የምኒልክ ቤተ መንግሥት!

0
711

ከሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን አውታሮች መከራከሪያ ሆነው ከሰነበቱትና የአሜሪካን ኤምባሲም ካስቆጡት መካከል በኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚንስትሩ መቀመጫ ሆኖ የሚገለግለው የምኒልክ ቤተ መንግሥት ይገኝበታል። የነገሩ መነሻ የኋይት ሀውስ አማካሪዋና የትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ጉብኝት ሲሆን አማካሪዋ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መምከሯ ነው። ምክክሩን በተመለከተ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ስለውይይቱ ትኩረት ጽፏል።
በኢቫንካ የተመራው ልዑክ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ሲወያይ አሜሪካ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ፣ ብልፅግናና መረጋጋት እሴቶች እንዲዳብሩ ድጋፍ እንደምታደርግ አንስቷል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔያቸውን 50 በመቶ ሴቶች ማድረጋቸውን ያደነቀችው አሜሪካ የሴቶች ምጣኔ ሀብታዊ አቅም እንዲፈረጥም እገዛዋን እንደምታጠናክር አረጋግጣለች።

ይህን የሚያትተው የኤምባሲው ጽሑፍ ታዲያ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በተለይም በፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች በኩል ኹለት ጎራ ከፍሎ ማከራከሩ ለአሜሪካ አልተዋጠላትም። ኤምባሲው ʻየምኒልክ ቤተ መንግሥት ማለት የለበትምʼ እና ʻበዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን የተሠራ እስከሆነ ድረስ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ቢባል ተገቢ ነውʼ የሚለው አከራክሯል።

ጉዳዩን ያስተዋለው ኤምባሲው የፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረውን “የምኒልክ ቤተመንግሥት” የሚል ሐረግ አውጥቶ “ያረምኩት ስለተሳሳትኩ አይደለም” ሲል አቋሙን አሳውቋል። ቤተ መንግሥቱ በልምድም የምኒልክ ቤተ መንግሥት እንደሚባል አስምሮበት “ከሐሳብ ይልቅ ቃል ላይ መንጠልጠላችሁን ተዉ” ሲልም ገስጿል። አክሎም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በመካሔድ ላይ ባለው የፖለቲካ ሒደት ዙሪያ ያላችሁ አተያይ ምንም ይሁን ምን “ታሪክን ልትቀይሩ አትችሉም” ያለ ሲሆን መጪውን ጊዜ ግን የተሻለ ልታደርጉ ትችላላችሁ ሲልም መክሯል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here