ሚኒስቴሩ ከኹለት ቅርንጫፎቹ 800 ሚሊዮን ብር አልሰበሰበም

0
653

የግብር ዕዳ ውሳኔ ላይ ባለመስማማት ለቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ቅሬታቸው ውሳኔ ሳያገኝ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ የገቢዎች ሚኒስቴር በ2009 በጀት ዓመት ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ሳይሰበስብ ቀርቷል። በአዲስ አበባ ኤርፖርትና በአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት የአቤቱታ ቅሬታው ውሳኔ ሳያገኝ መቅረቱ ጋር ተያይዞ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮብ ብር በላይ ብር ያልተሰበሰበ ሒሳብ አለ ቢባልም ግማሹ መሰብሰቡንና ስምንት መቶ ሚሊዮን የሚሆነው አሁንም እንዳልተሰበሰበ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩ የ2009 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል። በዚህም ወቅት በርካታ ኦዲት ግኝቶች የቀረቡ ሲሆን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ተገኘ ስለተባለው የኦዲት ግኝት የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች በእርግጥም ክፍተት እንዳለ እና በጊዜው ግልፅ ያልሆነ አሰራርና አቤቱታውን በጊዜ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ አለመቻሉን ገልፀዋል። ግማሽ ያህሉን የገንዘብ መጠን መሰብሰብ ቢቻልም ቀሪውን ለመሰብሰብ በትጋት እየተሠራበት እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሚኒስቴሩየ2009 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ለማወቅ እንደተቻለው በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ወይም በደንብ መተላለፍ ኦዲት ውሳኔ መሰረት የቀሪ ቀረጥና ታክስ ዕዳ ተወስኖባቸው በጊዜ ገደቡ ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ በዘጠኝ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ተደርጓል። ይህን የኦዲት ግኝት በመመርኮዝ የገቢዎች ሚኒስቴር ምላሽ ተሰቶበታል። አምራቾች የሚያስገቡት ዕቃ በተንጠልጠል ላይ በመሆኑ እንደዕዳ ይያዛል ተብሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በተንጠልጠል ላይ የሚገኙት የፋብሪካ ዕቃዎችና ግብዓቶች በመሆናቸው ለአምራች ዘርፉ መበረታታት ሲባል ሚኒስቴሩ እንደታገሳቸውመ እና ይህም እንደ ዕዳ ሊያዝ እንደተቻለ ተነግሯል። የንግድና ኢንዱስትሪም በጊዜው ትንሽ ታገሱ የሚል ደብዳቤም ለገቢዎች ሚኒስቴር የሚጽፍበት አጋጣሚ እንዳለም ታውቋል።

በቋሚ ኮሚቴው ስለቀረበው እና ተገኘ ስለተባለው የ1 ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ብር ከሚኒስቴሩ የተሰጠው ምላሽ እንደሚያመለክተው ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ እና በቃሊቲ ጉምሩክ የሚታየው ወጥ ያልሆነ የድኅረ ዕቃ አወጣጥ ሥነ ስርዓት እንቅፋት እንደሆነ ተጠቁሞ ለቀሪው ገንዘብ ያለመሰብሰብ ችግር በዋናነት እንደምክንያት ተጠቅሷል።
የገቢዎች ሚኒስቴር 1999 እስከ 2009 በጀት ዓመት ድረስ ለዐሥር ዓመታት ሳይወራረድ የቆየ ተሰብሳቢ ሒሳብ በዘጠኝ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶች 52 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን ከዚሁም ጎን ለጎን ማስረጃ የሌላቸውና ከማን እንደሚሰበሰብ የማይታወቅ ተሰብሳቢ ሒሳብ 48 ሚሊዮን የኦዲት ግኝት የታየ ሲሆን ከ48 ሚሊዮኑ ውስጥ 10 ሚሊዮኑን ማስተካከያ እንደተሠራበት ታውቋል።

በመጨረሻም በገቢዎች ሚኒስቴር ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በድምሩ የኦዲት ግኝት ያለበት ሲሆን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሚሆነውን ከ11 ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶቹ ሰብስቧል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ ታክስ ጋር በተገናኘ 8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊሰበሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 1 ብቻ መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል። የኦዲት ግኝቱን መሰረት አድርጎ የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በሚኒስቴሩ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ አድንቀው ነገር ግን ከበጀት አጠቃቀም፣ ከተሰብሳቢ ሒሳቦችና ከዚህም ጋር ተያይዞ ከማን እንደሚሰበሰብ ግልፅ ያልሆነ ሒሳብ ላይ ሚኒስትሩ ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here