ኢትዮጵያ ወደ ግራ፥ ኢሕአዴግ ወደ ቀኝ!

0
907

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ሆነው መምጣታቸው፥ ድርጅታቸው የተያያዘውን የቁልቁለት ጉዞ ለመግታት ብሎም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ለማድርግ መሆኑ የጠቀሱት ይነገር ጌታቸው፥ የዐቢይ ብሔርተኝነት ያለቅጥ መሰበኩ አገር ለማፈረስ ጫፍ መደረሱን በማጠየቅ መፍትሔው ኢትዮጵያዊነትን መመለስ መሆኑ የሚለው ትርክታቸው የድርጅታቸውን መሰረታዊ መርህ የጣሰ በመሆኑ የድርጅጅን ኅልውና አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል ሲሉ በማሳያ የመከራከሪያ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ።

የኢሕአዴግ ሰማይ ድንግዝግዝ ብሏል። እዚህም እዛም ያለው የእህት ድርጅቶች አተካራ በርትቷል። ሕወሓት ያለፈው ዓመት የተጀመረው ለውጥ መቀልበሱን በይፋ አውጃለች። ባለፈው ሳምንት ባወጣችው መግለጫም የአገሪቱን የለውጥ ጅምር የተኮላሸው ተሐድሶ በሚል ገልፃዋለች። አዴፓና ኦዲፒ ከየክልላቸው የፖለቲካ ልኺቃን በመነጨ ግፊት አብሮነታቸው ተደነቃቅፏል። ደኢሕዴን የክልሉን ሕዝብ ደኅንነት አይደለም የሚሰበሰብበትን አዳራሽ ሰላም ማስጥበቅ ተስኖታል። እንዲህ ያለው የዘመን እውነት የገዥውን ፓርቲ ህልም ሊነጥቅ ወደፊት እየከነፈ ነው። እንደ ሜክሲኮው አብዮታዊ ፓርቲ ሰባት ዐሥርታትን በሥልጣን መቆየት እችላለሁ ብሎ ያምን የነበረው ኢሕዴግም አሁን የኅልውና ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። የነገው መንገዱም ቀቢፀ ተስፋነትን አንግቧል። ይህ ከራስ ተስፋ መመነን አንድም ገዥው ፓርቲ ራሱ የለያቸውን ችግሮቹን ካለመፍታቱና በራሱ ላይ ከማመፁ የሚመነጭ ሲሆን አንድም ከፓርቲው ባሕሪይ ይቀዳል ።

የኢሕአዴግ በራስ ላይ አመፅ
የቀድሞው የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር መለስ ዜናው ለመጨረሻ ጊዜ በታደሙበት የፓርቲያቸው የፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ ኢሕአዴግ እየነጠፈ ነው የሚል ሐሳብ አንስተው ነበር። አሌክስ ደዋል (ፕ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኑዛዜ እያሉ የሚጠሩት ይህ የአቶ መለስ ንግግር ፓርቲው የስትራቴጅክ አመራር እጦት እንደገጠመው ያብራራል። እንዲህ ያለው ክሽፈትም ኹለት መሰረታዊ መነሻዎች አሉት ይላል። የመጀመሪያው ገዥው ፓርቲ የራሱ ሐሳብ አፍላቂ ቡድን (think tank) የሌለው ከመሆኑ ይመነጫል። ይህ ደግሞ የፓርቲውን ድክመት የመንግሥት ከማደርጉም በላይ የድርጅቱ የበላይ አካላት አመራር ከመስጠት በዘለለ የፖሊሲ አማራጮችን የማቅረብ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። የኢሕአዴግ በእርሳቸው ላይ ጥገኛ መሆን ያታከታቸው አልያም ያሳሰባቸው አቶ መለስ ድርጅታቸው የራሱ ሐሳብ አመንጭ ቡድን ካላቋቋመ በየጊዜው የሚመጡበትን ፈተናዎች መተንበይም ሆነ መፍታት እንደማይችል በሰፊው ተንትነዋል። የግንባሩ ስትራቴጅካዊ አመራር ችግር መነሻ ግን በዚህ ብቻ የተቀነበበ አይደለም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሰትር እንደሚሉት በግንባሩ ውስጥ የታቀፉ አባላት ጥራት የሚጠቀበቀውን ያህል አለመሆን ድርጅቱን የሐሳብ ድሃ ከማድረግ አልፎ በተራዘመ መንገድ ፓርቲውን ተብትቦ መያዙ የሚቀር አይደለም ።

አቶ መለስ ድርጅታቸው እንዲህ ያለ ፅልመት እንደዋጠው ቢረዱም የእሳቸው ፅልመት በመቅደሙ የመፍትሔው አካል አልሆኑም። የቀድሞው ሊቀ መንበር ህልፈት አንድም ኢሕአዴግ ከነውዝፍ ችግሮቹ ወደ ሌላ ሊቀ መንበር እንዲሸጋገር በር ሲከፍት በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲው የገጠመው የሐሳብ ማመንጨት ችግር እንዲባባስ ዕድል ፈጥሯል። እዚህ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ያመጣውን ድርጅታዊ የአመራር ክፈተት ወደ ጎን አድረግን ፓርቲው የስትራቴጅ ደሃ ወደ መሆን መሸጋገሩን ብቻ ለመመለከት እንሞክር። አሌክስ ደዋል “The Real Politics of the Horn of Africa” በተባለ መጽሐፋቸው አቶ መለስ መራሹ መንግሥት ሦስት ሐሳብ የሚያብላላባቸው ክፍሎች ነበሩት ይላሉ።

የመጀመሪያው የመንግሥት ሞተር የሚባለው ክፍል ነው። ይህ ስብስብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እየተገናኘ የሚመክር ሲሆን የንድፈ ሐሳብ ክርክር የሚደረግበት መሆኑ ይገለፃል። የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ የሚሳተፉበት ይህ ክፍል ዓለማቀፋዊ ፖለቲካዊ ኀልዮቶች በጥልቀት የሚተነተኑበት ነው። በአገሪቱ ልዕልና እንዲኖረው የሚፈለግ ሐሳብም መነሻው ከዚህ ክፍል ነበር። ኹለተኛው የሐሳብ አመንጭ ኃይል በአንፃሩ ንደፈ ሐሳባዊ ክርክሮችን አገራዊ መልክ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። በመጀመሪያው ክፍል ነጥረው የወጡ ሐሳቦችን ወደ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የመመለስ ሥራም ይሰራል። የውጭ ጉዳይ፣የግብርና፣ የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲዎችም ከዚህ ክፍል የሚመነጩ ናቸው። ሦስተኛው የሐሳብ ቋት የፖለቲካ ጉዳዮችን ብቻ የሚሰራ ነው። ለፓርቲው አባላት ንድፈ ሐሳባዊ ትንታኔ ከማቅረብ አንስቶ አዳዲስ አሰራሮችን የመቀየስ ተግባርንም ሲወጣ ቆይቷል።

ዳዋል አቶ መለስ መራሹን ኢሕዴግ ሲገመግሙ የሁሉም የሐሳብ ማመንጫ ክፍሎች አንቀሳቃሽ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነበሩ ይላሉ። በቢሮቸው ይካሔዱ በነበሩ የንድፈ ሐሳብ ክርክሮች ላይ ይሳተፉ የነበሩ የኢሕአዴግ አባላት ሚናም ታዛቢነት እንደነበር ያብራራሉ። አቶ መለስ ከዚህ ባለፍም የአገሪቱን ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች ብቻቸውን ነድፈው እንዲተገብሩ አድርገዋል። በፓርቲው ልሳን ላይም በርከት ያሉ የርዕዮተ ዓለም ተንተናዎችን ለተከታዮቻቸው አቅርበዋል። በዚህ ሒደትም መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላትን አገር የሚያስተዳደረው ገዥ ፓርቲ ሐሳብ አመነጭነቱ በግለሰብ ላይ የተንጠለ ሁኗል። በኢሕአዴግ ቤት የአቶ መለስ ህለፈት የድርጅቱ ሊቀመንበር ሞት ብቻ ተደርጎ የማይወሰደውም በዚህ ምክንያት ነው።

ይህ ደግሞ አቶ ኃይለማሪያም የተረከቡት ድርጅት የስትራቴጅ መካን እንዲሆን አድርጎታል። አሳሳቢው ነገር ግን እሱ ብቻ አይደለም። ኢሕአዴግ ወቅታዊው ሁኔታዎችን የተመለከቱ አዳዲስ ሐሳቦች ማምረት ብቻ ሳይሆን አስቀድመው የተዘጋጁትንም ወደ መሬት ማውረድ የተሳነው ግንባር ወደ መሆን እየተሸጋገረ ነበር። “ይህ ለምን ሆነ?” የሚል ጥያቄ ከተነሳ ቢያንስ ኹለት ነገሮችን በቀላሉ መጥቀስ እንችላለን። የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ከምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲ ስርዓት ይመነጫል። ይህ ስርዓት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነባቸውን አገራት ለተመለከተ ሰው የልማታዊ መንግሥት አስተሳስብ ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይልቅ ለአምባገነናዊ ስርዓት የተመቸ መሆኑን ይረዳል። እንዲህ ያለው እውነት ደግሞ ልማታዊ መንግሥት ከቡድናዊ ውሳኔዎች ይልቅ ለግለሰብ አሰተዳደር የተመቸ እንደሆነ ያረጋግጣል። ኢሕአዴግ ከሊቀ መንበሩ ህለፈት በኋላ የገጠመው አንዱ ችግር ከዚህ የሚቀዳ ነው። የአቶ ኃይለማሪያም ድርጅት ወደ ቡድናዊ ውሳኔዎች ፊቱን ያዞረ ነበር።

አቶ ኃይለማሪያም መራሹ ኢሕአዴግ ከአቶ መለሱ ኢሕአዴግ የሚለየው ግን ከላይ በጠቀስናቸው ጉዳዮች ብቻ አይደለም። የቀድሞው ሊቀ መንበር ግንባሩ ቆጥሮ ከሰጣቸው ኃላፊነት በተጨማሪ የግላቸው የነበሩ ገፀ በረከቶችም እንደነበራቸው አያከራክርም። በዚህ በኩል የሚጠቀሰው አቶ መለስ በወታደሩም ሆነ በሲቪሉ እኩል ተደማጭነት የነበራቸው ሰው መሆናቸው ነው። የቀድሞው ታጋይ መለስ ዜናዊ በወታደራዊም ሆነ በሲቪል ደኅንነት ውስጥ የነበሩ መረጃዎችን መዋቅራዊ ከሆነ ሰንሰለት ውጭ እንደልብ ማግኝተቻው አገራዊም ሆነ ቀጠናዊ ውሳኔዎችን በፍጥነት እንዲስተላልፉ ረድቷቸዋል። በፓርቲው ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ማዕከላዊነትን ተጠቅመውም ድርጅቱን እንዳሻቸው እንዲዘውሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ከዚህ አንፃር አቶ ኃይለማሪም የተረከቡት ኢሕአዴግ በኹለት እግሩ የቆመ ሳይሆን ለመቆም የሚታትር ነበር። የአዲሱ ሊቀ መንበር ፈተናም ድርጅቱ የተያያዘውን የቁልቁለት ጉዞ መግታት ብሎም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ማድርግ መሆኑ አያጠያይቅም።

ይሁን እንጅ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለዚህ የታደሉ ሰው አልነበሩም። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት ክርስቶፈር ክላፋም እንደሚሉት የቀድሞው የደኢሕዴን ሊቀ መንብር ወደ ኢሕአዴግ መሪነት መሸጋገር ገና ከጅምሩ ችግር ፈች የመሆን አቅም አልነበረውም። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊው ምክንያት አዲሱ ሊቀ መንበር የደቡብ ፖለቲከኛ መሆናቸው ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከደቡብ መምጣት የፖለቲካ ልምድን ብቻ ሳይሆን በቂ የፖለቲካ ካፒታልንም ያሳጣል።የክላፋም እንዲህ ያለ መከራከሪያ በቁም ሲያዩት ብዙም ትርጉም ባይሠጥም እውነት መሆኑ ግን አያከራክርም።

እራሳቸው አቶ ኃይለማሪያም ከመንበረ ሥልጣናቸው ከተሰናበቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የብሔር ፖለቲካ አሰላለፍ ያሰቡትን እንኳን ለመተግበር ዕድል እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል። ወዲህ የእሳቸው ድርጅት ደኢሕዴን የተለያዩ ብሔሮችን ያቀፈ በመሆኑ ከወላይታ ለመጡት ሰው ሙሉ ደጋፍ የሚያደርግ አልሆነም፤ ወዲያ የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር የሚፎካከሩት ኦሕዴድ፣ ብአዴንና ሕወሓት ጆሮ አልሰጧቸውም።

በዚህ ምክንያትም አቶ ኃይለማሪም የተረከቡትን ኢሕአዴግ ለመጠገን አይደለም ባለበት ሁኔታ ለማስቀጠል እየተሳናቸው መጣ። ቅፅበታዊ መለዋወጥ በሚያስተናግደው የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ አዳዲስ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማፍለቅም የማይታሰብ ሆነ። ፈጣን የመሪ ውሳኔዎችን በሚሻው የልማታዊ መንግሥት ጎዳና ገዥው ፓርቲ ወደፊት መራመድ ተሳነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሥራ አጥ ወጣቶች ከአደባባይ ተሰይመው ኢሕአዴግ ሥልጣኑን እንዲያስረክብ ይጠይቁ ያዙ። ሳሙኤል ሀንቲንገተን እንደሚለው በብዙ አገራት የሚፈጠሩ ፖሊካዊ ቀውሶች ፖለቲካውን የማዘመን ዕድል ይፈጥራሉ። በኢትዮጵያ የሆነውም ይህን የሚያንፀባርቅ ነው። ኢሕአዴግ ከዓመት በፊት አካሔድኩት ባለው ጥልቅ ተሐድሶ ስርዓቱን ለማሻሻል ቁርጠኛ እንደሆነ አረጋግጧል። በቀደመው ጊዜ ለነበረው ስህተትም አመራሩን ተጠያቂ በማድረግ አዲስ ሊቀ መንበር መርጧል፤ አቶ ኃይለማርያምን ሸኝቶም ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ወደፊት አምጥቷል።

በኢሕአዴግ ቤት ያለው የሊቀ መንበር መለዋወጥ በዋናነት ፓርቲው የገጠመውን ፈተና ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ ፈተና በአንድ በኩል ከላይ እንደገለፀው ባለፉት ሊቀ መናበርት ያልተፈታ የታሪክ ጣጣ ያለበት ሲሆን በሌላ በኩል በወቅታዊ ችግሮችም የታጠረ ነበር። ጥያቄው ዐቢይ እነዚህን መሰናክሎች እንዴት ያልፏቸው ይሆን የሚለው ነው። ዐቢይ እየከሰመ ያለ ድርጅታቸውን ለመታደግ በመጀመሪያ ያከናወኑት ተግባር ሕዝባዊ ጫናውን ለማርገብ መሞከር ነው። ለዚህ ደግሞ ዋና መሣሪያ ያደረጉት የኢትዮጵያዊነትን ትርክትን ማቀንቀን መሆኑ አያከራክርም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ደጋግመው አንስተዋል። “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፥ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ብለዋል። ብሔርተኝነት ያለቅጥ መሰበኩ አገር ለማፈረስ ጫፍ መደረሱን የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መፍትሔው ኢትዮጵያዊነትን መመለስ መሆኑን ደጋግመው ተርከዋል።

ይሁን እንጅ የዐቢይ አዲስ ፍኖት ከሚመሩት ፓርቲ አንጻር የሚያስኬድ አልነበረም። ኢሕአዴግ የብሔር ድርጅት ነው። በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልፅ እንዳሰፈረውም የአገሪቱ ችግር ሊፈታ የሚችለው የብሔር ብሔረሰቦች ችግር ሲፈታ ብቻ ነው። አዲሱ ሊቀመንበር ግን ከዚህ እውነት የሸፈቱ ናቸው። የብሔር ፖለቲካ ድርጅት እየመሩ የዜግነት ፖለቲካን አስፈላጊነት ይሰብካሉ። ይህ አካሔዳቸው የግጭት አዙሪት ውስጥ የነበረው የአማራ ፖለቲካ ልኂቅ ለጊዜውም ቢሆን ሰፊ ድጋፍ እንዲሰጣቸው አድርጓል። የአዴፓም መሪዎችም ከሕዝባዊ ተቃውሞዎች ፋታ እንዲወስዱ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ኦዲፒም የአንዲት ኢትዮጵያ አስተሳሰብ ከራሱ የመነጨ በመሆን ተቃውሞ አላሰማም። ኢሕአዴግን ከመዘወር ወደ ተሳፋሪነት የተዛወሩት የትግራይ ፖለቲካ ልኂቃን ግን የግንባሩን አዲስ ሊቀመንበር ተግባር ከድርጅቱ መርህ ጋር የሚጣረስ መሆኑን ለፈፉ። ደኢሕዴንም መንታ መንገድ ላይ ቆመ። የዐቢይ የብሔር ድርጅትን እየመሩ የዜጋ ፖለቲካን ማቀንቀን ያላተማቸው ከድርጅታቸው መተዳደሪያ ደንብ ጋር ብቻ አልነበረም። የአስፈፃሚው አካል ቁንጮ የሆኑት ሰው አዲስ መንገድ መንግሥታቸው ቆሜለታለሁ ከሚለውም ሕገ መንግሥት ጋር የሚጣረስ ነው።

ዐብይ ገና አራት ኪሎን ሳይረግጡ ባሰሙት የበዓለ ሲመታቸው ንግግር በግልፅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቀረን ሐሳብ ደጋግመው ሲያነሱ ተስተውለዋል። እዚህ ላይ በመጀመሪያ ንግግራቸው ያሰሟቸውን ሐሳቦች ለአብነት ለማንሳት እንሞክር። በዛ መድረክ አቶ ኃይለማሪያምን ለማመስገን ባለመው ንግግራቸው የዛሬዋ ቀን በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር የተደረገባት ታሪካዊ ቀን ናት ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ሐሳብ ኹለት መሰረታዊ ጥያቄ ያስነሳል። “ምን ዓይነት የሥልጣን ሽግግር ተደረገ? ማን ነው ለማን ሥልጣን ያሸጋገረው?” የሚል። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 73/2 በግልፅ እንደሰፈረው መንግሥታዊ ሥልጣን የሚመሰረተው በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ባለው ፓርቲ አማካይነት እንጅ በግለሰብ አይደለም ነው። እንዲህ ከሆነ የአቶ ኃይለማሪያም በዶክተር ዐቢይ መቀየር በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለ የአመራር መተካካት እንጅ የሥልጣን ሽግግርን አያመለክትም።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሥለጣናቸውን አሃዱ ባሉበት ቀን ያሰሙት ንግግር ሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያዊነትን የሚያይበትን መንገድም የናደ ነበር። ከላይ ከፍ ብዬ እንደገለፅኩት ዐቢይ በእንደራሴዎች ምክር ቤት ፊት ቆመው “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፥ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” የሚል ንግግር አሰምተዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒሰተሩ ሐሳብ በሰዎኛ ችግር ባይኖረውም እንደአገር መሪ ግን ተቃርኗዊ ነው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ወሰን የመሰረቷት ክልሎች ወሰን መሆኑን በግልጽ አስፍሯል። ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ብሔር ብሔረሰቦችን እንጅ ኢትዮጵያን እንደማያውቃት ያረጋግጣል። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ግን ሕገ መንግሥቱን ሳያሻሽሉ ኢትዮጵያዊነትን በግዛት ፖለቲካ ዕይታ ተርጉመውታል።

የአዲሱ ሊቀመንር በኢሕአዴግ ላይ ማመፀም ሆነ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አፍታም ሳይወስዱ መላተም በድርጅቱ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት ለማናር ጊዜ የሚውሰድ አልነበረም። ይህ ደግሞ በኢሕአዴግ ቤት ʻበእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍʼ የሚሉትን ዓይነት ችግር አስከትሏል። በታሪክ ዕዳ ለጎበጠው ፓርቲም ሌላ ጭነት ሆነውበታል። ይህ አጣብቂኝ ቀጣዩ የኢሕአዴግ ጉዞ ምን መልክ ይኖረው ይሆን የሚሉ ሐሳቦችን እንድናነሳ ዕድል ይፈጥራል። ኢሕአዴግን ማዳነ ይቻላል? የሚል ጥያቄም ያስነሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here