አሳሳቢው ሥራ አጥነት

0
961

በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የፖለቲካ ለውጥ እና ማሻሻያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ጎልቶ አልታየም በሚል ይታማል። ከዚያም በላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው ‘አዲስ ወግ’ የተሰኘ የኹለት ቀናት የውይይት ጉባዔ መዝጊያ ላይ ሲናገሩ የነደፍነው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ አለ ግን እንደ ፓርቲ ለምርጫ ስንወዳደር ይዘነው እንወጣለን በማለት የመንግሥትን የኢኮኖሚ ዕቅድ ለፓርቲው መወዳደሪያ ግልጽ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚመርጡ አመላክተዋል። ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተለይም በኦፊሴላዊ መንገድ ከሚጠቀሰው በላይ የተንሠራፋው ሥራ አጥነት እየወዘወዘው ነው። ኤፍሬም ተፈራ ይህንን ምጣኔ ሀብታዊ ፈተና የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ በማቅረብ የችግሩን ጥልቀት፣ መንሥኤ እና መፍትሔ ያስዳስሰናል።

በአዲስ አበባ ከተማ ሁሌም በሰዎች ከሚጨናነቁ ቦታዎች መካከል አራት ኪሎ ጆሊ ባር አጠገብ የሥራ ማስታወቂያ የሚለጠፍባቸው ሰሌዳዎች የሚገኙበት ቦታ ተጠቃሽ ነው። በዚህ ሥፍራ በአብዛኛው አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች የሚታዩ ቢሆንም፥ እንደ ቅዱስ ሥፍራ ለዓመታት የተመላለሱበትን ወጣቶች ማግኘት የተለመደ ነው። ለእነዚህ ወጣቶች ከዚህ ሥፍራ በቅርብ ርቀት የሚገኙት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ፓርላማው በቂ ምላሽ የሰጧቸው አይመስልም።
ከእነዚህ ተመራቂዎች መካከል ‘ዕድለኛ የሆኑት’ ጥቂቶች ቶሎ ሥራ ያገኛሉ። የ27 ዓመቱ እና የኢንጂነሪንግ ምሩቁ አባይነህ ደጀን የመሳሰሉ እና ‘ዕድለኛ ያልሆኑት’ ብዙኃኑ ደግሞ ለዓመታት በሥራ ፍለጋ ይንከራተታሉ።

የአገሪቱ ገበያ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ለመጣው ተመራቂዎች ሥራ ለማቅረብ አቅም እንደሌለው ለዓመታት ሲገለጽ ቆይቷል። ይሁንና ችግሩ ከመሠረቱ ስለመፈታቱ አሁንም ማሳያ ማቅረብ አይቻልም። ለአብነትም አባይነህ ከተመርቀ ሦስት ዓመት ሊሞላው ነው። የተማረውን ግን እስካሁን በተግባር ላይ ማዋል አልቻሉም።

ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስተምራ የምታስመርቃቸው እንደ አባይነህ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ቢጨምርም የሥራ ቦታው ከተመራቂው ቁጥር ጋር ሊመጣጠን አልቻለም። አባይነህ በተመረቀበት ሙያ ሠርቶ ለመቀየር የነበረው ሕልም መሞቱን ይናገራል። “ለዓመታት ያለ እረፍት ሥራ እየፈለኩ ነው። አንዳንድ ቦታ ስሔድ አራት ሰው ተፈልጎ አራት መቶ ሰው ተሰልፎ ስመለከት ያስጨንቀኛል፤ ወደፊት ስለሚኖረን ተስፋ ለደቂቃ ማሰቡ ያማል” ሲል አሳሳቢነቱን ይገልጻል። “ተስፋ ቆርጫለሁ” ሲልም በሥራ ማግኘቱ ላይ ያለውን ተስፋ ይገልጻል።

በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የሚሰጡትን መፍትሔዎች እንዳይታዩ ያደረጋቸው ይመስላል። ዘንድሮም ከዚህ የተለየ አይደለም። በ2009 በአገሪቱ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ብቻ 126 ሺሕ ተመራቂዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮችና ደረጃዎች ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ከዚሁ ውስጥ 109 ሺሕ ተመራቂዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
የእነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መብዛት የቅበላ አቅምንና የተመራቂ ተማሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል:: የቁጥሩ ጭማሪ እንደ ትልቅ እርምጃ የሚታይ ቢሆንም፣ የትምህርት ጥራትና የምሩቃን ሥራ አጥነት ጥያቄ ሆኖ መነሳቱ ግን አልቀረም:: በ1987 ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የገቡ ተማሪዎች ቁጥር 35,000 ብቻ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት የዩኒቨርሲቲዎች የቅበላ አቅም ከ100 ሺሕ በላይ ሆኖ ነበር:: በሌላ በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውና ተመርቀው መውጣታቸው ያለ በቂ ዝግጅት የተደረገ ለውጥ እንደሆነ በመጠቆም፣ ጥራት ለመጓደሉና ለሥራ ዓለም ብቁና ዝግጁ ያልሆኑ ተመራቂዎች ለመውጣታቸው ቁጥሩ ምክንያት መሆኑን የሚሞግቱም አሉ።

ሥራ አጥነት
እንደ ዓለም ባንክ ግምት በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 600,000 ሰዎች አምራች ኀይል የምንለውን የዕድሜ ክልል (15-64) ይቀላቀላሉ። የአፍሪካ ዕድገት ኢኒሼቲቭ ረዳት ዳይሬክተር የሆነችው ክሪስቲና ጎሉበስኪ ‘Trends in Ethiopia’s Dynamic Labour Market’ ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት ባሳተመችው ጽሑፏ በኢትዮጵያ ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ሽግግር፣ የሥራ እና የሥራ ዕድል ሁኔታ በሰጠችው ገለጻ እንደመነሻ ኢትዮጵያን ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ተርታ ትመድብና በመቀጠልም “ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በፈጣን ዕድገት ላይ ቢገኝም በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው አምራች ኀይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም” ብላለች።

ይህንንም በምጣኔ ሀብት ቋንቋ ስናስቀምጠው በሰው ኀይል ገበያው የሥራ ፈላጊው ወይንም አምራች የሆነው ሰው ኀይል አቅርቦት ከሥራ ቀጣሪው ወይንም ከቅጥር ፍላጎት በእጅጉ የበዛና የማይጣጣም ነው የሚል ትርጉም ይሰጠናል።
ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ ቢሆንም፥ በተለያየ የሥራ መስክ ሥራ ማግኘት ያልቻሉ፣ ሥራ ለማግኘት ግን በንቃት እያፈላለጉ ያሉ ሰዎች ሥራ አጥ በሚለው ሥያሜ ውስጥ ያርፋሉ። ከዚህ የሥራ አጥነት ትርጓሜ እንደምንረዳው ሥራ አጥ ለመሰኘት ሥራ አለማግኘት ወይንም አለመሥራት ብቻ በቂ ያልሆነ ሲሆን፣ በተጨማሪ ባለን ዕውቀት ወይም ጉልበት ሥራ ለማግኘት በንቃት ማፈላለጋችን መሠረታዊ መሆኑን ልብ ይለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሰይድ ኑሩ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፥ በከተማ ያለው የሥራ አጥነት ምጣኔ 16.5 በመቶ መሆኑ ምጣኔው ከፍተኛ እንደሆነ በመጠቆም፥ የገጠሩ ሥራ አጥ ምጣኔ 2 በመቶ ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ የአንድ አራሽ ገበሬ የመሬት ይዞታ (በነፍስ ወከፍ) በ1960ዎቹ ከነበረበት 1.2 ሔክታር በአሁኑ ጊዜ ወደ 0.33 ሔክታር ስለቀነሰ ድብቅ ሥራ አጥነት መኖሩን ያነሳሉ። በሌላ አነጋገር አንድ ጠንካራ ገበሬ ሊያለማው የሚችለውን መሬት አራት ገበሬዎች ይጋሩታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ስብጥር ወደ ወጣቱ እያመዘነ በመጣበት እና ትምህርት በገጠር በመስፋፋቱ ምክንያት ወጣቶች ወደ ከተማ በሚፈልሱበት በአሁኑ ዘመን የወጣት ሥራ አጥነት ከፍ ማለቱ አሳሳቢ ነው ሲሉ ሰይድ (ዶ/ር) ይነግሩናል። በ2005 ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት የሚደርሱ የከተማ ወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ 21.9 በመቶ፣ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 24 የሚደርሱት የሥራ አጥነት ምጣኔ 25.8 በመቶ፣ እንዲሁም ከ25-29 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሥራ አጥነት ምጣኔ 17.2 በመቶ ነበር። የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ሐቢስ ጌታቸው በበኩላቸው የዓለም ባንክ በቅርቡ ባደረገው ጥናት የአገሪቱ የሥራ አጥ ምጣኔ 19.8 በመቶ መድረሱን ይናገራሉ።

ሥራ አጥነትና ግብርናችን
በአገራችን ለምሳሌ፣ ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅጥር የያዘው ግብርናው ነው። እሱ ደግሞ ወቅት ላይ የተመሠረተ ነው። ዝናብን መሠረት አድርጎ ብቻ የሚንቀሳቀስ ነው። ስለዚህ ወቅትን እየጠበቀ የሚሠራን ሰው፣ ያውም እንደኛ አገር ባለ የተበጣጠሰ መሬት ላይ ለሚሠራ ገበሬ፥ ባለሥራ ነው ብለን የምንናገር ከሆነ፣ ስለ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ ማውራት አንችልም በማለት ያወሱን የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ሀቢስ ጌታቸው ናቸው።

ግብርናው ሰው እየጨመረ (ሥራ እየፈጠረ) የሚሔድ ዘርፍ አይደለም የሚሉት ሀቢስ፥ ቢጨምርም በገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ፣ ያላቸውን ጠባብ መሬት እየተጠቀሙ፣ ለአንድ ሰው የማትበቃ መሬት ይዘው የሚያርሱ በመሆናቸው፣ ሥራ ፈጣሪ የሆነ ዘርፍ ነው ሊባል አይችልም። ስለዚህ ግብርናው አሁን ባለው ሒደት ሰው የሚቀጥር መስክ አይደለም በማለት ግብርናው በሥራ ፈጠራ ላይ ያለውን ሚና ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምጣኔ ሀብት መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አጥላው ያላቸው ሐሳብ ግን ከዚህ የተለየ ነው፥ “ማኑፋክቸሪንጉ ከግብርና ጋር በደንብ የተያያዘ አይደለም። አገልግሎቱ በጣም ትልቅ ነው። ግብርናውን እየተካ ያለው ማኑፋክቸሪንጉ ሳይሆን አገልግሎቱ ነው። ሌሎች ትልቅ ዕድገት ላይ የደረሱ አገሮች በታሪክ እንደምናየው ግብርናውን መጀመሪያ የወሰደው ኢንዱስትሪው ነው” ይላሉ። አገልግሎቱ “ኢንዱስትሪውን ተከትሎ የሚያድግ ዘርፍ ነው” የሚሉት ዶክተሩ፥ በአደጉ አገሮች ግብርናው ከኢንዱስትሪው ጋር በመዛመዱ ማደግ ችሏል ሲሉ ያስረዳሉ። ግብርናው ማደግ የማይችል ሆኖ ሳይሆን ትኩረት ስላልተሰጠው ነው ሲሉ ግብርናው ትኩረት ያጣ ዘርፍ መሆኑን ያብራራሉ።

“የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ አናሳ ነው” የሚሉት ዶክተር ካሳ፥ “ለምሳሌ የተለያዩ አገሮችን ብናወዳድር በተመሳሳይ ደረጃ የነበሩ፣ በ1980ዎቹ ሽግግሩን ስናይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረዋል፤ ተመሳሳይ አቀራረብ የሚከተሉ አገሮች አሉ። ነገር ግን የኛ በጣም ቀርፋፋ ነው። የኢንዱስትሪ ዕድገቱ ማለት ነው፣ በተለይም ማኑፋክቸሪንግ። ምክንያቱም ከ30 በመቶ በላይ የኢንዱስትሪ ዘርፍን ዕድገት ላይ ድርሻ ያለው ኮንስትራክሽን ስለሆነ ያ ሲታይ በጣም ብዙ መሠራት አለበት። በጣም ብዙ ይቀረናል” በማለት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የሽግግሩ መዳረሻ ኢንዱስትሪ ቢሆንም የግብርናው ምርትና ምርታማነቱ ማደግ እንደሚገባው የሚያሳስቡት አጥላው፣ ለኢንዱስትሪው በቂና ጥራት ያለው ጥሬ ዕቃ ማጉረስ እንዳለበት ይመክራሉ። ከ80 በመቶ በላይ ዜጎች የኢኮኖሚ ምንጭ ነውና ለኑሮና ሕይወታቸው መሻሻል ግብርናውን ማዘመን አንዱ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑንም ያነሳሉ። “ግብርናውን ለማዘመን አቅም ያለው ገበሬ መፈጠር አለበት” በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በመሬት ማነስና በጉልበት ብክነት መካከል ስላለው አለመጣጣምም እንዲህ ይናገራሉ፦ “ለምሳሌ አንድ ሔክታር ለማረስ አራት ቀን ነው የሚፈጅበት። አራት ጊዜ ቢያርሳት 16 ቀን ነው፤ በዓመት ውስጥ 16 ቀን ለማረም፣ ሌላ 16 ቀን ለማጨድ ቢፈጅበት፥ በዓመት 48 ቀናት ናቸው – ከነቤተሰቡም ከሠራ። ገበሬ መሬቱ ትንሽ ስለሆነች ጉልበቱ ይባክናል”። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባለፉት 40 ዓመታት የተከተልነው የግብርና እና የመሬት አጠቃቀም ስትራቴጂ ውጤት እንደሆነ አስተያየታቸውን ይናገራሉ። ገበሬው መሬቱን ለቆ ሲሔድ “እነጠቃለሁ” በሚል ፍርሐት ተዘዋውሮ ለመሥራት እንደማይፈልግ ገልጸው፥ አሁን የተጀመረው ‘የይዞታ ማረጋገጫ’ ምናልባት የባለቤትነት መብት ስለሚሰጥ የገበሬውን ሥጋት ሊያቃልል እንደሚችል እምነት አላቸው።
ሲያጠቃልሉም “ለዘመናዊ ግብርና ዘመናዊ ግብዓት ያስፈልጋል፤ እነዚህ ግብዓቶች ደግሞ በቀላሉ አይገኙም። አንደኛ በአገር ውስጥ መመረት አለባቸው። ሁሉንም ግብዓቶች ከውጭ ለማምጣት ዋጋው ውድ ነው፤ በገበሬው አቅም። ርካሽ አድርገን ማምረት አለብን። ርካሽ የሆነውን የገበሬ ጉልበት ተጠቅሞ ለምን ዘመናዊ ማዳበሪያ አንሠራም። ኬሚስት፣ ኬሚካል ኢንጂነር፣ ግብርና የምናሥተምረው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት ነገሮችን እንዲያሻሽሉ ነውና መጀመሪያ ማኑፋክቸሪንጉ ለአገራችን ግብርና ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን ለማምረት ዝንባሌ ሊኖረው ይገባል። ገበሬው ደግሞ ከግብርና እየወጣ ሌላ ሥራ መሥራት የሚችልበትን የመቆጠብ አቅም ማጎልበት አለበት”። ግብርናውን በማዘመን በርካታ ወጣት ሥራ ፈላጊዎችን በዛ ማቀፍ እንደሚቻልም ይመክራሉ።

ሰይድ በበኩላቸው ግብርናውን ማዘመን ካልተቻለ የአገር ዕድገትንና ሥራ አጥነትን መቅረፍ የማይታሰብና የማይቻል ነው ባይ ናቸው።

የአገራችን ቀውስና ኢኮኖሚው
በአንድ አገር ላይ በሚፈጠሩ ቀውሶች፣ የመጀመሪያው ተጠቂ ኢንቨስትመንቱ ነው። ከዘርፎች መካከል ደግሞ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት እየመራ የነበረው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተቀዛቅዟል።

ሌላው የሥራ አጥነቱን ችግር ይቀርፋሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው፣ የተወሰኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርቀው መከፈት ሲጀምሩ፣ የፖለቲካ ቀውሱ ጫፍ ላይ ስለደረሰ በሚጠበቅባቸው ፍጥነትና ደረጃ አስተዋፅዖ አላደረጉም። ይህ ደግሞ የሥራ አጥ ቁጥሩ እንዲጨምር ያደርጋል። በአንዳንድ ቦታ ድርጅቱን የሚመሩት የውጭ ዜጋ ሁሉ እስከመገደል ደርሰዋል። እንዲህ ዓይነቱ አስፀያፊ ተግባር ሌላው የኢንቨስትመንቱ ችግር ነው – እንደ ሀቢስ ጌታቸው ዕይታ።

ሌላው፣ ባለፉት አራት ዓመታት በነበረው ቀውስ በየቦታው የነበረው የሥራ እንቅስቃሴ ሲቀዛቀዝ ኢኮኖሚውን እየጎዳ፣ መንግሥት የሚሰበስበውንም የግብር መጠን እየቀነሰ ነው የሔደው። ይህ ደግሞ፣ የአገሪቱ ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል።

ሰይድ ኑሩ (ዶ/ር) “አገር ሰላም ካጣ የመጀመሪያው ተጠቂ ኢንቨስትመንት ነው” ይላሉ። በአጠቃላይ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን መረጃ መሠረት በ2010 የበጀት ዓመት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የዕድገት ምጣኔ ወደ 7.7 በመቶ ለመቀዛቀዙ ከመዋቅራዊ ለውጡ አዝጋሚነት በተጨማሪ የፖለቲካ ቀውሱ አንድ ምክንያት መሆኑን ያስታውቃሉ።

የትምህርት ፖሊሲው
ሰዒድ ኑሩ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ችግር እና የሥራ አጥነት ትሥሥር” ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ሚያዝያ 25/2010 ባካሔደበት ወቅት በዕለቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እየመጣ ያለውን የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ሽግግር ጠቀሜታ ከትምህርት ጥራትና ሥራ አጥነት ጋር በማዛመድ አጭር ጥናት አቅርበዋል። አቅራቢው የሕዝብ ብዛት በመጨመሩ በገጠር ውስን ቢሆንም ድብቅ ሥራ አጥነት (disguised unemployment) ማለትም በ1960፣ 1.2 ሔክታር መሬት የአንድ አርሶ አደር ይዞታ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ያንኑ ተመሳሳይ የመሬት መጠን የአምስት ሰዎች ይዞታ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። ይህ ማለት አራቱ ሰዎች ድብቅ የሆነ ወይም ያልተመዘገበ ሥራ አጥነት ውስጥ ይገኛሉ፤ በከተማም ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት እንደሚስተዋልም ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍና ወጣቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተዘረጋው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተደራሽነት አበረታች ቢሆንም የጥራት ሁኔታ አሁንም ትልቁ ችግር እንደሆነ ቀጥሏል ይላሉ ሰኢድ። ሰዒድ “እያደገ የሚመጣ የሕዝብ ቁጥር ጥራት ባለው ትምህርት ታግዞ ለኤኮኖሚው ግብዓት ካልሆነ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ትሩፋት መሆኑ ቀርቶ ሸክም ወደመሆን ይሸጋገራል” በማለት ተዛምዶውን እና አስከፊ ውጤቱን አብራርተዋል።

በፌደራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ተሻለ ዓለም፥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች ብቁ ባልሆኑ አሠልጣኞች እየተሰጡ መሆኑ፣ ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ሠልጣኞች በስርዓተ ትምህርቱ መሠረት 70 በመቶ የሚሆነውን የትምህርት ጊዜ ሙሉ በሙሉ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲማሩ ባለመደረጉ እና የሥልጠና መስኮች ዓይነት ብዛት ከገበያው ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ ጥራቱን ማሻሻል እንዳልተቻለ ነው የሚናገሩት።

ሌላው የፓናል አቅራቢ የሆኑት ዋና ሌቃ (ዶ/ር) የትምህርት ስርዓታችን ከስትራቴጂ እና ፖሊሲ ዝግጅት በዘለለ የጠራ ፍልስፍና ባለመኖሩ ምክንያት ጥራት መልስ ያላገኘ የዘወትር ችግር እንደሆነ መዝለቁን ያወሳሉ። እንደዋና ገለጻ “ቴክኒክና ሙያ ከክልል ክልል፣ ከተቋም ተቋም የማይመሳሰልና ወጥነት የጎደለው የጥራት ደረጃ መከሰቱ ዘርፉ ሥልጠናውን ከማዳረስ በዘለለ በጠራ መርሕ ላይ ተመሥርቶ እየተተገበረ እንዳልሆነ ማሳያ ነው” በመሆኑም የፖሊሲ አውጪዎችና ምሁራን ለዚህ ግዙፍ ሴክተር በምርምር የታገዘ ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባልም ብለዋል።

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚወስዱት ሥልጠና ከዚያ ወጥተው ሥራ ላይ የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ክሕሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንዳልሆነም ባለሙያው ሞግተዋል።

“ሥልጠናው አሁንም ድረስ ንድፈ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ነው። የሥልጠናው ደረጃ ራሱ ደግሞ በጣም ዝቅ ያለ ነው። ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ ከዝቅተኛው መሥፈርት ውስጥ ከ50 በመቶ በታች ያመጡ እንደሆኑ የመንግሥት ሰነድ ያሳያል። የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ኃላፊዎችም የሚመጡትን ተማሪዎች ምንም ልናደርጋቸው የማንችላቸው ዓይነት ናቸው” በማለት ቅሬታ ያቀርባሉ።

“ቀጣሪዎች ደግሞ ተመራቂዎች የሚፈልጉትን ክሕሎት ወይም አመለካከት ያላቸው አይደሉም ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ። ለእኔ መሠረታዊ ችግር የሚመስለኝ የሥልጠናው ተፈጥሮ ነው። ጥራቱን የጠበቀ ግብዓትና ሒደት ስለሌለው ጥራቱን የጠበቀ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም” ብለዋል።

ሀቢስ “ተመራቂዎችን ሥራ ፍጠሩ ስላልናቸው ሥራ አይፈጥሩም። በሥራ መፍጠር ሒደት ላይ ያሉ እንቅፋቶች ካልተነሱ፣ በደንብ የተሳለጠ ተቋማዊ አሠራር እንዲቋቋም ካልተደረገ፣ ሥራ ፈጠራ ዝም ብሎ በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ።

የሥራ አጥ ምሩቃን መበራከትና በመንግሥት የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ከሠለጠኑበት የትምህርት መስክና ከወሰደው ጊዜ ጋር የማይጣጣሙ እንደሆኑ የሚተቹት ሀቢስ፥ የመንግሥት 70፡30 ፖሊሲ ምሩቃኑን የመቅጠር አቅም ያለው የማኑፋክቸሪንግ ሴክተር መፈጠርን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉን ይጠቁማሉ። በዩኒቨርሲቲዎች ሥልጠናና በገበያው መካከል የላላ ግንኙነት መፈጠሩ የሥራ አጥ ምሩቃንን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉንም ያስረዳሉ::

የዓለም ባንክ ሪፖርት የግሉ ዘርፍ የተለያዩ ማነቆዎች ስላለበት ሥራ በመፍጠር ረገድ የሚጠበቅበትን ያህል እያገዘ እንደማይገኝ አመልክቷል። ዘርፉ ከብድር አቅርቦት ውስንነት፣ ከንግድና ሎጂስቲክስ ውጤታማነት፣ ከአቅርቦት ተደራሽነት፣ ከታክስና ግብር አስተዳደር፣ ከሕግ ማዕቀፎች ተገማችነት፣ ጥራትና ጫና፣ ከውጭ ምንዛሪ፣ ከመሬትና ጫና ከሚያሳርፉ የመግቢያ መሥፈርቶች ምክንያት ማነቆዎች እንዳሉበትም ጠቅሷል።

የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ስኬት አልባነት
ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት ይፋ በሆነው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ለማስፈፀም የፌዴራል መንግሥት እስካሁን ወደ 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ለተጠቃሚዎች በክልሎችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አስፈፃሚነት ቢያቀርብም መመለስ የነበረበት ከግማሽ በላይ ብድር እስካሁን ተመላሽ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ መዘገቧ ይታወሳል።
የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በሚል ዓላማ የፌዴራል መንግሥት 10 ቢሊየን ብር ከመደበ በኋላ ለተጠቃሚዎች የተሰጠው ብድር በተቀመጠለት ጊዜ መሠረት ባለመመለሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረም ይታወቃል።

በፌዴራል ደረጃ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚንስቴር እንዲከታተለው የተደረገው ይህ ብድር ይፋ ከሆነ አንስቶ፥ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እስከ ካለፈው ሩብ በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ወደ 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አሰራጭቷል።
የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የዕቅድ እና ክትትል ዳይሬክተር የሆኑት መነን መለሰ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በአገሪቷ ዴሞክራሲና ለውጥ እንዲመጣ ላበረከትነው አስተዋፅዖ ሽልማታችን ነው በማለት ከ90በመቶ በላይ የሆኑ የፈንዱ ተጠቃሚ የሆኑት ወጣቶች (ተበዳሪዎች) ብድሩን አንመልስም ብለዋል።

“ከዚህ በተጨማሪ ብድሩ ከመሰጠቱ ቀደም ብሎ፤ ለተጠቃሚዎች የገበያ ትሥሥር አለመፈጠሩ፣ የመሥሪያ ቦታ አለመዘጋጀቱ እና ክሕሎታቸውን ለማሳደግ በቂ የሆነ ሥልጠና አለመሰጠቱ ተጠቃሚዎች ውጤታማ ሆነው ብድራቸውን በአግባቡ እንዳይመልሱ እንቅፋት እንደሆነባቸው” ገልጸዋል።

ከወጣቶች ዐሥር ቢሊዮን ብር በጀት ተጠቃሚ ለመሆን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሥራ አጦች መመዝገባቸው ይታወሳል። ኢሕአዴግ ይህንን ዕቅድ ድንገተኛ ደራሽ በሆነ መንገድ በፓርላማ እንዲፀድቅ ያደረገው የተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅ አንዱ መነሻ ምክንያት የወጣቶች ሥራ አጥነት ስለሆነ ሥራ አጥነቱን በመቀነስ ሕዝባዊ አመፁን ማብረድ እችላለሁ ከሚል ስሌት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ።

ይህ 10 ቢሊዮን ብር በእርግጥ የሥራ አጥነት ችግርን ያቃልላል ወይ? መልሱ በአጭሩ አያቃልልም የሚል ይመስላል። ለምን?
ከዚህ ቀደም ለወጣቱ የተደረጉ ተመሳሳይ የገንዘብ ድጎማዎችና ብድሮች ውጤት አላስገኙም። ይህን ለመረዳት ሩቅ መሔድ አያስፈልግም። የ“ጥቃቅንና አነስተኛ” ፕሮጀክቶች ስኬት ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ብቻ ይበቃል።

ከፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ባገኘነው መረጃ መሠረት “በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጠናቀቂያ ላይ ከ700 ሺሕ በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የነበሩ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ በ2008 ወደ ታዳጊና መካከለኛ ደረጃ መሸጋገር የቻሉት 1,586 ናቸው”።

ይህም ማለት ከተጀመሩት የ“ጥቃቅንና መለስተኛ ኢንተርፕራይዞች” ውስጥ 99.8% የሆኑት ከስረዋል፣ ከጀመሩበት ፈቅ ማለት አልቻሉም ወይም ከስመዋል ማለት ነው።

ይህን በማጠናከር ሀቢስ “ጥቃቅንና አነስተኛ” ብድር “ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል ለወጣቱ በመፍጠር፣ ወጣቱን የሙያ ባለቤት በማድረግ፣ አቅም በመፍጠር፣ ለአገር ዕድገትና ልማት በማበርከት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ድጋፍ በማስገኘት ረገድ ጭምር ይህ ነው የሚባል ነገር አለመፈየዱን” ለአዲስ ማለዳ ነግረዋል።

ዐሥር ቢሊዮን የሚለው የገንዘብ መጠን ሥራ አጥ ከሆኑት ወጣቶች ቁጥር ጋር ተገናዝቦ ውጤት ሊያስገኝ በሚችል መንገድ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተደረሰበት አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት አጥላው (ዶ/ር)፣ በጥናት ቢሆን ኖሮ ከገንዘቡ ቀድሞ በመጀመሪያ በፍላጎት (በገበያ) ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶችና በዚህ ውጤት መሠረት የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች በቅድሚያ መታየት እንደነበረባቸው ያመላክታሉ።

እንደ አጥላው (ዶ/ር) ንግግር ይህን በሚመለከት የተደረጉ ጥናቶች፣ የጥናት ውጤቶችም ሆነ ፕሮጀክቶች አልታዩም፣ አልተመዘገቡም። እውነተኛ ጥናት ተደርጎ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች ቢኖሩ ኖሮ በሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው በየጊዜው ውጤታቸው መገምገምና በግምገማው ውጤት መሠረት ቴክኒካዊ፣ አስተዳደራዊና የምርትና የገበያ ማስተካከያዎችን ማድረግ ስለሚያስፈልጋቸው ያንን ዝግጅት በዘገባዎችና በመግለጫዎች እንዲሁም በድርጊት እናይ ነበር።

ይህ 10 ቢሊዮን ብር ለሁሉም ወጣቶች እኩል “ተደራሽ” መሆኑ የተዘገበ መሆኑ ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው። ይህ ገንዘብ እኩል ተደራሽ የሚሆን ከሆነ የተጠቀሱት 3.3 ሚሊዮን ወጣቶች ብቻ ናቸው። በኢትዮጵያ ሥራ አጥ የሆኑት የሚለው ስህተት ነው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ከ18 – 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። 3.3 ሚሊዮን ብቻ የሥራ አጦች ተመዝግበዋል ብሎ ማለት ከተጠቀሰው 25 ሚሊዮን ወጣት ውስጥ 13 በመቶ ብቻ ሥራ አጥ ናቸው ማለት ነው።
ይህ ደግሞ እስካሁን በግልጽና በተደጋጋሚ የተጠቀሰውን ትክክለኛ ስታትስቲክስ በጠቅላላ የሚቃረን ነው። በኢትዮጵያ

ከጠቅላላው ወጣት ከ25በመቶ በላይ ሥራ አጥ እንደሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንዲህም ሆኖ 30 ቢሊዮን ብር ለተጠቀሱት 3.3 ሚሊዮን ወጣቶች ከሙስና ፍፁም በፀዳ መንገድ ይከፋፈል ቢባል እንኳን ለእያንዳንዱ ወጣት የሚደርሰው ብር 2900 ብቻ ነው። ብር 2900 ለአንድ ወጣት ለአንድ ወር ቀለብ ሊሆን ይችላል። አንድን ወጣት በዘላቂነት ራሱን ያስችላል ማለት ግን ከቀልድም ቀልድ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ያወሳሉ።

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሦስት ዓመት በፊት ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች የሆነው የማኅበረሰብ ቁጥር 71 ከመቶው ነበር። እነዚህ ወጣቶች ለአገሪቱ ቀጣይ ዕድገት ጠንካራ መሠረት በመሆናቸው፣ ለወጣቱ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ አስቀድሞ መሥራት የግድ ነው። ዋና ከሚባሉት መካከል የጤናው እና የትምህርት ዘርፎች፣ እንዲሁም፣ ለወጣቱ አስተማማኝ የሆነ የሥራ እድል መፍጠርም ይጠቀሳሉ።

ኢኮኖሚችን እንዲያድግ
ሰይድ ኑሩ (ዶ/ር) የሥራ አጥ ቁጥሩን ለመቀነስና ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ የመጀመሪያውና ለማንም ግልጽ የሆነው ጉዳይ በአገራችን ሰላም ማስፈን እንደሆነ ይመክራሉ። የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት አንዱ የሆነው አዳም ስሚዝ አንድን አገር ከፍፁም ድህነት ወደ ብልጽግና ማማ ለማሸጋገር ከሰላም፣ ቀለል ካለ ታክስና የታክስ ስርዓት፣ እንዲሁም ከፍትሕና ቅቡልነት ካለው የሠመረ አመራር የሚቀድም ነገር እንደሌለ እና ሌሎች ጉዳዮች በራሳቸው ጊዜ መሥመር እንደሚይዙ ማስተማሩን የሚጠቅሱት ሀቢስ ጌታቸው አገር ሰላም ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገቶች በዕቅድና በጥናት መመራትና መሠራት ከተቻለ ያደጉት አገራት የደረሱበት ደረጃ የማይደረስበት ምክንያት የለም ይላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here