የ6 ቢሊዮን ብር የሐሰት ግብይት የፈፀሙ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

0
635
  • የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎቹ ከመረጃ ቋት ጋር እንዲናበቡ የሚያደርግ ሶፍት ዌር ለመተግበር ዝግጅት ተጠናቋል

ያልተፈፀመ ግብይት አድርገናል በሚል ሐሰተኛ ደረሰኝ በማቅረብ ግብር ለማጭበርበር የሞከሩ 183 ድርጅቶች ላይ ስድስት ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የውሸት ግብይት ፈፅማችዋል በሚል እርምጃ መወሰዱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። ድርጅቶቹ ባላከናወኑት ግብየት ደረሰኝ በመግዛት ግብር በመሰወራቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ድርጅቶቹም የተለዩት በምርመራ እና በግብር ኦዲት ወቅት ሲሆን ገቢያቸውን ዝቅ በማድረግ እና የሚያወጡትን ወጪ ከፍ በማድረግ ሲያጭበረብሩ በመቆየታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ግብር ከፋዮች በራሳቸው ግዜ ገቢያቸውን እንዲያሳውቁ ህጉ የሚፈቅድ ሲሆን ካሳወቁ በኋላ ግን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ኦዲት ያደርጋል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ከ400 በላይ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች እንደጠፉበት እና አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሊያገኛቸው ወይም ከአገልግሎት ውጪ ሊያደርጋቸው እንዳልቻለ ሲያስተውቅ ነበር፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ሚኒስትሩ 124 ድርጅቶችን ለተመሳሳይ ወንጀል ሲፈልግ ቆይቶ 14 ድርጅቶች በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እየተንሰራፋ የመጣውን የደረሰኝ ንግድ ከሚኒስቴሩ ካዝና ቢሊዮኖች በተመላሽ መልክ እንዲዘረፍ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ድርጅቶቹም ያለ እቃ ልውውጥ ደረሰኝ ከመሸጣቸው በዘለለ ሐሰተኛ ንግድ ፍቃድ ፣ በሐሰተኛ የመሥራች ጽሁፍ ፣ በሐሰተኛ መታወቂያ የተቋቋመ እና ሐሰተኛ የግብር ክፍያ መለያ ቁጥር በመጠቀም ግብር የማያሰውቁ በመሆናቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ችግሩን ለመቆጣጠር ሲሞክር ቢቆይም ባለፉት 9 ወራት ብቻ 6 ቢሊዮን ብር በሐሰት ግብይት መፈፀሙን ደርሶበታል ፡፡
ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ከመያዝ ባለፈ ሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖቹ በሚኒስቴሩ የመረጃ ቋት ላይ እንዲታዩ እና ተመሳሳይ ደረሰኝ በማዘጋጀት የማጭበርበሪያ መንገድ የሚጠቀሙበትን መንገድ ለማስቀረት እየተዘጋጀ ያለውን የኮምፒተር ፕሮግራም በቅርቡ አጠናቀን ይፋ እናረጋለንም በማለት ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ ተናገሯል፡፡

ለሕጋዊ የንግድና የታክስ ስርዓት መጎልበት የሁሉም ዜጋ አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በሽያጭ ወቅት ደረሰኝ መስጠት የሻጭ መቀበል ደግሞ የገዥ ኃላፊነት ነው፡፡ ይንንም ለማጠናከር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ መስሪያ ቤቱ ገልፃል፡፡

ደረሰኝ በዕቃ ወይም በአገልግሎት ግብይት ላይ ተመስርቶ ከአቅራቢው ለገዥው የሚሠጥና ግብይት ስለመፈፀሙ፣ ገንዘብ ስለመሰብሰቡ፣ ዋጋው ስለመከፈሉ ወይም ለወደፊት ለመክፈል ውል መግባቱን የሚያሣይ ሰነድ ሲሆን ሁሉም ግብር ከፋዮች የንግድ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ግብይቱ ግዴታ በደረሰኝ የተደገፈ መሆን ይኖርበታል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here