የአክስዮን ማኅበራትን የሥነ ምግባር ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ጥናት ቀረበ

0
640

በርካታ የአክሲዮን ማኅበራት በንግድ ሕጉ መሰረት ማኅበራቸውን ኦዲት ባለማስደረግና በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባለማጸደቅ ከፍተኛ የሀብት ብክነት እንዲኖር ማድረጋቸውን የፌደራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። በአክሲዮን ማኅበራት ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል እና ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራቶችን ለማከናወን የሚያስችል ጥናታዊ ጽሑፍ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ትብብር ተሰርቶ መጠናቀቁም ታውቋል።

በጥናታዊ ጽሑፉ ዙሪያ ከአክሲዮን ማኅበራት ጋር እሁድ፣ መጋቢት 29 ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በቀጣይ ችግሮቹን ለመቅረፍ ወደሚያስችል ተግባር እንደሚገባ ከፌደራል ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በጥናታዊው ጽሑፉ የማኅበራቱ መስራቾች የማኅበሩን መግለጫ (ʻፕሮስፔክተስʼ) አዘጋጅቶ አለማቅረብ ችግር መኖሩን፣ አንዳንድ መሥራቾች የሚያቀርቡት የማህበሩ መግለጫ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ እና ትክክለኛ አለመሆን፣ የማኅበሩ መሥራቾች በሕጉ መሠረት ከመዝጋቢው አካል የጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኙ አማላይ ማስታወቂያዎችን በማስነገር ገንዘብ የሚሰበስቡበት ሁኔታዎች መኖሩን አስታውቋል፣ አልፎ አልፎ አንዳንድ የአክስዮን ማኅበራት በሕግ የተቀመጡትን መስፈርቶች ሳያሟሉ ገንዘብ ከሕዝብ በመሰብሰብና ገንዘቡን ይዞ በመሰወር በሕዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መሆኑ እንደተግዳሮት ከተነሱት መካከል ናቸው።

የአክስዮን ማኅበራት ምዝገባ በክልሎችም ጭምር እንዲካሔድ በመፈቀዱና ከክልሎችም ሥራውን ወደ ወረዳ ወይም ወደ ከተማ ቀበሌ በማውረዳቸው ከልምድ ዕጥረት የተነሳ አልፎ አልፎ ከሕግ ውጪ ምዝገባ እንደሚፈጸም ያስታወቀው ሰነዱ፣ አንዳንድ የአክሲዮን ማኅበራት የምስረታ ወቅት የተራዘመ መሆኑ ከተመሰረቱም በኃላ ቶሎ ወደ ሥራ ስለማይገቡና ያለአግባብ ወጪ በማውጣት የገንዘብ ብክነት እንደሚስተዋልባቸው አስታውቋል።

በልዩ ልዩ ምክንያቶች በመሥራች አባላትና በሌሎች አባላት መካከል ከመስራችነት ጥቅም እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች አንፃር የሚከሰቱ ግጭቶች መኖራቸውን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ አንዳንድ አባላት ከመነሻው የቦርድ አባል በመሆንና የአክሲዮን ማህበሩን ሥራዎች ከራሳቸው ሥራ ጋር በማገናኘት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አስበው ስለሚገቡና የንግድ ህጉም በግልፅ የቦርድ አባላት የአገልግሎት ጊዜን ያልገደበ በመሆኑ በድጋሜ ካልተመረጡ ደግሞ ብጥብጥ የሚፈጥሩ መሆናቸውን አስቀምጧል።

አክሲዮን ማኅበራት ለመመስረት እና ውጤታማ ለመሆን የሚሠራው ሥራ ሀብት እና ራዕይ አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም በብዙ የአክሲዮን ማኅበራት መሥራቾች ላይ አክሲዮን ማኅበራትን ስለመመስረት ስራው እና ሀብቱ እንጂ በሚመሰረቱት አክሲዮን ማኅበራት ላይ ያላቸው ራዕይ አናሳ መሆን ለአክሲዮን ማህበራት ውጤታማ አለመሆን እንደምክንያት ሲቀርብ ይስተዋላል።
በዓይነት የሚደረገው መዋጮ ማኅበሩ ከተመሰረተ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ወደ ማኅበሩ ንብረትነት መዞር እንዳለባቸው ባለመደንገጉ ችግሮች እየተስተዋሉ ስለመሆኑም ተነስቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here