‘አፍሪ ሄልዝ’ ቴሌቪዥን ጣቢያ በከፊል ተሸጠ

0
429

በሕክምና፣ በመገናኛ ብዙኃን አውታር ባለሙያዎች እና በባለሀብቶች በ40 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ʻአፍሪ ሄልዝʼ የቴሌቪዥን ጣቢያ 50 በመቶ ድርሻው ለሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተሸጠ።

አፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን ሲቋቋም ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው ሰዎች የራሳቸውን ጤና በራሳቸው መንከባከብ እንዲችሉ ትክክለኛ የጤና መረጃዎችን ማቅረብና ጤናማ ማኅበረሰብን መፍጠርን ነበር። ሆኖም እንደታሰበው ስላልሆነለት እና ጣቢያው ባለው ውስን ፕሮግራሞች ምክንያት መቀጠል የሚያስችለው ደረጃ ላይ ባለመሆኑ ሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን 50 በመቶ የአክስዮን ድርሻውን በመግዛት የቴሌቪዥኑን የይዘት ድርሻ 90 በመቶ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንዲሸፍኑት ሊያደርግ መሆኑ ተሰምቷል።

በጤና ነክ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚያሰራጨው የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና መስሪያ ቤቱን ዱባይ ያደረገም ነው። ጣቢያው በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በመክፈት የፕሮዳክሽን ኩባንያ ወይም ልዩ ልዩ የይዘት ፕሮግራሞችን መቅረፅ ማዘጋጀት የሚያስችለውን ሥራ መጀመሩም ይታወሳል።

የቴሌቪዥኑን የ50 በመቶ ድርሻ ሽያጭ ውል ኹለቱ ወገኖች ባለፈው ወር መፈራረማቸውንም ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ጣቢያው ግማሽ አክሲዮኑን መሸጡን ተከትሎም ʻአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥንʼ ይባል የነበረውን የቀድሞ ስያሜውን በመቀየር ʻአፍሪ ቲቪʼ በሚል ሥያሜ የቀየረ ሲሆነ አርማ ወይም መለያ ቅርፅ ቅያሬም አድርጓል።

የ50 በመቶ ድርሻ ገዢው ሐበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ዐውደ ርዕዮችን የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ በተጨማሪም የዓለም ዐቀፍ አገልግሎት ሰጪ የግል ተቋም ሆኖ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ዘርፍ ተሰማርቷል። በገበያ ትስስር የተለያዩ ኹነቶችን በማዘጋጀትም ይታወቃል። ተቋሙ መቀመጫውን አዲስ አበባ ላይ በማድረግ በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ የንግድ ማዕከላት በሆኑ ከተሞች ቅርንጫፎችን በመክፈትና የገበያ ትስስር ባለሙያዎችን በማሠማራት እየሠራ እንደሚገኝም ይነገርለታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here