ከኻያ በላይ ቡና ላኪዎች ፍቃዳቸው ተመለሰላቸው

0
923

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዳይገበያዩ እገዳ ተጥሎባቸው ከነበሩ 81 የቡና ላኪዎች ውስጥ ከኻያ በላይ የሚሆኑት ፈቃዳቸው መመለሱን የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ባለሥልጣኑ እንደገለጸው ምክንያታቸው በኮሚቴ ታይቶ አሳማኝ ሆነው የተገኙ ከኻያ በላይ የቡና ላኪዎችን ፈቃድ እገዳው እንዲነሳና ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርገዋል። ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን በገቡት ውል መሠረት በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ቡናን ወደ ውጭ መላክ ባለመቻላቸው ፈቃዳቸው እንዲታገድ ማድረጉን ቢያሳውቅም ሌሎች ምክንያቶች እንደነበሩም ለአዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በቡና እና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ተወካይ ዳይሬክተር ትዕዛዙ ኢዶሳ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፥ ቡና ላኪዎች ከገዢዎች ጋር ውል በገቡ በሦስት ወራት ውስጥ ቡናውን መላክ እንዳለባቸው የሚደነግግ ሕግ ቢኖርም ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው 81 የቡና ላኪዎች እንዲታገዱ ሆነዋል ብለዋል። አያይዘውም ከገዢዎች ጋር ሳይሥማሙ የቀሩ የቡና ላኪዎች የውሉን መቋረጥ ለቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ማሳወቅ ቢኖርባቸውም ሳያሳውቁ ከሌሎች ገዢዎች ጋር በመሥማማት በቀጥታ በብሔራዊ ባንክ በኩል ግብይት ሲፈፅሙ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ውል መቋረጡን ባለማሳወቃቸው እንደኹለተኛ ውል እንደሚቆጠርባቸው እና ሕጋዊነታቸው ጥያቄ ውስጥ መግባቱም ለእገዳው አንደኛው ምክንያት እንደሆነ ታውቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዓለም ዐቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ሳያገኙ ሲሠሩ ነበሩ ያላቸውን ቡና ላኪዎች ባለሥልጣኑ እንዳገዳቸው እና ከ81 ቡና ላኪዎችም ውስጥ እንደሚገኙበት መረጃዎች ያመላክታሉ። የታገዱት ቡና ላኪዎች ካለፈው ጥር 24/2011 ጀምሮ በደብዳቤ ጥሪ ሲደረግላቸው የቆዩ ቢሆንም ምላሽ ባለመስጠታቸው ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ትዕዛዙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። በዚህም መሠረት እገዳው ከመጋቢት 6/2011 ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል። ትዕዛዙ ኢዶሳ ጨምረው እንደገለጹት፥ ታገዱት ቡና ላኪዎች አድራሻ እንደሌላቸው እና ማንነታቸው እንደማይታወቅ ተደርጎ በአንዳንድ የዜና አውታሮች የተነገረው ሐሰት መሆኑንም አስረግጠዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነፃነት ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፥ የታገዱት ቡና ላኪዎች አብዛኞቹ የምርት ገበያ አባላት ያልሆኑና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውስጥ መቀመጫ ያልነበራቸው እንደሆኑ ታውቋል። ግብይትም ይፈፅሙ የነበረው ምርት ገበያው አገናኝ ብሎ በሰየማቸው ሕጋዊ ሰውነት ባላቸው አካላት እንደሆነ የገለጹት ነፃነት መታገዳቸው በምርት ገበያው ገቢ ላይ የሚያሳድረው ጉልህ ጫና እንደማይኖር አክለዋል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በተጨማሪም ሲገልጹ ከሰኔ 2009 ጀምሮ “ቨርቲካል ኢንትግሬሽን” የሚባል አዲስ አሠራር ተግባራዊ እንደሆነና ይህም አርሶ አደሮች፣ የኅብረት ሥራ ተቋማትና ሌሎች ባለሀብቶች ቡናን በማቀነባበር ምርት ገበያን ሳይነካ በቀጥታ ለዓለም ዐቀፍ ገበያ የሚቀርብበት መንገድ መኖሩን ተናግረዋል። አያይዘውም እገዳ የተጣለባቸው ቡና ላኪዎችም በዚህ መንገድ ይነግዱ የነበሩ በርካቶች ናቸው ብለዋል።

እግዳቸው ያልተነሳላቸው ቡና ላኪዎችን በሚመለከት የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን አጣሪ እና ጉዳያቸውን የሚመለከት ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለው እንደሚገኝ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት ላይ እንደሚደርስ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 24 ሚያዚያ 12 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here