ገዱ አንዳርጋቸው ባልተገኙበት ሹመታቸው ፀደቀ

0
512
  • ለማ መገርሳ እና አይሻ መሐመድ ቃለ መሃላ ፈፅመዋል

የቀድሞ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው በሌሉበት ተሹመዋል። ገዱ አንዳርጋቸው መጋቢት 10/2011 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት ለሹመት ከታጩት ውስጥ አንዱ ቢሆኑም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ አልፈፀሙም፤ ያልተገኙበትም ምክንያት አልተገለፀም።

ከገዱ አንዳርጋቸው በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ለሹመት የታጩት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ለማ መገርሳ እና የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ቀርበው ቃለ መሓላ ፈፅመዋል። በአዲሱ የሹመት ሥነ ስርዓት ለማ መገርሳ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ አይሻ መሐመድ ደግሞ ጃንጥራር አባይን ተክተው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በመሆን ተሹመዋል።

ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ከማገልገላቸውም በተጨማሪ በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ተመድበው ማገልገላቸው ተጠቅሷል። በትምህርት ዝግጅታቸውም የመጀመሪያ ዲግሪ በምጣኔ ሀብት ያገኙ ሲሆን፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል። ለማ በከፍተኛ የሥራ ጫና ምክንያት እስካቋረጡበት ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ ነበሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በመሆን የተሾሙት አይሻ መሐመድ የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here