በገናን ለመታደግ

0
753

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ባሕላዊና መንፈሳዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል በገና አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑም ይታወቃል። በተለይ እንደዚህ እንደአሁን የፆም ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በገና ዝማሬዎች መስማት በጣም የተለመደ ነው።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በገናና በገናን የመሰሉ መሣሪያዎች የእስራኤል ቤተ መንግሥታት ውስጥ እንደሚጠቀሙ ታሪካዊ መረጃዎች ያሳያሉ። በአራተኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ሲመጣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህናት በገናን አሁን በሚታወቀው መልኩ መጠቀም ጀመሩ።

ይሁንና ለባለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት የበገና ጥበብ ከተወሰኑ ሰዎች ውጪ እየጠፋ መጥቷል። ዓለሙ አጋን የመሰሉ ጥቂት ባለሙያዎች በዓለም ዙሪያ ስለበገና ጥበብ እያሳዩና እያስተማሩ ይገኛሉ። የበገና አስተማሪዎችም ሆኑ ተማሪዎች እየተመናመኑ መምጣታቸው በግለጽ የሚታይ ቢሆንም አሁን አሁን እንደ ሲሳይ ደምሴ ዓይነተ በርካታ የበገና አስተማሪዎችና ተማሪዎች ጥበቡን ለማቆየት እየተጣጣሩ ይገኛሉ።

ሲሳይ የበገና ትምህርት የጀመረው ነገሌ ቦረና ይኖር በነበረበት ወቅት ነው። በሙያው መምህር የሆነው ሲሳይ፥ ለረጅም ጊዜ የበገና መዝሙሮች ይወድ ነበር፤ ይሄ የጥበብ ፍቅሩ የበገና አሰራርና ድርድርን እንዲማር ገፋፋው። በ2005 ወደ አዲስ አበባ የመጣው ሲሳይ፥ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ʻሲሳይ የበገና እና መሣሪያ ማሰልጠኛ ተቋምʼን ከፈተ።

“አዲስ አበባ መጥቼ ከዓለሙ አጋ መማር ጀመርኩ። ከዛ በኋላ ነበረ የራሴን ማምረቻና ማሰልጠኛ ለመክፈት የወሰንኩት” የሚለው ሲሳይ “የበገና ሥልጠና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና ማኅበረ ቅዱሳን በኩል ቢሰጥም፤ ለብዙ ሰዎች በማይመች የማታ ክፍለ ጊዜ ነበር” በማለት እንዴት በገናን በሙሉ ሰዓት ማሰልጠን እንደጀመረ ያስታውሳል። ሥልጠናው በሙሉ ሰዓት መሰጠቱ ተማሪዎች በልዩ ትኩረት እንዲማሩ ማስቻሉን ሲሳይ ይናገራል።

በግላቸው በገናን የሚያሰለጥኑ መምህራን ቢኖሩም፥ የቴክኒክና ሙያ እውቅና የተሰጠው የመጀመሪያው ተቋም የሲሳይ ማሰልጠኛ ነው። ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው ማሰልጠኛ ተቋሙ፥ ያለ ዕድሜ ገደብ ከልጆች እስከ አዛውንት ድረስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን የተቋሙ መምህራን ምስክርነት ሰጥተዋል።
የተቋሙ ግድግዳዎቹ በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለሞችና በተሰቀሉ ክራሮች፣ በገናዎችና ማሲንቆዎች ያሸበረቁ ናቸው። ክፍሎቹ ዳር ላይ የተቀመጡት ወንበሮች ላይ የበገና መማሪያ መጻሕፍት ተቀምጠዋል። ተማሪዎች ሲመጡ ለብቻቸውም ቢሆን በቡድን ሰሌዳው ላይ የተፃፉትን መዝሙሮች ይማራሉ። በማንኛውም ሰዓት ወደ መማሪያ ክፍሉ የሚሔድ ሰው ቢያንስ አንድ መሣሪያ የሚለማመድ ተማሪ ያያል።

አብዛኞቹ ተማሪዎች የበገና ድርድርን በበዓላት ወቅትና በቤተክርስቲያን ትምህርት መርሃ ግብሮች ላይ አገልግሎት ለመስጠት ይጠቀሙበታል።

ሰላም ሰለሞን ላለፉት ሰባት ዓመታት የበገና መምህር ሆና እየሰራች ትገኛለች። ከቀደመው ጊዜ አንፃር ሲነጻጸር፥ በአሁን ጊዜ የበገና ጥበብ ትምህርት ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን የምትናገረው ሰላም “ሴቶች ተማሪዎች ከወንዶች በብዛት ይበልጣሉ። በተጨማሪም ከአሁን በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት እስከ 80 ዓመት የሚደርሱ ተማሪዎቻችን ለመማር ይመጣሉ” የምትለው ሰላም፥ ቀድሞ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም ግን ብዙ መሠራት እንዳለበት በአጽንዖት ትናገራለች።

የ23 ዓመቷ እሌኒ ደስታ የተቋሙ ተማሪ ስትሆን ከስድስት ወር በፊት በገናን መማር ጀመረች። በቅርቡ ወደ በገና ትምህርት ከመጡት ወጣቶች መካከል ትመደባለች። “ለእኔ በገና እራሴን የማረጋጋበት ዘዴ ነው። መንፈሴን ያድሳል፤ በሁሉም የሕይወቴ ክፍሎች በጣም ረድቶኛል›› ትላለች።

በገና በሌሎች አገሮችም እውቅናው እየጨመረ ነው። አዳም ሙሉጌታ የ24 ዓመት ተማሪ ሲሆን የሚኖረው አሜሪካ ነው። በገናን የተዋወቀው በሚኖርበት ዳላስ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኩል ነው። ከዚህ በፊት ሌሎች ባሕላዊ መሣሪያዎችን ተምሮ ነበር። “በገናን ከወደድኩት ቆይቻለሁ። ሳስበው ግን መማር የሚከብድ ይመስለኝ ነበር። መሰንቆና ክራር ተማርኩኝ፤ እናቴ ደግሞ በገናን እንድማር ስታበረታታኝ ለመጀመር ወሰንኩኝ። አዲስ አበባ መጥቼ የመማር እድሉን ሳገኝ ደስ ብሎኝ ነው የመጣሁት” የሚለው አዳም፥ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሆኖ በመተጋገዝ መማሩን በጣም እንደጠቀመውም እንዳስደሰተውም አልሸሸገም። እንደሌሎቹ ተማሪዎች አዳምም የወሰደውን ሥልጠና ቤተክርስቲያን ለማገልገል ይጠቀምበታል።

ይሁንና የበገናን ጥበብ ለማስተዋወቅና ለመጠበቅ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በግለሰቦች ብቻ የሚሠራበት መሆኑ ሲሳይ በመጥቀስ ስጋቱን ይገልፃል። “የመንግሥት ትኩረት አልተሰጠውም። ባሕላዊ ጥበቦችን ለመጠበቅ መንግሥት ተነሳሽነት ያለው አይመስልም። ለባሕላዊ ጥበብ ተቋማት ቢያንስ በግብር ደረጃ ማበረታቻ ሊሰጥ ይገባል። ባለንበት ሁኔታ ግን እየጠፉ ያሉትን ጥበቦች መመለስና መጠበቅ ያቸግራል” ይላል።

በሌላ በኩል የበገና ዋጋ ራሱ እየጨመረ መጥቷል። በገና የሚመረተው ከቆዳ ከእንጨትና ከበግ አንጀት ነው። እንደ መሣሪያው ማጌጫው ዲዛይን የለያል። ይህም ዋጋው ላይ የሚያመጣው ልዩነት አለው። ባለፉት ዓመታት ግን በቆዳ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ የበገናንም ዋጋ ቀይሮታል። ከሦስት ዓመት በፊት 2 ሺሕ 500 ብር የሚያወጣ በገና አሁን እስከ 3 ሺሕ 500 ብር ያወጣል። አንድን በገና ለማምረት 14 የበግ አንጀት ያፈልጋል።

ቢሆንም ለትምህርቱ የሚከፈለው ዋጋ ብዙ እንዳይሆን ጭምር መምህራን የሚችሉትን እያደረጉ ነው። ለምሳሌ በሲሳይ ማሰልጠኛ መማር የሚፈልግ ነው ለ90 ደቂቃ ትምህርት 75 ብር ይከፍል። “የቆዳና የአንጀት ዋጋ ቢጨምርም ብዙዎቹ ተማሪዎቻችን ወጣቶች ስለሆኑ ዋጋ ብዙ ላለመጨመር እንሞክራለን” ይላል ሲሳይ።

በአጠቃላይ ግን በገና ወደ ጥሩ ቦታው እየተመለሰና እያንሰራራ መሆኑን መምህራን ይናገራሉ። “ወጣቱ እንደአጥፊ በሚቆጠሩበት በዚህ ጊዜ፥ እኔ ግን ትልቅ ተስፋ ጥዬባቸዋለሁ። ይሄንን ስሠራ ያየሁት ወጣቱ ለባሕሉ ያለውን ፍቅርና ክብር ነው። ይህን ጥበብና ሌሎችን ባሕሎቻችንን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ቦታ ማድረስ እንችላለን ብዬ አስባለሁ” በማለት ሲሳይ ሐሳቡን ተስፋ በመሰነቅ ቋጭቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here