የሥጋ ነገር

0
1162

በተለምዶ ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው አንድነት ሥጋ ቤት በተቆጣጣሪነት የምታገለግለው ምዕራፍ ትዕግስቱ የሥጋ ተመጋቢ ደንበኞች የሥጋ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ትናገራለች። በተለይም በቡድን የሚመጡ ጓደኛሞች በጋራ እስከ አራት ኪሎ ጥሬ ሥጋ በአንድ ማዕድ መመገብ እንደተለመደ ታስረዳለች። በአዲስ አበባ የሚገኙ ሥጋ ቤቶች ቅዳሜ፣ እሁድ፣ ማክሰኞና ሐሙስ የሥጋና የአልኮል መጠጥ ፍላጎት ይጨምራል። በተለየ መልኩ ደግሞ ቅዳሜና ሐሙስ ሥጋ ቤቶቹ ተጨናንቀው ይስተዋላሉ።

የአንድነት ሥጋ ቤት ደንበኞች እንደሚናገሩት ለቤተሰባቸው እስከ 2 ኪሎ ይገዛሉ የምትለው ምዕራፍ በደሞዝ ወቅት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ይይዛል፣ የበዓል ቀን አንድ በሬ ላያልቅ ይችላል ምክንያቱም ሁሉም በየቤቱ ቅርጫ አለው እናም እርድ ስለሚያከናውኑ ገበያ ይቀንሳል። በፆም መያዣ ላይ የሥጋ ገበያ በጥሩ ሁኔታ የጦፈ ነው። በጾምና በፍስክ ወቅት ያለውን ልዩነት በንጽጽር መመልከት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ከሥጋ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ከፍተኛ ነው።

ጥሬ ሥጋ መበላት የጀመረበት ከክርስቶስ ልደት 29 ዓመት በፊት የሮማው ንጉሥ አውግስቶስ ቄሣራ አገራችን ኢትዮጵያን በሰሜኑ በኩል በጦር ወርሮ ለመግባት የጦር እንደራሴው የነበረ ጄኔራል ከመላኩ በፊት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥሬ ሥጋ ቢበላ እንደነውር ይቆጠርበት፣ የነበረ ብቻ ሳይሆን በፍፁም የተከለከለም እንደ ነበር ይታወቃል። በጦርነቱ ወቅትም ዘማች ሠራዊት ምግቡን ለማብሰል እሳት በሚያነድበት ስፍራ የሚወጣውን ጭስ በመመልከት የጠላት ሠራዊት አስከፊ አደጋ እያደረሰ በወገን ላይ ጉዳት ማመዘኑ፣ የወቅቱ ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች ደረሱበት። በጭሱ ሳቢያ የሚደርሰው ሽንፈትም እጅግ ስለበዛ ሥጋ ለማብሰያ እሳት እንዳይቀጣጠል፣ ጭስ እንዲቀር፣ የኢትዮጵያ ጦርም ጥሬ ሥጋ እንዲበላ እንደታዘዘ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥሬ ሥጋ መብላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ባህል ሆኖ መለመዱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሥጋ ሲነሳ በተለይ የጥሬ ሥጋ አመጋገብ በኢትዮጵያውያን ዕይታ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ተግባር ነው፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ የንፅህናና የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ኋላ ቀርነት ይታይበታል።

ሕገወጥ እርድ ለጤና ችግር መጋለጥ፣ ቆዳ እንዴት እንደሚገፈፍ ባለማወቅ አገራችን የሚያስፈልጋት የቆዳ ጥራት በሚፈለገው መልኩ አለመሆኑን በተለይም በበዓላት ወቅት ከድርጅቱ ውጭ የሚከናወኑ እርዶች ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ገቢ እንደምታጣ ከድርጅቱ እውቅና ውጭ የሚደረግ እርድ ሰዎች ከታክስ ለመሸሽ እንደሆነ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አታኽልቲ ገብረሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ንፁህ ሥጋ ለኅብረተሰቡ የማቅረብና ተረፈ ምርት የማምረት ሥራ የሚሠራ ሲሆን በቀን 1 ሺሕ 500 በሬ እና 1 ሺሕ 500 ፍየልና በግ የማረድ አቅም አለው ያሉት ኃላፊው አሁን ላይ እየተበራከተ ያለው ሕገወጥ እርድ ኅብረተሰቡ እንዲከላከልና ጤናማ የሆነ ሥጋ እንዲጠቀም ይመክራሉ። ከሌላው ጊዜ በተለየ በዘንድሮ ፋሲካ በዓል ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ እርድ እናከናውናለን ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።

አገራችን በሥጋ ተመጋቢ ከዓለም 11ኛ ስትሆን አንድ ሰው በቀን በአማካይ 8 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም እንደሚመገብ መረጃዎ ያሳያሉ፤ ሆኖም የሥጋ መሸጫ ልኳንዳ ቤቶቻችን ከመኪና ማውረድ ጀምሮ እስከ ሽያጭ እስከሚቀርብበት ያለው ከመንገድ ዳር ሆነው የተለያዩ የመኪና ጭስ አቧራ የሚቅም፣ በዓይን ለማይታይ ጀርምና ባክቴርያ የሚጋለጠውም ቀላል የሚባል አይደለም።
ጥሬ ስጋ ለሰውነት ግንባታና ለደም ስሮች መስሪያነት እንደግብአትነት ቢያገለግልም ሰዎች በብዛት እና አዘውትረው ሲጠቀሙ ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች ያሉ ሲሆን እነርሱም ለኮሶ፣ ለሪህ (የመገጣጠሚያ አካባቢ የሚያጋጥም ህመም)፣ የዩሪክ አሲድን መጠን በሚጨምር የኩላሊት ጠጠር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ በየረር አጠቃላይ ሆስፒታል ጠቅላላ ሃኪም የሆኑት አንተነህ ዳኛቸው (ዶክተር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአገራችን በሰፊው የሚስተዋለው የሥጋ መሸጫ ልኳንዳ ቤቶች መንገድ ዳር በመሆናቸው ለባክቴሪያ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው።

ጥሬ ሥጋን ስንመገብ በተጓዳኝ ንፁሕ ውሃ መጠጣት አለባቸው ያሉት አንተነህ ከዚህም ባሻገር የኮሌስትሮን መጠንን ለማመጣን በቀን ኹለት ቢራ ቢጠቀሙ ይመከራል።

መጪው የፋሲካ በዓልን ተከትሎ ለኹለት ወራት የተፆመ ፆም ስለሆነ ከፍተኛ የሆነ ቅባት ምግቦች መጠንቀቅ አለባቸው፣ ሥጋን በጥሬ ከመጠቀም ይልቅ ከ60-75 ዲግሪ ሴንቲግሬድ አብስሎ በመጠቀም አለባቸው ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here