‘ኢሕአዴግ’ዎች ምን እያሉን ነው?

0
901

በአራት ብሔራዊ ድርጅቶች የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግንባርና በብሔራዊ ድርጅቶቹ መካከል የሚያወጣቸው መግለጫዎችና ያዝኩ የሚላቸው አቋሞች ለየቅል እየሆኑ ብዙዎችን ግራ ማጋባት ይዘዋል።

በተቃርኖ ውስጥ ነው የሚባለው ግንባሩ የምክር ቤቱን ስብሰባ ከሰሞኑ አድርጎ ያወጣው መግለጫም በብሔራዊ ድርጀቶቹና በግንባሩ ረገድ ያለውን አለመጣጣም ያመለከተ እንደሆነ በማስረጃነት የሚያነሱት አሉ።

ምክር ቤቱ ስብሰባውን ረቡዕ፣ ሚያዚያ 9/2011 አጠናቅቆ ባወጣው መግለጫ ባለፈው አንድ ዓመት “በተለይም 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ከተካሔደበት መስከረም ወር ጀምሮ የጉባዔውን ዋና ዋና ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ያስቻሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን” ምክር ቤቱ በዝርዝር ተመልክቷል ሲል አትቷል።

ከፖለቲካዊ ሥራዎች አንፃር ሠፊ ውይይት ከተካሔደባቸው ጉዳዮች መካከል የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት እንደሚገኙበትም ምክር ቤቱ አመልክቷል። በዚህም በግንባሩ “እህት ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል” ሲልም መግለጫው ውስጥ አካቷል። ከዚህ አኳያ “መታረምና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ፍፁም ነፃ በሆነ መንገድ ሐሳብ እንዲንሸራሸርና በመጨረሻም አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ስለመፈጠሩም” አክሏል።

በኢሕአዴግ ዘንድ ʻየውስጠ ድርጅትና አመራር መጠራጠር አለ፣ መወገድ እንዳለበትም ተስማምተናልʼ የሚል መግለጫ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ ሐሳብ ከኢሕአዴግ መግለጫዎች አልተለየም።
ኢሕአዴግ እና ድርጅቶቹ

ከላይ እንደተጠቀሰው በኢሕአዴግ ውስጥ መቃቃር ስለመኖሩ ብዙ ማሳያዎች አሉ። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኢሕአዴግ ሊቀመንበሩ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኹለት ሳምንት በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢሕአዴግ ማደጉን በመጥቀስ ጠንካራ ድርጅት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል። ሊቀ መንበሩ ይህን ይበሉ እንጂ በኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአደባባይ እየታየ ያለውን ተቃርኖ በመጥቀስ “በእርግጥ ግንባሩ አለ ወይ?” የሚለው ጥያቄ እየተነሳ ነው። ዐቢይ በኢሕአዴግ ውስጥ ሁሉም ሰው አንድ ድምፅ እንዲኖረውና እንዲያጨበጭብ እንደማይጠበቅ በመግለፅ በግንባሩ አመራሮች በኩል ያለው የሐሳብ ልዩነት የሚበረታታ ነው የሚል አቋም አላቸው። ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግን የሰለቸው አንድ ዓይነት ነገር ብቻ ማውራት ነው በማለትም ይህ አዋጭ አለመሆኑን ይገልፃሉ። እሳቸው የሚፈልጉት በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ሁሉም ሰው የግል አመለካከቱን ያለፍርሃት እንዲገልፅ ነው። ከዚያ በኋላ ግን የጋራ ወይም የአብላጫ ድምፅ ያገኘውን ውሳኔ መተግበር የሚጠበቅ ሥነ ምግባር ነው ይላሉ።

ሊቀ መንበሩ ይህን ቢሉም እውነታው እሳቸው ባሉት ልክ አይደለም የሚሉ አሉ። ለምሳሌ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያፀደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በትግራይ ክልል እንዳይተገበር ክልሉን በሚመራውና በኢሕአዴግ መሥራቹ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታግዷል። ይህ እንዴት ግለሰቦች የራሳቸውን ሐሳብ በነፃነት ገልፀው ውሳኔን ግን መተግበር ይጠበቃል ከሚለው የዐቢይ እምነት ጋር ይገናኛል? ኢሕአዴግስ አለ ወይ? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ሊቀ መንበሩ ዐቢይ “ኢሕአዴግ እንደተቋም አለ፤ ኢሕአዴግ በውስጡ ድሮም እንዲህ ዓይነት ባሕሎች ነበሩት፤ መከራከር፣ መጨቃጨቅ፣ በአቋም መውጣት የሚባሉት ጉዳዮች ነበሩት። የኢሕአዴግ በሽታ የነበረው ይህን ልምምዱን ወደ ውጭ አያወጣውም፤ አሁን አደገ ኢሕአዴግ በውስጥም ይከራከራል፤ ሳይፈራም ወደውጭ ያወጣል፤ ይህ መቀጠል አለበት። ኢሕአዴግ አለ፣ እስካሁን አለ እንግዲህ ሕዝብ መርጦ እስኪጥለው ድረስ አለ፣ አገርም እየመራ ነው ያለው” ሲሉ ኢሕአዴግ ጠንካራ ስለመሆኑ ሊያሳምኑ ጥረዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ዮሐንስ ቧያለው በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች መካከል የተለያየ ሐሳብ መነሳቱ የሥልጡን ፖለቲካ ማሳያ ነው ሲሉ የዐቢይን ሐሳብ ይጋራሉ። እንደሳቸው ገለፃ ከዚህ ቀደም የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የታፈነ ስለነበር የልዩነት ሐሳቦች ይፋ አይሆኑም (ይታፈናሉ)፣ አሁን ግን ነፃነት ስላለ ሁሉም ሐሳብ አደባባይ ላይ ይወጣል። ኃላፊው፣ ይህም በኢሕአዴግ መካከል ልዩነትና የከረረ ቅራኔ የተፈጠረ ያስመስላል እውነታው ግን የድርጅቶቹ ግንኙነት አሁንም ጠንካራ መሆኑ ነው ባይ ናቸው።

ዐቢይና ዮሐንስ ይህን ይበሉ እንጂ ባለፈው ዓርብ፣ ሚያዚያ 4/2011 በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የወጣው መግለጫ የኹለቱን ሐሳብ ውድቅ የሚያደርግ ነው። ቀናትን ስብሰባ ላይ የነበረው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በማጠቃለያው ያወጣው መግለጫ በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል መራራቅ ስለመፈጠሩ የሚያሳብቅ ነው። የኢሕአዴግ በጥልቀት የመታደስ ጉዞ ʻተኮላሽቷልʼ ያለው ሕወሓት አሁን በፌደራል ሥልጣን ላይ ያለው አመራርን ጨምሮ ያለፉትን 27 ዓመታት ሙሉ የጨለማ ጊዜ አድርጎ የመፈረጅ አዝማሚያ መታየቱን በመጥቀስም በተደጋጋሚ ሲወቅስ ከርሟል።

ሕወሓት በሰሞነኛ መግለጫው ኢሕአዴግ የሚታወቅበትን መስመር በመሳቱ አገር የከፋ አለመረጋጋት ውስጥ መግባቷንም ያነሳል። ኹከትና ግርግር ጨምሮ ሕግ ማስከበር አለመቻሉን በዚህም ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች እንደፈለጉ እየፈነጩ ነው ሲል ከሷል።

ሕወሓት ያለፈውን ሳምንት መግለጫ ባወጣ ማግሥት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ መደረጉ ይታወሳል። ምክር ቤቱ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት ውጤት ማስመዝገቡን በመግለፅ፣ እህት እና አጋር ፓርቲዎች እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችን በመግለጫው ያሞካሻል። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተፈረመውን የቃል ኪዳን ሰነድ በማድነቅም ኃይሎቹን በፅንፈኝነት ሳይሆን በአማራጭ ሐሳብ አቅራቢነት ተመልክቷቸዋል።
ኢሕአዴግ፣ ሕገ መንግሥት እና ምርጫ

የኢሕአዴግ ድርጅቶች በየክልላቸው በሚያወጡት መግለጫ እርስ በእርስ እስከመወነጃጀልና ጦርነት ለመግጠም እስከመከጃጀል ሲደርሱ፣ አንዱ አንዱን ጠላትና አገር አፍራሽ አድርጎም በግልፅ ሲፈርጅ ተስተውሏል። አንዱ የፌደራል ስርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን ለማፍረስ የሚተጋ ሌላው ደግሞ ይህን ለመታደግ ያለእረፍት የሚጥር ሆነውም በመግለጫ ʻሲጠዛጠዙʼ ከርመዋል።

ለአብነት አዴፓ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ የአማራ ሕዝብ በወጉ አልተወከለም የሚለውን የክልሉ ሕዝብ ቅሬታ በመቀበል ለውይይት እንዲቀርብና እንዲሻሻል አቋም መያዙን በመግለጫ አውጥቶ ነበር። ሕወሓት ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የፌደራል ስርዓቱ ምሰሶ መሆኑን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወደውና ፈቅደው ማፅደቃቸውን በመግለፅ እንዲሸራረፍ አይፈልግም። በአማራ ክልል ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ተደርገው በነበሩ ሰልፎች የተያዙ መፈክር፣ ሰንደቅ ዓላማና አርማዎችም ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱ እንደሆኑም በመወንጀል ጭምር መግለጫ አውጥቷል፣ በትግራይም ይህንኑ የሚኮንን ሰልፍ አስደርጓል። ኦዴፓ በበኩሉ “በፌደራሊዝም ስርዓቱ ላይ አልደራደርም” በማለት አቋሙን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ተቃርኖ ባለበት ሁኔታ የተሰበሰበው ምክር ቤቱ ግን ምን አቋም ይዞ እንደወጣ በመግለጫው ያነሳው ነገር የለም።

የምርጫ ጉዳይም በብዙዎች የሚጠበቅ፣ በፖለቲካ ኃይሎች መካከልም በጊዜው ይካሔድና ይራዘም ሐሳብ ላይ ልዩነት ያለበት ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ መክሮበት ኢሕአዴግ እንደፖለቲካ ኃይልም ሆነ እንደ ገዥ መንግሥት አስተያየቱ ምን እንደሆነ አላሳወቀም።

ኢሕአዴግን የማዋኀድ ትልም
ኢሕአዴግ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ራሱን ከግንባርነት ወደ አንድ ውሕድ ፓርቲነት ለመቀየር አስቦ ጥናት መጀመሩ ይታወቃል። ይሁንና ይህ ሐሳብ ባለፈው ዓመት በኢሕአዴግ ቤት የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።
ዐቢይ ከወራት በፊት በጽሕፈት ቤታቸው የሱማሌ፣ ሐረሪ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችን ሰብስበው ሲመክሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢሕአዴግ የሚባል ግንባር እንደማይኖር ይልቁንም አንድ አገራዊ ውሕድ ፓርቲ እንደሚመሰረት መናገራቸው ይታወሳል።

በሰሞነኛው የግንባሩ ምክር ቤት ስብሰባ ዋዜማ የወጣው የሕወሓት መግለጫ ደግሞ ውሕድ ፓርቲን ማሰብ እንደማይቻል አቋሙን ግልፅ አድርጓል። ሐሳቡ ነባር መሆኑን ያልካደው ሕወሓት፥ ኢሕአዴግን የማዋሐድ ሐሳብ ተጠንስሶ የነበረው ኢሕአዴግ ʻጤናማʼ እንደነበር በመግለፅ አሁን ላይ በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል መሰረታዊ የእምነት ልዩነት መፈጠሩን ይፋ አድርጓል።

ግንባሩ ጉራማይሌ ሐሳብ ውስጥ መግባቱን ጠቅሶም እንኳን ለመዋሐድ ባለው ግንባር አደረጃጀት ለመቀጠልም የሚያበቃ የጋራ እምነት እንደሌለ አደባባይ አውጥቶታል። ይህም ኢሕአዴግ በአሁኑ ምክር ቤት ስብሰባው በጥልቅ መክሮበት ግንባሩ ዕጣ ፈንታው ይለይለታል በሚል ብዙዎች ሲጠብቁት ነበር።

ይሁንና በምክር ቤቱ መግለጫ ስለውሕድ ፓርቲ ሐሳብ አንዲትም ቃል አልተፃፈም። በእርግጥ ሳይወያይበት ቀርቶ ነው ወይስ ከጀርባ ምን አለ ይሆን? የሚለው ሐሳብ ያከራክራል። ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ አብስሎ ለሕዝብ የሚበስረው ነገር እንደማይኖር ይልቁንም ከረቂቁ ጀምሮ ሕዝብ በግልፅ እየመከረና በአደባባይ እየተሞገተ የመጨረሻው ሐሳብ ይገዛል ያሉት ቃል የውሃ ሽታ በመሆኑና ምክር ቤቱም በዝግ በመምከሩ ምን ይነሳ፣ ምን ይጣል የታወቀ ነገር የለም። ግን ደግሞ በመርህ ደረጃ በመግለጫው ያልተካተተው ስላልተነሳ ነው ተብሎ ስለሚታመን ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት የጎላ ቅራኔው ላይ ተወያቶ ውሳኔውን ለሚመራው ሕዝብ ካላሳወቀ የመሰብሰቡ ጥቅም እንደተለመደው ʻተሸናግሎʼ ለመለያየት ነው ወይ? በሚልም እያስወቀሰው ነው።

ኢሕአዴግ በፖለቲከኞችና ተንታኞች ዕይታ
የቀድው ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው ኢሕአዴግ ምክርና የሌሎችን ሐሳብ አልቀበልም በሚል ʻድርቅናውʼ 27 ዓመት ኢትዮጵያን እንደጎዳት ያነሳሉ። ያለፈው ዓመት ለውጥ የተደራጀ የተቃውሞ ኃይል ባለመኖሩ ከኢሕአዴግ እጅ ወጥቶ ቢሆን ኖሮ የከፋ ችግር ይገጥም እንደነበር በመግለፅም አሁንም ግን ኢሕአዴግ በሚፈለገው ልክ ለውጥ አለማምጣቱን ይኮንናሉ። ይህም ግንባሩ ራሱን የለውጥ ደጋፊና ተቃዋሚ፣ አሳሪና ታሳሪ አድርጎ ኢትዮጵያን ወዳልተፈለገ አዘቅት እየጎተታት ነው የሚል ነው። ይህ ደግሞ ዳግም ʻአገርና ሕዝብን መካድʼ ነው በማለት ኢትዮጵያን መካስ ካለበት መጀመሪያ ራሱን አንድ ማድረግ [በአቋምና ተግባር] እንዳለበት አፅንዖት ይሰጣሉ። አሁን እየሆነ ያለው ግን ኢሕአዴግ በምክር ቤት ስብሰባው በሙሉ ድምፅ ወስኖ የወጣበትን ጉዳይ ድርጅቶቹ በየክልላቸው ሲሄዱ የተለያየ አቋም መያዝና መግለጫ ማውጣት ውስጥ መግባት ነው የሚሉት ልደቱ እንደ አገር መሪ የፖለቲካ ኃይል ከዚህ አባዜው ሊወጣ እንደሚገባውም ይመክራሉ።

ሌላው ፖለቲከኛ ይልቃል ጌትነት ደግሞ በኢትዮጵያና ኢሕአዴግ ውስጥ አሁን ያለውን ሁኔታ ለመረዳት አስቸጋሪ መሆኑን በመግለፅ በዚህ ወቅት ዋነኛ ችግር ከሚባሉት ውስጥ አንዱ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ተቃርኖ እንደሆነ ያሰምሩበታል። ከመሰረቱ ኢሕአዴግ በተቃርኖ የተሞላ እንደሆነ በማንሳትም ላይም በድርጅቶቹ መካከል ያለው ከምስረታቸው ጀምሮ ያለው መጥፎ ነገር እንደሆነ ያምናሉ። ውስብስብ ችግር ያለበት ኢሕአዴግ በሚመራው አገር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚችልበትን ስልት አለመንደፉና አለማስተዋወቁም ሌላው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነ ያክላሉ።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሰሚር የሱፍ (ዶ/ር) አሁን ላይ መንግሥት (ኢሕአዴግ) በውስጡ ወጥነት እንደሌው በመግለፅ አንዱ የቀጣይ ጉዞ ፈተና እንደሚሆንና ፈጥኖ ሊታረም እንደሚገባው ከዚህ ቀደም በሸራተን አዲስ ሆቴል የዐቢይ አህመድን የአንድ ዓመት ጉዞ በገመገሙበት የውይይት መነሻ ሐሳባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

የፖለቲካ ተንታኙ ጎይቶም ገብረልዑል ከሰሞኑ በአልጄዚራ ʻዘ ስትሪምʼ መርሃ ግብር ላይ ቀርበው ሲወያዩ ኢሕአዴግ በሚመራው አገር ውስጥ የዜጎች በሚሊዮን መፈናቀልን፣ የሕግ የበላይነት መርህ መጣስን፣ የተደራጁ ቡድኖች የሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች መብዛትንና ሌሎችንም ቀውሶች በመጥቀስ ዋና ኃላፊነቱ ኢሕአዴግ ላይ እንደሚወድቅ አስምረውበታል። በመሆኑም ኢሕአዴግ ከችግር ለመውጣት ቁጭ ብሎ ከልቡ ሊመክርና መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚገባውም መክረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here