ነጻ ፕሬስ ለዴሞክራሲ

0
690

ዴሞክራሲያዊ በጥቅሉ ሦስት ቅርንጫፎች አሉት። ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚው እና አስፈፃሚው አካል። ሦስቱ እርስ በርስ እየተጠባበቁ እና የእርስ በርስ ቁጥጥር እያደረጉ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ስርዓት እንዲኖር ያደርጋሉ። ይሁንና አራተኛው የመንግሥት ቅርንጫፍ (‘fourth estate’) የሚባለው ደግሞ አለ – ነጻ ፕሬስ።

ነጻ ፕሬስ በጥቅሉ ገለልተኛ የሆነውን ሚዲያ በሙሉ ይወክላል። ዴሞ-ክራሲ ማለት ሕዝባዊ-አስተዳደር ወይም ሕዝባዊ ተሳትፎ የተረጋገጠበት ስርዓት ነው ሲባል ወቅት እየጠበቁ ምርጫ ስለሚያደርጉ ብቻ አይደለም። በምርጫ ወቅት ይበጀኛል የሚሉትን አካል እንዲመርጡ ዕጩዎችን እና አማራጮችን በብቃት በማሳወቅ (‘well informed’ የሆኑ) መራጮችን ነጻ ፕሬሶች ያዘጋጃሉ። ምርጫ የቱንም ያህል ነጻ እና ርትዓዊ ቢሆንም መራጮች ስለ ዕጩዎች እና አማራጮች በቂ መረጃ ከሌላቸው ዴሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም።

በተጨማሪም፣ ዴሞክራሲ በምርጫ ወቅት ብቻ አይወሰንም፤ ይልቁንም በምርጫዎች መካከል ዜጎች የሚሳተፉበት እና ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩበት መንገድ መኖር አለበት። ይህንን የሚያስችሉት ነጻው ፕሬስና ሲቪል ማኅበራት ናቸው።

‘ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ሚዲያ አሲስታንስ’ የተባለ ድርጅት እ.አ.አ. በ2014 ባወጣው ሪፖርት የፕሬስ ነጻነት እና የአንድ አገር ሕዝቦች ነጻነት ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አሳይቷል። ማዕከሉ 100 መለኪያዎችን በማስቀመጥ ባደረገው ማወዳደር ጠንካራ እና ነጻ ፕሬስ ያላቸው አገራት ፖለቲካዊ ነጻነትም ያለባቸው አገራት መሆናቸውን በ95 በመቶ እርግጠኝነት አሳይቷል።
ነጻ ፕሬስ ባለባቸው አገራት ሙስናም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን እና የመንግሥት አሠራር ግልጽነት እንደሚረጋገጥ በተለያዩ ተግባራዊ ‘ኢምፔሪካል’ ጥናቶች ተረጋግጧል። በተጨማሪም የዓለም ኖቤል ሎሬት አማርትያ ሴን ‘ፍሪደም አዝ ዴቨሎፕመንት’ በሚለው መጽሐፋቸው እንዳመላከቱት ነጻ ፕሬስ ኖሮት ድርቁ ወደ ረሀብ የተሸጋገረበት አገር የለም። ይህም የሆነበት ምክንያት ነጻ ፕሬሱ ድርቁ ወደ ረሀብ ከመሸጋገሩ በፊት መረጃው ለሕዝብ ደርሶ አስፈላጊው ዕርዳታ እና ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ስለሚችል ነው።

በጥቅሉ ዴሞክራሲ ያለ ነጻ ፕሬስ ምሉዕ ሊሆን እንደማይችል ጥናቶች ሁሉ ያመላክታሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here