የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ችግር እየገጠመው እንደሆነ አስታወቀ

0
546

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት በከተማዋ ውስጥ እየተባባሰ በመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ባሳለፍነው ሳምንት ለአንድ ቀን ተኩል አገልገሎቱን አቋርጦ ውሏል። የትራንዚቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደረጀ ተፈራ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የኃይል መቆራረጡ ከአንድ ሳምንት ወዲህ እየተባባሰ እንደመጣ ያስታወቁ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮችን በሙሉ ወይም በከፊል ለማቆም መገደዳቸውን አብራርተዋል።

ኃላፊው ጨምረው ሲገልጹ፥ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቢያሳውቅም ምላሽ ካለማግኘቱም በላይ ችግሩ ጭራሽ እየተባባሰ እንደመጣ አስታውቀዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ያለፈው ማክሰኞ መጋቢት 8/2011 ከጥዋት ጀምሮ ምንም ዓይነት የባቡር መጓጓዣ እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ድረስ ያልነበረ ሲሆን በዚህም ሳቢያ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ደረጀ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በቀጣዩ ቀን ረቡዕ መጋቢት 9/2011 ተመሳሳይ ችግር ማጋጠሙን የተናገሩት ኃላፊው በዚህ ሳምንት የተከሰተው ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛው እንደሆነ ጠቁመዋል።

“የኃይል መቆራረጡ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ባቡሮችን ማንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው እንጂ እስካሁንም በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እየደረሰን አልነበረም አገልግሎት ስንሰጥ የነበረው” ሲሉም ተናግረዋል።

መጋቢት 9/2011 የችግሩን መደጋገምና መባባስ በመጥቀስ በድጋሚ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቅሬታውን ያስገባው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የኃይል መቆራረጡ በመላው አዲስ አበባ እንደተከሰተና ለቀላል ባቡሩም የሚደርሰው ከከተማዋ የተለየ ስላልሆነ በትዕግስት እንዲጠባበቁ የሚገልጽ ምላሽ ከኤሌክትሪክ ኃይል አግኝቷል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ያለውን ሙሉ አቅም አሟጦ እንዳይጠቀም በከተማዋ እየተባባሰ የመጣው የኃይል መቆራረጥ አንደኛውና ዋነኛው ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑም ተገልጧል፡፡

እንደ ደረጀ ገለጻ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሥራ በጀመረበት ወቅት በኹለት የጉዞ መሥመሮች ብቻ 41 ባቡሮች የነበሩት ቢሆንም ሁሉንም ሥራ ላይ ማዋል ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሚጠይቅ ከኻያ አምስት ባልበለጡ ባቡሮች እንዲሠራ መገደዱን አውስተዋል።

ስለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሕዝብ ግንኙነት ሞገስ መኮንን ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የተፈጠረው ችግር ጊዜያዊ እንደሆነና ባፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸው፥ ችግሩ የተፈጠረውም በቅርቡ አዲስ የተጀመረውን ‘የዲስትሪቢዩሽንና ኔትወርኪንግ’ ሥራዎችን ተከትሎ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ኃይል እንደሚቋረጥ ማሳሰቡን ተናግረዋል።

የከተማዋን ቀላል ባቡር በተመለከተ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ ሲሆን፥ ኅብረተሰቡንም በመጓጓዣ እጦት ምክንያት ከሚፈጠርበት መጉላላት እንደሚታደግ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here