ዐቃቤ ሕግ የ1077 ነጋዴዎች ክስ ማቋረጡን ገቢዎች ሚኒስቴር አልደገፈም

0
677

የአዲስ አበባ ግብር ከፋይ የሆኑና ጉዳያቸው በፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ እና በፍርድ ቤት የተያዙ 1077 ነጋዴዎች ክስ እንዲቋረጡ ወሳኔ መተላለፉን የገቢዎች ሚኒስቴር ተቃወመ።

በምክትል ከንቲባው ታከለ ኡማ የሚመራው አስተዳደሩ የነጋዴዎች ክስ እንዲቋረጥና ፍርድ የተሰጣቸው በምህረት እንዲለቀቁ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ምላሹን እንዲሠጥ የተጠየቀው ሚኒስቴሩ ተገቢ እርምጃ አይደለም ሲል ውሳኔ ሐሳቡን ኮንኗል።

በመስተዳደሩ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በዐቃቤ ሕጉ ባለፈው ሐሙስ፣ ሚያዚያ 3 ይሁንታ ቢያገኝም ሚኒስቴሩ ከኹለት ሳምንት በፊት በጻፈው ደብዳቤ ሕገ ወጥነት ያበረታታል በማለት ሥጋቱን አሳውቆ ነበር።

በገቢዎች ሚኒስትር አዳነች አበቤ የተፈረመው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ምህረት ከተደረገላቸው ነጋዴዎች መካከል የተጨማሪ እሴት ታክስ ዕዳ ያለባቸው ግብር ከፋዮች የተካተቱ ሲሆን ይህ መሆኑ ደግሞ መስተዳደሩ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ካለው ሥልጣንና የሥራ ድርሻ ጋር የሚፃረር ነው።

የተጨማሪ እሴት ታክስ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ነው ብሎ ያወሳው ደብዳቤው ምህረቱ መደረግ ያለበት በገንዘብ ሚኒስቴር ነው ብሏል።

በተጨማሪም ምህረት ከተደረገ በአገር ዐቀፍ ሁሉንም ነጋዴዎችን ባማከለ መልኩ መሆን እንዳለበትና የመስተዳደሩ እርምጃ ግን የታክስ ማጭበርበርን የሚያበረታታ እንደሆነ ሚኒስቴሩ በደብዳቤው ገልጿል።

ለአብነትም በፌዴራል መንግሥት ተመዝገበው ከሚገኙት ግብር ከፋዮች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኪሳራ የሚያሳውቁ እንጂ ግብር የማይከፍሉ መሆናቸውን የገለፀው ሚኒስቴሩ ያለፈው ስድስት ወር ሪፖርት አያይዞ ገልጿል። ይህም የሕግ ማስከበር ክፍተት መኖሩን የሚያሳይ ማረጋገጫ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከዚህ ቀደም ዐቃቤ ሕግ ለደረጃ 1 ተቋራጮቸ ተመሳሳይ የክስ ማቋረጥ ተደረጉን ተከትሎ አስተያየቱን የተጠየቀው ሚኒስቴሩ ተቃውሞውን በደብዳቤ ገልፆ ነበር። በተጨማሪም ውሳኔው በወንጀል ምርመራ ቢሮ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
የዛሬ ኹለት ወር ገደማ የገቢዎች ሚኒስቴሯ አዳነች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ግብር ከፋዮች ያለአግባብ ግብር ከተጣለባቸው አልያም ክስ ከተመሰረተባቸው ቅሬታቸው እንደሚስተናገድ ገልፀው ነበር። ነገር ግን ከዚህ ውጪ ተቋርጦ የተገኘ መዝገብ ቢኖር እንኳን ደግሞ እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጠው ነበር።

ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ለ1077 የተደረገው የታክስ ምህረት እጅግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን የያዙ ሆነው ያለ ደረሰኝ እና ከዋጋ በታች ግብይት የተከናወነባቸው፣ ደረሰኝ ሳይዙ ዲኪላራይሶን ሳይኖራቸው የተለያዩ ዕቃዎች በንግድ ሱቃቸው የተገኘባቸው፣ የባለሥልጣኑን ሥራ በማሰናከል እና ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣርያ አድራሻ ጋር የተፈፀሙ ጥፋቶች በመሆናቸው ምህረቱ ችግር አያመጣም ብሏል።

እነዚህ ወንጀሎች ከአፈፃፀማቸው፣ ከያዙት የገንዘብ መጠን አነስተኛ መሆን እንዲሁም ከተያዘው የታክስ ሪፎርም እና ከግለሰቦቹ የኢኮኖሚ አቅም አንፃር በምርመራ እና በፍርድ ቤት ደረጃ ያሉ በሙሉ እንዲቋረጡ ቢደረጉ በመንግሥት እና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዝቅተኛ በመሆኑ ክሳቸው ተቋርጦ ወደ ሥራ ቢገቡ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ አዎንታዊ ሲል አክሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here