ኢትዮጵያ ከግብር የሚሰበሰበውን መጠን ለማሳደግ ተግባራዊ እያደረገች ያለችውን ዘመቻ የግብሩን መሰረት ከማስፋት ይልቅ የግብር መጠንን በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ሳምሶን ኃይሉ ይተቻሉ። እንደዚህ ዓይነት አካሔድ የንግድና መዋዕለ ነዋይ ፍሰት መቀዛቀዝ ብሎም የምጣኔ ሀብት ዕድገት መቀነስ ሊያስከትል ስለሚችል ትክክለኛ ፖሊሲ መቅረጽንና ፍትሐዊ አተገባበር ማስፈንን ሳምሶን እንደመፍትሔ አቅርበዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት መንግሥት የሚሰበስበውን የግብር መጠን ለማሳደግ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ዘመቻ ጀምሯል። ይህ ዘመቻ በዋነኝነት ግብ ያደረገው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ ደግሞ ከሦስት ዓመት በፊት የተነሳውን ሕዝባዊ አመፅ ተከትሎ እየቀነሰ የመጣውን የግብር መጠን ወደ ነበረበት ደረጃ መመለስና ለጥቆም ሌሎች ድርሻ ከሳሃራ በታች ያሉ አገሮች ከደረሱበት ደረጃ ማድረስ ነው።
ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሰበሰበው የግብር መጠን ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆነ ቅናሽ አሳይቷል። ያለፈውን ዓመት የግብር መጠን ብንመለከት እንኳን የተሰበሰበው ግብር በ51 ቢሊዮን ብር ከዕቅዱ ያንሳል። በዚህም የተነሳ ከግብር የሚገኘው ገንዘብ ከዓመታዊ ጥቅል ምርት ጋር ሲነፃፅር በ2007 ከነበረው ከ12 ነጥብ 7 በመቶ በ2010 ወደ 10 ነጥብ 7 በመቶ ሊወርድ ችሏል።
በፖለቲካ አለማረጋጋት ውስጥ የሚገኙ አገራት በግብር መልክ የሚሰበስቡት የገንዘብ መጠን ቅናሽ ሊያሳይ ይችላል። ምክንያቱም የንግድ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ስለሚስተጓጎሉ ፋብሪካዎች የጥሬ እቃ አቅርቦት ማነስ ያጋጥማቸዋል። በተጨማሪም አገልግሎት ሰጪዎችና ነጋዴዎች በአግባቡ ኅብረተሰቡን ማገልገል ያቅታቸዋል። የተለያዮ አገራት ተሞክሮ እንደሚያስረዳው በፖለቲካ አለማረጋጋት ውስጥ የሚያልፉ አገራት ከግብር የሚገኙት ገንዘብ ከዓመታዊ ጥቅል ምርታቸው ጋር ሲነፃፅር ከአንድ እስከ ሦስት በመቶ ቅናሽ እንደሚያሳይ ነው።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተስተዋለው የግብር መጠን መቀነስ ሊያስገርም አይገባም። ሆኖም ግን አንፃራዊ ሰላም ሲሰፍን መንግሥት የግብር መጠኑን ለመጨመር እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት እሙን ነው። ምክንያቱም ግብር ለአንድ አገር ምጣኔ ሀብት እንደምሶሶ ስለሚቆጠር ነው። ከግብር የሚገኘው ገንዘብ ሕዝብን ለማስተዳደር፣ አገሪቱን ከጠላት ለመጠበቅ፣ እንደ ጤናና ትምህርት የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ለማዳረስና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመገንባት ስለሚረዳ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ አገሮች የግብር አስተዋፅዖ የትየለሌ ነው።
በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት በግብር መልክ በየዓመቱ የሚሰበሰበውን የገንዘብ መጠን ለመጨመር የተለያዩ ሥራዎችን በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት አከናውኗል። የኤሌክትሮኒክስ የሽያጭ ምዝገባ ማስተዋወቅ፣ የተጨማሪ እሴት ግብር፣ የግብር ከፋዮች መለያ ቁጥር እና የአንድ መስኮት አገልግሎት (Single-Window System) ሊጠቀሱ ይችላሉ። ስለሆነም በግብር መልክ በየዓመቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ በኢትዮጵያ ጭማሬ አሳይቷል።
ለምሳሌ በ2003 ጠቅላላ በግብር መልክ የተሰበሰበ ገንዘብ 50 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ነበረ። በ2007 የግብር መጠኑ 156 በመቶ አድጎ 128 ቢሊዮን ብር ደርሶል። ስለሆነም የግብር መጠን ከጠቅላላው ዓመታዊ ጥቅል ምርት ጋር ሲነፃፅር ያለው ድርሻም በ2003 ከነበረው 6 ነጥብ 7 በመቶ ጨምሮ በ2007 አስራ ኹለት ነጥብ 7 በመቶ ደርሶ ነበር። የፖለቲካ አለማረጋጋቱ መንግሥት ያስቀመጠው የግብር መጠን ከጠቅላላው ዓመታዊ ጥቅል ምርት ጋር ሲነፃፅር ያለው ድርሻ ከሳሃራ በታች ያሉ አገሮች በአማካኝ ከደረሱበት 18 በመቶ የማድረስ እቅድ አሰናክሎታል ብለው ባለሥልጣናት ይሟገታሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች በዘመቻም ሆነ የሕግና የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ይህንን እቅድ ለማሳካት እንደሚጥሩ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።
በእኔ አመለካከት እቅዱ ራሱ ነባራዊ የአገሪቱን ሁኔታ ያላገነዘበ ከመሆኑም በላይ ግቡ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የሚከተለው ነባራዊ ሁኔታዎችን የማያገናዝብና ትክክለኛ ያልሆነ የግብር ፖሊሲን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ይህንን ግምገማዬን ለማስረዳት በተለይም ከሳሃራ በታች ያሉ አገሮች የሚገኙባቸውን ደረጃዎች በማነፃፀር ትንታኔዬን አስቀምጣለው።
በተለያዩ አገሮች እንደሚስተዋለው ግብር በዋናኝነት የሚሰበሰበው ከግል ሴክተሩ መሆኑን እሙን ነው። ከ17 ዓመት እገዳ በኋላ 1983 በኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት ባደረገው የምጣኔ ሀብት መሻሻያዎች ምክንያት የግሉ ሴክተር በኢትዮጵያ እንደገና ማንሰራራት ችሏል፤ ቀስ በቀስም ዕድገት እያሳየ መጥቷል። ከኮንስትራክሽን ጀምሮ እስከ ሆቴልና ፋይናንስና ተቋማት ድረስ በስፋት በግሉ ዘርፍ ሊመሩ እና ሊስፋፉ ችለዋል። በአሁን ሰዓት የግል ሴክተር ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ድርሻ 15 በመቶ ደርሷል። በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ ግን ይህ ዕድገት በጣም አነስተኛ ነው።
ይህንን ለማሳየት በምጣኔ ሀብት አቅም ከኢትዮጵያ ጋር የምትቀራረበውን የጎረቤታችንን የኬንያ ተሞክሮ ማየት በቂ ነው። ኬንያ ከቅኝ ግዛት በፊት ጀምሮ በንቃት ተሳትፎ የሚያደርግ የግል ዘርፍ የነበራት ቢሆንም ከነፃነት በኋላ ግን ከፍተኛ እመርታ ሊያስመዘግብ ችሏል። ከ1960ዎቹ በፊት 20 በመቶ ድርሻ ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርት የነበረው የኬንያ የግል ዘርፍ በአሁን ሰዓት ወደ 70 በመቶ ሊያድግ በቅቷል። ከአገር አልፈውም በአሕጉር ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የግል ኩባንያዎች በኬንያ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ከሳሃራ በታች ያሉ አገሮች በዛም አነሰም በንፅፅር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ያሉ የግል ሴክተሮች አሏቸው።
እንደገና ማንሰራራት ከጀመረበት ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ያስመዘገበው ዕድገት አበረታች ቢሆንም በኢትዮጵያ ያለው የግል ዘርፍ ሌሎች ከሳሃራ በታች ያሉ አገሮች ከደረሱበት ደረጃ ጋር ግን በፍፁም ሊወዳደር አይችልም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱ ሕጋዊና የተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች፣ የግል ኩባንያዎች እና አገልገሎት ሰጪዎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ተመሳሳይ የግል ተቋማት በኬንያ ውስጥ ይገኛሉ።
ከእነዚህም እውነታ ባሻገር በኢትዮጵያ ከጠቅላላው የግል ድርጅቶች 60 በመቶ የሚሆኑ ብቻ ግብር የሚከፍሉ ሲሆን በኬንያ ግን 95 በመቶ የሚሆኑት የግብር ግዴታቸውን ይወጣሉ። በተጨማሪም በኢትዮጵያና ኬንያ ያለው አማካኝ የገቢ መጠን ከፍተኛ ልዩነት አለው። በዓለም ባንክ ዘገባ መሰረት በኬንያ አማካኝ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ገቢ 1991 ዶላር ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ 767 ዶላር አካባቢ ነው።
እነዚህ ማስረጃዎች በግልፅ እንደሚያሳዩት በዝቅተኛ ደረጃ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግል ዘርፍ እንደ ሌሎች ከሳሃራ በታች እንደሚገኙ አገሮች ግብር መክፈል የማይችል መሆኑን ነው። ʻላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማʼ እንደሚባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደርም እንደቀድሞ ሁሉ የከፋዩን አቅም ባላገናዘበ መልኩ ግብር በመሰብሰብ ይህንን እቅድ ለማሳካት መዋተቱን ቀጥሏል። ይህ የሚሳየው በወሬ ደረጃ አሁን ያለው አስተዳደር የግል ዘርፍ ልማትን በጥሩ ጎኑ የሚመለከተው ቢመስልም ሥራዎቹ ግን በተግባር የሚያሳዩት ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው የመንግሥት የተዛባ የግብር ፖሊሲና ፍትሐዊነት ከጎደለው አተገባበር ጋር መጓዝን መምረጡን ነው።
በአሁን ጊዜ በሥራ ላይ ያለውን የግብር ሕግ የተዛባ፣ ፍትሐዊነት የጎደለውና የግል ዘርፉን ከማበረታታት ይልቅ የሚጨቁን ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የግል ሴክተሩን በኪራይ ሰብሳቢዎች የተሞላ ነው ብለው ከመፈረጃቸው ባሻገር ይህን ለመገንዘብ በ2007 የተሻሻለውን የግብር አዋጅ መመልከት ያሻል። በግብር አዋጁ ላይ የተቀመጡት ግቦች በመሰረታዊነት የሚመነጩት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እስከ 1980ዎቹ ድረስ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ከነበረው ግብር በመንግሥት መሪነት ለሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሣሪያ ነው ከሚል አስተሳሰብ ነው። የዚህ አስተሳሰብ አቀንቃኞች የግብር መጨመር ከምጣኔ ሀብት ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው ብለው ይሞግታሉ። በመሆኑም የግብር መጠንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የመንግሥት ዋነኛው ተግባር በመሆን የልማታዊ መንግሥት የፖለቲካ ቅቡልነት ላይ ዐቢይ አስተዋፆ ያሳድራል።
በመርህ ደረጃ ሲታይ የግብር መጠን ማደግ ለማንኛውም አገር ጥቅም እንጂ ጉዳት ሊኖረው አይችልም። በተግባር ሲታይ ግን የግብርን መጠን ለማሳደግ የሚተገበሩ ማሻሻያዎች አሉታዊ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል። ይህም በተለይም 1950 እና 1960ዎቹ በስፋት እንደታየው የግብር መሰረታቸውን (Tax Base) ሳያሰፉ የግብር መጠንን ለማሳደግ የሞከሩ አገሮች ያጋጠማቸውን ዓይነት የንግድና መዋዕለ ነዋይ ፍሰት መቀዛቀዝ ብሎም ይህን ተከትሎ እንደመጣው ዓይነት የምጣኔ ሀብት ዕድገት መቀነስ ሊያስከትል ይችላል።
በኢትዮጵያም ተመሳሳይ የሆነ አዝማሚያ ይታያል። መንግሥት የግብር መሰረቱን ከማስፋት ይልቅ ከፍተኛ የሆነ የግብር መጠን በተቋማት ላይ መጫንን መርጧል። ከአቅማቸው በላይ ግብር እንዲካፍሉ በመጠየቃቸውም ብዙ የንግድና የአገልግሎት ተቋማት እንዲሁም ፋብሪካዎች ለመዘጋት በቅተዋል፤ ሠራተኞቻቸውንም ለመበተን ተገደዋል።
የግብር መጠንን ለመጨመር በዋነኝነት የግብር መሰረቱን ማስፋት ያስፈልጋል። የዓለም ባንክ ከኹለት ዓመት በፊት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ከጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የግል ተቋማት ውስጥ 81 በመቶ የሚሆኑት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑት ሕግ ሳይከተሉና በግብር መረብ ውስጥ ሳይታቀፉ ይንቀሳቀሳሉ።
ይህንንም ለመቀየር ማበረታቻ በመስጠት በግብር መረብ ውስጥ ያልተካተቱትን ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ወደ ግብር ስርዓቱ ማስገባት ያስፈልጋል። ባለፉት ዓመታት የግብር መሰረቱን ለማስፋት በመንግሥት ጥቂት የማይባሉ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ የግብር መጠን በመጣል የሚሰበሰበውን ገንዘብ መጨመር ላይ ብቻ ትኩረት ስለተደረገ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አልተቻለም። የዓለም ባንክ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመላክተው 63 በመቶ የሚሆኑት በግብር መረብ ውስጥ ያልተካተቱት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ላለመታቀፋቸው ዋነኛ ምክንያት የግብር ጫናውን መቋቋም አለመቻላቸው ነው።
ግብር ለአንድ አገር ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢኖረውም የሚጣለው ግብር የከፋዩን አቅም ያገናዘበ መሆን ይኖርባታል። የከፋዩን አቅም ባገናዘበ መልኩ ግብር እየጣሉ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ለመጨመር ደግሞ የግብር መሰረቱን ማስፋት ግድ ይላል። ይህን ለመከወን ግን የግብር ሕጉን ማሻሻል ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ የግብር አሰራሩን ማዘመን ያስፈልጋል። መንግሥት ይህን ሳያደርግ ከግል ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ግብር ለመሰብሰብ መንቀሳቀስ ግን የግል ዘርፉ ለአገሪቱ ማድረግ የሚኖርበትን አስተዋፆ ያዳክመዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011