የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከስድስት መቶ በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞችን አባረረ

0
634
  • ከዐሥራ ስድስት ዓመት በላይ ያገለገሉ ሠራተኞች ይገኙበታል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ከአራቱም ዲስትሪክት ስድስት መቶ ሠራተኞችን በድንገት ማባረሩ ታወቀ። ከሥራ ገበታቸው ከተገለሉት ሠራተኞች መካከል 16 ዓመትና ከዛ በላይ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያገለገሉ ሠራተኞች በቁጥር በርካቶች ናቸው።

ሠራተኞች ካለአግባብ ከሥራ ገበታችን እንድንባረር ተደርገናል ሲሉ አቤት ለማለት መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያቀኑ ሲሆን ምላሽ የሚሰጣቸው በማጣታቸው ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅሕፈት ቤት ቢያመሩም በፖሊስ እንደተባረሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ቅሬታ አቅራቢዎች እንደተናገሩት በድንገት አቁሙ እንደተባሉና ከሥራ ለመታገዳቸው ኃላፊነት የሚወስድ አካል ባለመኖሩ ለማን አቤት ማለት እንዳለባቸው እንደማያውቁ ገልፀዋል።

መጋቢት አንድ ውላቸው እንዲቋረጥ እንደተደረገ የሚገልፁት ሠራተኞች ምክንያቱን በውል እንደማያውቁትና ሊያብራራላቸውም የሚፈቅድ ሰው እንደሌለ ተናግረዋል። ከአንድ ዲስትሪክት በቁጥር ወደ 200 የሚጠጋ የጥገናና የመስመር ዝርጋታ ሠራተኛ እንደሚኖር የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ አሁን በተደረገው ድንገተኛ የውል መቋረጥ ከአንድ ዲስትሪክት 180 የሚሆን ሰው እንደተቀነሰ አስረድተዋል። ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁት ደሞዛቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ተቀማጭ ገንዘብ ስለሌላቸው በድንገት አቁሙ ሲባሉ ከፍተኛ ችግር ላይ እንደወደቁ ምሬት በቀላቀለ አንደበት ተናግረዋል። አያይዘውም በአፋጣኝ መንግሥት ምላሽ እንዲሰጣቸው እና ከተጋረጠባቸው ችግር እንዲገላግላቸው ተማፅነዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል ደግሞ ከተለጠፈው ማስታወቂያ መረዳት እንደተቻለው፤ ከዚህ ቀደም የተወሰነ ሥራን በተወሰነ የጊዜ ገደብ ለማከናወን የተቀጠሩ ሰዎች ከዚህ በኋላ በቁርጥ ዋጋ እንዲቀጠሩ ፍላጎት እንዳለው ታውቋል።

ይህም የሚሆነው በሚመለከተው መንግሥት አካል ተደራጅተው ሲመጡ እንደሆነና በሦስተኛ ወገን እንዲሠሩ ያዘጋጃቸውን የʻዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክʼ ግንባታና ማዛወሪያ ሥራዎችን በቁርጥ ዋጋ ለማሠራት በመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራር ተወስኗል።
በተለጠፈው ማስታወቂያው ላይ እንደገለፀው ሠራተኞች በሚመለከተው የመንግሥት አካል ተደራጅተው ሕጋዊ ሰውነት ይዘው በመምጣት በቁርጥ ዋጋ እስኪሠሩ ድረስ መስሪያ ቤቱ ሕግና ደንብ በሚፈቅደው መሰረት የቁርጥ ዋጋ ከፍያ ውል ስምምነት መሰረት መሥራት ለሚፈልጉ በሩ ክፍት እንደሆነ ጠቁሟል። ለተገልጋይ ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ የመጣውን የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ መልካም አስተዳደር እጦት ለመቅረፍ ታስቦ የአሰራር ለውጥ እንደተደረገ ተጠቅሷል።

ስለ ተፈጠረው ችግር አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here