ወርቅ አምርቶ በአገር ውስጥና በውጭ መሸጥ የሚያስችል ረቂቅ ቀረበ

0
1147

ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ ከማቅረብ በዘለለ ምርቱን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ረቂቅ ቀረበ። በባሕላዊ መንገድ የሚመረተውን ወርቅ በመግዛት ለብሔራዊ ባንክ ያቀርቡ የነበሩ የንግድ ፈቃድ ባለቤቶች ምርታቸውን አገር ውስጥና ውጪ በመላክ መሸጥ እንደሚችሉ ረቂቁ ላይ ተብራርቷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በባሕላዊና ዘመናዊ መንገድ ወርቅ እንደሚመረት የታወቀ ሲሆን በዘመናዊ መንገድ የሚመረተው ወርቅ አምራቾች የመላክም ፈቃድ ስለሚኖራቸው በቀጥታ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን በባሕላዊ መንገድ የሚመረተው ወርቅ ከተሰበሰበ በኋላ በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ ይቀርብ እንደነበር ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ይሁን እንጂ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ወደ ውጪ የመላክ መብትን ይሰጣል።

በዚሁ ረቂቅ ላይ የፌደራል መንግሥት ሥልጣን የነበረውን የዕደ ጥበብ ሥራ ፈቃድ፣ አዲስ የተጨመረው የማቅለጥ ፈቃድ እና የንግድ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የመስጠትና የማስተዳደር ሥልጣንና ኃላፊነት ለክልሎችም እንደሚሰጥ ታውቋል።
የማዕድናት ግብይት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ለማወቅ እንደተቻለው ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መሰረት ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡን የማስተዳደር ሥልጣኑ በግልፅ ያልተደነገገ መሆኑ ይታወቃል። ማስተዳደር ሥልጣኑ በግልፅ አይታወቅ እንጂ እስካሁን ባለው አሰራር በፌደራል መንግሥት ብቻ ተወስኖ የቆየ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ እንደተካተተው ፈቃድ ሰጪው ባለሥልጣን እንደ አግባቡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ክልል አካል እንደሚሆን የተደነገገ ሲሆን፥ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጪው አካል ደግሞ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ወይም የማዕድን ዘርፍ ሥራ የሚመለከተው የክልል አካል ይሆናል።

በረቂቁ እንደተብራራው ከከበሩ፣ በከፊል ከከበሩ ወይም ከብረት ነክ ማዕድናት በማጠንከር ወይም በመቅረፅ ወይም የኹለቱን ውጤት አጣምሮ ሌላ ቅርፅ በማስያዝ ማዕድናት የመጨረሻ ቅርፃቸውን እንዲይዙ የማድረግ ሒደትን ዕደ ጥበብ በሚል ጥቅል ማዕቀፍ ውስጥ ገብተዋል። በዚህም መሰረት የማንጠር ፈቃድ፣ የመቅረፅ ፈቃድ፣ የማጣመር ፈቃድ በሚል በሦስት የፍቃድ ዘርፎች ተዘርዝረዋል። ይህንም ተከትሎ ወርቅ ወይም ብርን ሕግ በሚወስነው መሠረት የመግዛት፣ የመያዝ፣ የማጓጓዝ እና ምርቱን በአገር ውስጥና በውጭ አገር መሸጥ መብትን ይሰጣል። በኹለተኛ ደረጃ ተቀመጠው የመቅረፅ ፈቃድ ሥር ደግሞ ከብርና ፕላቲኒየም ውጪ ያሉትን የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናትን የመግዛት፣ የመያዝና የመቅረፅ ሥራ የማከናወንና ምርቱን በአገር ውስጥና በውጭ አገር የመሸጥ መብትን ይሰጣል።

ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ያለቀላቸው ማዕድናትን የመግዛት፣ የማጓጓዝ፣ በማጣመር ጌጣጌጥ ሠርቶ ምርቱን በአገር ውስጥና በውጭ አገር የመሸጥ መብት የሚሸጥ ሲሆን፤ ባለፈቃድ ጥሬ ማዕድናት ገዝቶ ጌጣጌጥ መሥራትና መሸጥ ግን ክልክል መሆኑን በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በነባሩ አዋጅ ያልነበረው እና ማዕድንን በጥሬው ከመላክ ባሻገር እሴት የተጨመረበት ማዕድን ስለመላክ ያላካተተ በመሆኑ በአዲሱ ረቂቅ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህም መሰረት በቅርቡ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ጨረታ የወጣው የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ ድርጅት እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ለመላክ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በነባሩ አዋጅ የላኪነት ፈቀድ ባለቤት ማዕድን ሲገዛና ሲሸጥ ሕጋዊ ደረሰኝ መጠቀምን በተመለከተ በግልፅ ያለተደነገገበት አካሔድ መኖሩን የሚጠቅሰው አዋጁ፤ በአዲሱ አዋጅ ላይ ግን በማዕድናት ግዥ እና ሽያጭ ወቅት የላኪነት ፈቃድ ያለው ግለሰብ ደረሰኝ መጠቀም እንደሚኖርበት የሚገልፅ ሐሳብ እንዲጨመር ተደርጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here