልክ የሚመጣው ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንስ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት በራሳቸው አቅም ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች መገንባት አይችሉም ወይ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን የገንዘብ አቅም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን ብዙ ግድቦችን በመገንባት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት የሚገድባት፤ እነዚህን ትላልቅ ግንባታዎችን በትክክለኛው ጊዜና ጥራት መፈፀማቸውን የሚካታተል የተማረ የሰው እጥረት በከፍተኛ ደረጃ አለ። በሚገርም መልኩ ባለፉት 20 ዓመታት ከተገነቡ ግድቦች መካከል አንድ እንኳን በታቀደለት ጊዜ የተጠናቀቀ የለም።

ከኹለት ዓመት በፊት የተጠናቀቀውን 1870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለውን የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብን አፈፃፀም መመልከት ብቻ ጉዳዩን ግልፅ ለማድረግ ይበቃል። ግድቡ 1998 ሲጀመር በሰባት ዓመት ለማጠናቀቅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም እስከ 2009 ድረስ ተጓቷል። በዚህም ምክንያት የግንባታ ወጯው በ30 በመቶ አሻቅቦ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚታየው በጣም አነስተኛ የሆነ የማስፈፀም አቅምም የአደባባይ ሚስጢር ነው።

እንግዲህ እንደዚህ ባሉ አንኳር ችግሮች ተከበን ነው ፈጣንና መሰረታዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማረጋገጥና ኢትዮጵያን 2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የምንውተረተረው። በእኔ አስተሳሰብ እነዚህ ችግሮች እያሉ ሙሉ ትኩረታችንን ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች ግንባታ ላይ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

መፍትሔ የሚሆነው በከፊልም ቢሆን ከፍተኛ ወጪና የተማረ የሰው ኃይል ወደማይጠይቁት ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮች ፊታችንን ማዞር ነው። የአፍሪካ አገሮች ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም እንግዳ አይደሉም። ለምሳሌ እንደ ግብፅ፣ ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ በስፋት የድንጋይ ከሰልን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎቻቸውን ለማንቀሳቀስ ይጠቀሙበታል።

ኢትዮጵያም ቢሆን ከሰባት ዓመት በፊት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የጠለለ የድንጋይ ከሰልን በትንሹም ቢሆን እንዲጠቀሙ ማድረግ ችላ ነበር። እንቅስቃሴው በተለያየ ምክንያት ቢቆምም በትንሽ ጥረት በማስቀጠል በስፋት ወደ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ማስፋፋት ይቻላል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን መጠቀም ሲጀምሩ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የካርቦን መጠን አይጨምርም ወይ የሚል መሰረታዊ የሆነ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ይህን በግልፅ ለመረዳት ጉዳዩን ከአንድ አገር ወይም አህጉር በዘለለ ዓለም ዐቀፋዊ በሆነ መነፅር ማየት ያስፈልጋል።

በዓለም ላይ አብዛኛው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚመጣው ታዳሽ ካልሆኑ ምንጮች ነው። በቅርቡ በወጣው የዓለምን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በሚያሳየው ሐተታ መሰረት ከኹለት ዓመት በፊት ከነበረው ጠቅላላው የዓለም የኃይል ፍጆታ ውስጥ 34 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል የመነጨው ከተፈጥሮ ዘይት ሲሆን ከድንጋይ ከሰል 28 በመቶ፣ ከተፈጥሮ ጋዝ 23 በመቶ እና ከኒክሌር 8.5 በመቶ ተገኝቷል። ከኒክሌር የተገኘውን ብንቀንስ እንኳን 85 በመቶ የሚሆነው የዓለም ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለሟሟላት በዋነኝነት የካርቦን መጠን በከባቢ አየር ለመጨመር ምክንያት ናቸው የሚባሉትን እንደ የድንጋይ ከሰል፣ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ሥራ ላይ ውለዋል።

በዚህም ምክንያት በከባቢ አየር የሚገኘው የካርቦን መጠን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በኹለት በመቶ ጨምሮ 37 ቢሊዮን ቶን ደርሷል። አስገራሚው ጉዳይ ያደጉትም ሆነ በፍጥነት እያደጉ ያሉ አገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የካርቦን መጠን ከመቀነስ ይልቅ የበለጠ ጨምረውታል። እንዲያውም ከጃፓን በስተቀር አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሕንድና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ከኮፐንሀገንኑም ሆነ ከፓሪሱ ስምምነት በተቃራኒ የካርቦን ልቀታቸው መጠን በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ ነው። ይህ በትክክል የሚያሳየው እነዚህ አገራት እራሳቸው ባወጡት ሕግ መመራት እንደማይፈልጉ ነው። ነገር ግን ከጠቅላላው የካርቦን ልቀት አንድ በመቶ እንኳን አስተዋፆ የሌላቸው የአፍሪካ አገራት በዚሁ ሕግ እንዲመሩ ያስገድዳሉ። በየትኛውም መመዘኛ ይህ ፍትሐዊ አሰራር አይደለም።

ኢትዮጵያንና የአፍሪካ አገራት በዚህ ወቅት መንታ መንገድ ላይ ይገኛሉ። በአንድ በኩል የአረንጓዴ ምጣኔ ሀብት አቅጣጫን በማስቀጠል አዝጋሚም ቢሆንም ቀስ በቀስ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት መሥራት ነው። አለበለዚያም ይህንኑ አቅጣጫ ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩና ለራስ በሚስማማ መልኩ ከልሶ ፈጣን ዕድገት አስመዝግቦ የአፍሪካን ትንሳኤ ዕውን ለማድረግ መትጋት ነው።

ሳምሶን ኃይሉ የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት የሆነችው ʻኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪውʼ ምክትል መራሔ አሰናጅ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው ebr.magazine1@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here