ካንሰር ሊያስከትሉ የሚችሉ 1600 ቶን ፀረ አረም ኬሚካሎች በኹለት ክልሎች ተገኙ

0
1328
  • ኬሚካሉን ለማስወገድ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገምቷል

የግብርና ሚኒስቴር ባካሔደው ኦዲት ጊዜው ያለፈበት 1600 ቶን ፀረ አረም ኬሚካሎች በኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች መገኘታቸው ተጠቆመ። ለባለፉት 13 ዓመታት ያልተወገዱት ፀረ አረም ኬሚካሎች ለጤና ጠንቅ በመሆናቸው ለካንሰር ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው በዓለም ጤና ድርጅት ስምምነቶች መሰረት ፀረ አረም በተመረተ በኹለት ዓመት ውስጥ መወገድ ያለበት ቢሆንም ከ1998 አንስቶ ያለፈባቸው ፀረ አረሞች እንዳልተወገደ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ቀደም በተወገዱበት ወቅት ከዓለም ጤና ድርጅት በተገኘ 15 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ወደ ውጭ በመላክ ወደ 1 ሺሕ ቶን ፀረ አረም ኬሚካሎችን ለማስወገድ ተችሎ ነበር። ነገር ግን ተገቢው ትኩረት በመንግሥት ባለመሰጠቱና ከገንዘብ እጥረት ጋር ተያይዞ ይህ ሊቆይ አልቻለም። በዚህም የተነሳ በኹለት ክፍሎች ብቻ ያለውን 1600 ቶን ፀረ አረም ለማስወገድ ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር ሊወስድ እንደሚችል ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ሳይንስና የጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ሆኑት ገብረኪዳን አስረሳኸኝ እንደገለፁት ለጤና በከፍተኛ ደረጃ ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎች በተለየያዩ ቦታዎች እንደሚገኙና በኢትዮጵያ ማስወገድ የሚቻልባቸው መሣሪያዎች ባለመኖሩ ለተበላሹት ፀረ አረሞች መከማቸት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

በሰዓቱ ባለመወገዳቸው ምክንያት የሆነው ዶላር ዋጋ መጨመርንና የዋጋ ግሽበት ከፍ ማለቱን ተከትሎ መንግሥት ለማስወገድ የሚያስፈልገውን ወጪ ከፍ አድርጎታል ሲሉ ገብረኪዳን ተናግረዋል። በተጨማሪም የግብርና ሚኒስትር የሆኑት ኡመር ሁሴን ባለፈው ማክሰኞ፣ ሚያዚያ 1 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስምንት ወራት አፈፃፀም ባቀረቡበት ወቅት የፀረ ተባይ ኬሚካልን ጨምሮ ሌሎች የንብረት ኦዲት ግኝቶች የመለየት፣ የማደራጀትና የማስወገድ ሥራዎች በተጠናከረ መንገድ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ የሚወገዱትን ፀረ አረም የመለየቱ ሥራ ከኦሮሚያና ጋምቤላ ውጪ አልተጠናቀቀም።

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ የፀረ አረም ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲቋቋም ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ጥያቄ ማቅረቡን ማወቅ ተችሏል። በተለይ ባለስልጣኑ ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች ከመቆጣጠር አንፃር ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል። ባለሥልጣኑ የራሱ ቤተ ሙከራ የሚኖረው ሲሆን ግንባታውን ለማካሔድ ግብርና ሚኒስቴር ጨረታ አውጥቶ ድርጅቶችን በማወዳደር ላይ ነው።

ኢትዮጵያ በዓመት ከዐሥር ሚሊዮን ሊትር በላይ ፀረ አረም ኬሚካሎች የሚያስፈልጓት ቢሆንም ባለፈው ዓመት ከውጪ የገባው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ብቻ ነበር። ይህ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ወደ አገር ውስጥ ከገባው ጋር ሲነፃፀር በኹለት እጥፍ ያነሰ ነው። ይህም አሁን ለኮንትሮባንድ ንግድ መጋለጡ ጊዜ ያለፈባቸው ፀረ አረም መድኃኒቶች በሥራ ላይ እንዲውሉ ክፍተት እንደፈጠረ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here