ሕዝባዊ አመፅን ለመቆጣጠር ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር

0
775

የዕድገቱ መጠን የቱንም ያህል እያወዛገበ ቢሆንም፥ ኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የዓለማችን አገራት ተርታ ተሰልፋለች። ይሁን እንጂ ባለፉት አራት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ተቃውሞ እና የተከተለው ለውጥ የዕድገት ፍጥነቱን እያቀዛቀዘው ይገኛል። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ላየችው ሕዝባዊ ተቃውሞ የዳረጋት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ፍትሐዊ አለመሆን በአንድ በኩል እና ከፍተኛ የሥራ አጥነት በሌላ በኩል ነው።

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሦስት ዓመት በፊት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑት ዜጎች ቁጥር 71 ከመቶ መሆኑ ተገልጾ ነበር። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፥ ከነዚህም ውስጥ በኦፊሴላዊ ግምት ብቻ የ16.5 በመቶ የሚያድግ የሥራ አጥነት እንዳለ ይነገራል። ይሁንና ይህ የሚያመለክተው ብዙውን ጊዜ በከተማ ያሉ የሥራ አጦችን ነው። ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ ለእርሻ የሚሆነው መሬት በውርስ እየተሸነሸነ በመመናመኑ ምክንያት ወጣቶች የሚያርሱት መሬት በጣም ትንሽ ነው። በዚያ ላይ በአገራችን የእርሻ ሥራ የሚከናወነው ወቅት ጠብቆ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ሥራ መፍታታቸው የተለመደ ነው። ስለዚህ የሥራ አጦች (unemployed) እና ከአቅማቸው በታች እየሠሩ ያሉ (underemployed) ወጣቶች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው።

እንደ ዓለም ባንክ ግምት በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 600 ሺሕ ሰዎች አምራች ኀይል የምንለውን የዕድሜ ክልል (15-64) ይቀላቀላሉ፡፡ የ‘አፍሪካ ግሮውዝ ኢኒሼቲቭ’ ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት ክርስቲና ጎሉብስኪ “Trends in Ethiopia’s Dynamic Labour market” በሚለው ጽሑፋቸው፥ በኢትዮጵያ ስላለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ሽግግር እና የሥራ ዕድል ሁኔታ በሰጡት ገለጻ እንደመነሻ ኢትዮጵያን ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ተርታ ይመድቡና በመቀጠልም “ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በፈጣን ዕድገት ላይ ቢገኝም በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው አምራች ኀይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም” ብለዋል።

የሥራ አጥነት ለሕዝባዊ አመፅ ዋነኛ ገፊ ምክንያት ነው። በኢትዮጵያ የታዩት ያለፉት ዓመታት አመፆችም ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተሳተፉባቸው ነበሩ። ይሁንና አሁን የፖለቲካ ለውጥ እየታየ ባለበት ሰዓት ውስጥ ሥር ነቀል የምጣኔ ሀብት ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ምክንያት ኢኮኖሚውም አልተነቃቃም፣ የሥራ አጥነት ችግሩም አልተቀረፈም። ይህም ሌላ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን መገመት አይቸግርም።

የሥራ አጥነቱ ችግር በሁሉም ዕድሜ ክልል ያለ ቢሆንም በወጣቶች ዘንድ ይጨምራል። በጥቅሉ 16.5 በመቶ የሆነው የሥራ አጥነት ምጣኔ ዕድገት፥ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 24 በሆኑ ወጣቶች ዘንድ 25.8 በመቶ መሆኑን ሰዒድ ኑሩ (ዶ/ር) ይናገራሉ። እዚህ ላይ የትምህርት ስርዓቱም የራሱን አሉታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይኸውም ሥራ መፍጠር የማይችሉ ብዙ ሺሕዎችን ዩኒቨርሲቲዎች ቢያስመርቁም እነርሱን መቅጠር የሚችል ኢንዱስትሪ ግን አልተዘጋጀም። በዚያ ላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ባልተጠናከረበት ሁኔታ በ70፡30 ምጥጥን ኢንጂነሮችን እና ሌሎችን ማስመረቅ ካለው የሥራ ዕድል በላይ የሰው ኀይል ገበያው ላይ ማፍሰስ በመሆኑ፥ በድሀ አገር መዋዕለ ንዋይ የተማሩ ዜጎች በሥራ ፍለጋ ለዓመታት እንዲንከራተቱ ሰበብ ሆኗል።

የወጣቶች ቁጥር በፍጥነት መጨመር፣ ደካማ የትምህርት ስርዓት፣ የአምራች ዘርፉ ዕድገት መቀጨጭ፣ የሥራ አጥነት እና ሕዝባዊ አመፆች እርስ በርስ ግንኙነት አላቸው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በከፍተኛ መጠን እያደገ ያለው የወጣቶች ቁጥር በርካታ የሰው ኀይል ወደ ሥራ ገበታ የሚገፋቸው በመሆኑ ምክንያት የሥራ ፈላጊው ቁጥርም እንዲሁ ያሻቅባል። የትምህርት ስርዓቱ የሚያስመርቃቸው ወጣቶች ደግሞ ለሥራ ፈጠራ ብቁ አይደሉም። ብቁ ቢሆኑም የሰው ኀይል ገበያው በጥቅሉ ሥራ ፈጠራን የሚየበረታታ አይደለም። የማምረቻ ዘርፉ በሥራ ፈላጊው እና በዩንቨርሲቲ ምሩቆቹ ቁጥር ዕድገት አንፃር ሲታይ በጣም ቀርፋፋ በመሆኑ ምክንያት የሚያስፈልገውን ያክል የሥራ ዕድል እየፈጠረ አይደለም። በዚህም ምክንያት የሥራ አጥነት ተበራክቷል። ሥራ አጥ ወጣቶች ደግሞ በግል ብሶታቸውም ይሁን በፖለቲካ ልኂቃን ግፊት ለሕዝባዊ አመፅ የተመቻቹ ናቸው።

አዲስ ማለዳ መንግሥት ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት የሰጠውን በጎ ምላሽ የሚመጥን ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ላይ አትኩሮ መሥራት ካልቻለ፥ ሌላ ሕዝባዊ አመፅ መከተሉ እና አሁን የታየውን የለውጥ ድባብ የሚያደፈርስ ነገር መፈጠሩ አይቀሬ መሆኑን ታሳስባለች። ከእያንዳንዱ ሕዝበዊ አመፅ በስተጀርባም ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች አሉ። ስለሆነም አስቸኳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here