በአዲስ አበባ ለሞተር ሳይክል ሰሌዳ መስጠት ቆሟል

0
973

በአዲስ አበባ ለሞተር ሳይክሎች ሰሌዳ መሰጠት መቆሙን የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የውስጥ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ 24 ሺሕ የሚያህሉ ሞተር ሳይክሎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 16 ሺሕ የሚሆኑት የክልል ሰሌዳ ያላቸው መሆኑም ታውቋል።

እነዚህ ሞተር ሳይክሎች በጦር ኃይሎች፣ አየር ጤና፣ ወይራ ሰፈር፣ ካራ፣ አስኮና ቄራ አካባቢ ኮድ ኹለት ታርጋ ይዘው የሕዝብ አገለግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የብዙኀን መጓጓዣን የማበረታታት አቅጣጫ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በአገሪቱ በሕገወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ሞተር ሳይክሎችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰንና የብዙኀን መጓጓዣን ለማስፋፋት ጥናት እያደረገ መሆኑን ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሞተሮቹን የሚያሽከረክሩት አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃድ ሳይኖራቸው በመዲናዋ አዲስ አበባ ሰዎችን እየጫኑ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ እያደረሱ መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የመንገድ ደኅንነት አፈጻጸምን በተመለከተ ባቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ላይ ያስታወቀ ሲሆን፣ እነዚህ ሞተር ሳይክሎች የአደጋ መንስኤ ሆነው እንዳይቀጥሉ ባለሥልጣኑ በተግባር የተደገፈ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን ጥናት እያጠናቀቀ መሆኑን።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የመንገድ ደኅንነት አፈጻጸምን በተመለከተ የተከናወነውን የክዋኔ ኦዲትን መሰረት በማድረግ መጋቢት 26/2011 ለተቋሙ የበላይ የሥራ ኃላፊዎች ለውይይት መነሻ ባቀረበው ጥያቄ፣ እነዚህን ሞተሮች የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከ2 ሰው በላይ እየጫኑ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ እያስከተሉ መሆኑን ማንሳቱ ይታወሳል።

˝እነዚህ ሞተር ሳይክሎች የሠሌዳ ቁጥር እንዲኖራቸውና የሚያደርሱትንም አደጋ ለመቆጣጠር ለምን አልተሰራም? አሁንስ ባለሥልጣኑ ይሄንን ለማስተካከል ምን እየሠራ ነው?˝ በማለት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ባለሥልጣኑ በነዚህ ሞተሮች ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ ለመውሰድና የሚያደርጋቸውን ጥናቶች ሲያጠናቅቅ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የአዲስ ማለዳ ዕትም ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ባለኹለት እግር ሞተር ተሸከረካሪዎች አስፈላጊውን ማስረጃና የሠሌዳ ቁጥር እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሁኔታ የመሥራት ኃላፊነት እንደሚኖር ተጠቅሷል። በተጨማሪም በአጠቃላይ 134 ሺሕ 345 ሞተር ሳይክሎች ተመዝግበው ሰሌዳ ሳይሰጣቸው በመንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በፓርላማ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here